1የካቲት ፳፻፲፰ቅጽ ፪ ቁጥር ፰
2ዋና አዘጋጅውብአረገ አድምጥምክትል አዘጋጅሩት ሃብተማርያምአርታኢልዑልሰገድ አሥማማውዝግጅት ክፍልግራፊክስ ዲዛይንብርሃን ደርበው
3ማውጫ05ነፃ ፈቃድ (Free Will) vs ተወሳኝነት (Determinism)ዮናስ ታደሰ1820መሰንበት ነው ደጉፍሬው ማዕሩፍ29የሞት መልስ ቅኝቶችውብአረገ አድምጥእውነትና ስሜትዘውዴ አለልኝ
448አብረን እንውደቅ?ቴዎድሮስ የማነብርሃን ለማ53ለቁጭት እንባ እንኳን የሚሆን...ዮዲት አማኑኤል
5ነፃ ፈቃድ (Free Will) vs ተወሳኝነት (Determinism)ዮናስ ታደሰቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
6ነፃ ፈቃድ (Free Will) vs ተወሳኝነት (Determinism)ዮናስ ታደሰእንደ መግቢያእኛ ሰዎች በውሳኔዎቻችን ላይ ነፃ ቁጥጥር ያለን ፍጥረቶች ነን ወይስ አይደለንም? ይህ ጥያቄ የተለያየ የሐሳብ ቅርፅ ይዞ ከጥንት ግሪክ ጀምሮ ታላላቅ ፈላስፎችንና አሳቢዎችን ሲያከራክር የቆየ የ “ነፃ ፈቃድ ወይስ ተወሳኝነት” (Free will vs Determinism) ክርክር ምንጭ ነው። ገና ከጥንት “ሰው በዕድል ዕጣ-ፈንታ ነው የሚመራው ወይስ በራስ-ወከልነት (Fate vs Agency)” በሚል ክርክር ጀምሮ፤ “በፈጣሪ ውሳኔ የሚመራ ነው ወይስ በውሳኔዎቹ ላይ ነፃነት አለው (God vs Freedom)” በሚል አልፎ፤ አሁን ድረስ፣ “በሳይንሳዊ ምርምር ተለይተው ሊታወቁ በሚችሉ ደረቅ የመንስኤና ውጤት መካኒክሶች ቁጥጥር ውስጥ ያለ ነው ወይስ፣ ስለ ውሳኔዎቹና ድርጊቶቹ ሐላፊነት መውሰድ የሚችል አካል ነው? (Science vs Responsibility)” በሚል ክርክር እንደቀጠለ ነው።አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኒውሮ ሳይንስ ጥናት እድገትና የአርተፊሻል ኢንተሊጀንስ (AI) ክስተት፣ የነፃ ፈቃድ እና የተወሳኝነት ክርክሩን በአዲስ መልክ እያሟሟቀው ይገኛል። በዚህ ፅሑፍ የነፃ ፈቃድ (Free will) እና የተወሳኝነት (Determinism) መከራከሪያ ሐሳቦችን እንመረምራለን። የአንደኛው ጎራ አቀንቃኞች በሌላኛው ጎራ አቀንቃኞች ሐሳቦች ላይ የሚሰነዝሯቸውን ትችቶች እንፈትሻለን። በመጨረሻም የነፃ ፈቃድ ብያኔን እና መገኛ ቦታን (locus) ለዘመናት ከቆየው የክርክር አውድ በማላቀቅ በአዲስ መልክ የሚበየኑበትን መንገድ እንጠቁማለን። ሙሉ የፅሑፉ ሐሳብ እጅግ ሰፊ በመሆኑ፣ በሦስት ተከታታይ ክፍሎች ለማቅረብ እንሞክራለን። ለዚህ ፅሑፍ እንደ ማጣቀሻ የተጠቀምኩባቸውንና ሐሳብ የተዋስኩባቸውን መፃሕፍቶችንና አርቲክሎችን ወይም መጣጥፎችን ብዙ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹን ከስር አስቀምጣቸዋለሁ። ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
7ነፃ ፈቃድ vs ተወሳኝነትአሁን የነፃ ፈቃድ እና የተወሳኝነት ብያኔዎችን አስቀምጠን በሁለቱም ጎራዎች አቀንቃኞች መሐል ወደ አለው ክርክር እናመራለን። ነፃ ፈቃድ ማለት ሰዎች የተወሰኑ አእምሮአዊና አካላዊ ድርጊቶችን ማስነሳትና መቆጣጠር ይችላሉ፤ ይህም ከፊታቸው የተደቀኑ ሌሎች አማራጭ ድርጊቶችን ማድረግ እየቻሉ የመረጡትን በነፃነት መርጠው የሚያደርጉት ነው የሚል ሐሳብ ነው።ተወሳኝነት ደግሞ ሁሉም ተግባሮቻችን (አእምሮአዊና አካላዊ) ከቁጥጥራችን ውጪ በሆኑ ኃይሎች መንስኤነት እና አስገዳጅነት የሚከናወኑ እንጂ ማንኛውም ድርጊት ቢሆን በነፃነት የሚመረጥ ነገር አይደለም የሚል ሐሳብ ነው። 1.1 የነፃ ፈቃድ መከራከሪያዎች (The Case for Free will)በነፃ ፈቃድ አቀንቃኞች ዘንድ፣ “ለመሆኑ የፈቃድ ነፃነቱ መገኛ ቦታ የት ነው?” ለሚል ጥያቄ የተለያየ ምላሽ ነው ያላቸው። የተለያዩ የነፃ ፈቃድ ብያኔዎችና ሀልዮቶችም ተሰጥተዋል። አንኳር የሚባሉትን ሦስቱን እንመለከታለን።፩. የድርጊቶች ምርጫ (Choice of Actions)የዚህ ሀልዮት አቀንቃኞች በስፋት ህልውናውያን/ኤግዚስቴንሻሊስቶች ሲሆኑ፤ ወደ ዘርዓያዕቆብ የፍልስፍና ት/ቤት ልሂድ ወይስ አልሂድ፣ ቫኒላ ልብላ ቸኮሌት፣ ከፍቅረኛዬ ጋር ሲነማ ልግባ ወይስ ኳስ ልመልከት፣ እውነት ልናገር ወይስ ልዋሽ... ወዘተ አይነት ድርጊቶች ወደ ምንም አይነት መንስኤ የማንቀንሳቸው በነፃ ፈቃዳችን መርጠን የምናከናውናቸው እንደሆኑ ይናገራሉ። በዚህም አማራጭ ድርጊቶች መሰረታዊ የነፃ ፈቃድ መገኛ ቦታ ናቸው ማለታቸው ነው። ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
8በእርግጥ በነዚህ ድርጊቶች ውስጥ ምርጫ እንዳለ ሁሉም የነፃ ፈቃድ ሀልዮቶች አቀንቃኞች ይስማማሉ። የድርጊት ምርጫ አቀንቃኞች በተለይ እያሉ ያሉት ግን እነዚህ ምርጫዎች ወደ ምንም ዓይነት መንስኤ የማንቀንሳቸው ተቀዳሚ ምርጫዎች ናቸው፤ አማራጭ ድርጊቶች የነፃ ፈቃድ መገኛ ቦታ ናቸው ነው።ይህ ዓይነቱ የነፃ ፈቃድ መገኛ ቦታ ብያኔ ግን ለብዙ ትችቶች የተጋለጠ ነው። በግልፅ ማየት እንደሚቻለው የሰዎች ድርጊቶች በዚህ መልኩ ድንገት ደራሾች (spontaneous) አይደሉም። በተለያዩ የአእምሮ ውሳኔዎች ላይ የሚመረኮዙ ናቸው። እነዚህ የድርጊት ውሳኔዎች እንዲሁ በባዶ ሜዳ የሚሰጡ ሳይሆን፤ በአንድ ሰው እውቀት፣ ፍላጎት፣ ዓላማ... ወዘተ ላይ በመመስረት ነው። አንድ ሰው የሆነን ድርጊት ያለምንም ቅድመ ዝግጅት በችኮላ ሲሰራ እንኳ አስቀድመው አእምሮው ውስጥ በነበሩ ሐሳቦችና ተግባራት መግፍኤ ምክንያትነት የሚሰራቸው ናቸው።እንደ ሳርተር ያሉ ኤግዚስተንሻሊስቶች ግን ለምሳሌ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በገደል አፋፍ አጠገብ እየተራመድን እያለ ጓደኛዬን ከገደል አፋፉ ገፍትሬ ልጣለው አልጣለው የሚለው የድርጊት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ በነፃ ፍቃዴ ላይ የሚመረኮዝ ነው ይላሉ። እንዲህ ዓይነቱ ሀልዮት ንቃተ-ህሊና የባህሪ ቁጥጥር ላይ ምንም ዓይነት ሚና እንደሌለው አድርጎ የሚወስድ ነው። ማለትም በሐሳቦች፣ እሴቶችና እምነቶች እና በድርጊቶች መካከል ሸለቆ በመፍጠር ሰው በራሱ ላይ ምንም ዓይነት ቁጥጥር የሌለው ፍጥረተ-ህይወት (organism) ያደርገዋል። ነፃ እንድንሆን የተረገምን ነን—we are condemned to be free—የሚለውን ዝነኛ የሳርተር አባባል ልብ ይሏል።፪. የመግፍኤ ምክንያት ምርጫ (Choice of Motives)ይህ ሀልዮት ደግሞ የተለየ የ “ፈቃድ” ፋኩልቲ አለን የሚል ነው። ይሄም ከሁለት ተፎካካሪ/ተወዳዳሪ ምኞቶች/ፍላጎቶች የትኛው ፍላጎት ነው ለድርጊት መነቃቃት ያለበት ብለን ወስነን እንድንመርጥ የሚያስችለን ነው የሚል ነው። ነፃ ፈቃድ በፍላጎቶቻችን እና በድርጊቶቻችን መካከል ጣልቃ እየገባ የሚወስን ፋኩልቲ ነው ማለት ነው።የረውማንትሲስት (Romanticist) ፈላስፎች የዚህ ሀልዮት አቀንቃኞች ናቸው። እንዲህ አይነት እይታ ያላቸው ሃይማኖተኞችም ብዙ ናቸው። ይህ ዓይነቱ የነፃ ፈቃድ መገኛ ቦታ ብያኔም ቢሆን ግን ልክ እንደ የድርጊቶች ምርጫ ተመሳሳይ ትችቶች የሚሰነዘርበት ነው። ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
9ይሄኛው ሀልዮት ድርጊቶችን ሳይሆን ምኞቶችን/ፍላጎቶችን ነው ተቀዳሚ ያደረገው። ነገርግን ፍላጎቶችም ቢሆን ልክ እንደ ድርጊቶች አእምሮ ውስጥ ባሉ አስቀድመው በተሰሩ ወይም በተከናወኑ ሐሳቦች እና ተግባራት መግፍኤነት ላይ የሚመረኮዙ ናቸው።ፍላጎቶች አእምሮአዊ-ስሜቶች (emotions) ናቸው። ስሜቶቻችንን በነፃ ፈቃዳችን መምረጥ የምንችላቸው ናቸው ቢባል እንኳ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የምንመርጣቸው? የሚል ጥያቄ ለመመለስ ስንሞክር ችግር ያለበት እሳቤ መሆኑን እንገነዘባለን። ለምሳሌ አንድ ሰው እውነትን በአደባባይ መናገር እየፈለገ የመንጋ ቁጣና ዘለፋን ፈርቶ ደግሞ ውሸት መናገርን ቢፈልግ፣ ይህ ሀልዮት የዚህ ሰው ምርጫ ምንም መንስኤ የሌለው ጭፍን ምርጫ እንደሆነ ነው የሚነግረን። ማለትም እውቀት፣ አሰላስሎት፣ ከራስ ጋር ምክክር መንስኤያዊ አግባብ የሌላቸው (causally irrelevant) ናቸው ነው የሚለን። ይህ ግን ከላይ የድርጊቶች ምርጫ ላይ እንደተመለከትነው ችግር ያለበት እሳቤ ነው። ፫. የሐሳቦች ምርጫ (Choice of Ideas) ይህ ሀልዮት ደግሞ (ከሌሎቹ ሀልዮቶች ትንሽ ጠለቅ ብሎ) አንድ ሰው የትኞቹን ሐሳቦችና የእሴት ዳኝነቶች መቀበል እንዳለበት በነፃ ፈቃዱ መምረጥ ይችላል ይለናል። ምንም እንኳ የድርጊቶቻችን እና የመግፍኤ ምክንያቶቻችን ምርጫዎች በእምነቶቻችን እና በእሴቶቻችን ላይ የሚመረኮዙ ቢሆኑም ቅሉ፤ ምን ማመንና ምን በእሴትነት መቀበል እንዳለብን ግን በቀጥታ ነፃ ፈቃዳችንን የሚመለከት ጉዳይ ነው ይለናል። አሁንም ቢሆን ይህ ዓይነቱ የነፃ ፈቃድ መገኛ ቦታ ብያኔም ልክ እንደ የድርጊቶች ምርጫ እና የመግፍኤ ምክንያት ምርጫ ተመሳሳይ ትችቶች የሚሰነዘርበት ነው።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
10እምነታችንን ተቀዳሚነት ባለው ምርጫ የምንመርጠው ነገር አይደለም። የሐሳቦች ዓይነት እና መጠነ ስፋት ታሳቢ ያደረጉ የተለያዩ ሂደቶችን አልፈን የምንቀበለው ነው። ወደ መደምደሚያዎቻችን ላይ የምንደርሰው ሎጂካል ወይም ምክኑያዊ በሆነ መንገድ ነው ወይስ ኢምክኑያዊ በሆነ መንገድ በሚል ሂደት ላይ የሚመረኮዙ ናቸውና። ማለትም እምነታችንን እና ወደ እምነታችን እንድንደርስ ያደረገንን ሂደት ነጣጥለን ማየት አንችልም። አንድን ድምዳሜ ትክክል እንደሆነ ከገባኝ ወይም ግልፅ ከሆነል፣ ያንን ድምዳሜ አምኛለሁ ወይም ተቀብያለሁ ማለት ነው። ለምሳሌ፣ ከፊት ለፊቴ የምመለከተው ነገር ቀይ ጨርቅ መሆኑን አረጋግጫለሁ ቀይ ጨርቅ መሆኑ ለማመን ግን ገና አልመረጥኩም ማለት አይቻልም።1.2 የተወሳኝነት መከራከሪያዎች (The Case for Determinism) እንደ ተወሳኝነት ከሆነ ሁሉም ኩነቶች—በቁጥጥራችን ስር ናቸው ብለን የምናስባቸው ኩነቶችንም ጨምሮ ምን አይነት ስራ ላይ እንደምንሰማራ፣ ምን አይነት ሰው እንደምናገባ፣ አስተማሪ ነው የምንሆነው አሸባሪ፣ የምንወደው የከለር ምርጫችን፣ ወደ ክላስ እንሄዳለን ወይስ እንቀራለን... ወዘተ—አስቀድመው በነበሩ ኩነቶች መንስኤነት የምናከናውናቸው ናቸው። ከነዚህ ኩነቶች በፊት የነበሩ መንስኤ ኩነቶችስ? ብለን ጠይቀን ወደኋላ ምንጭ ፍለጋ ስንጓዝ ከመወለዳችን በፊት፣ የሰው ልጅ ምድር ላይ ከመከሰቱ በፊት፣ ህይወት ምድር ላይ ከመከሰቷ በፊት፣ መሬትም ይሄ አሁን ያለችበትን ቅርፅ ከመያዟ በፊት... እያለ Sam Harris እንደሚለው ወደ ዩኒቨርሱ የሚያመራን እና የዩንቨርሱ መጫወቻ አሻንጉሊት—a puppet of the universe—መሆናችንን እንገነዘባለን። በዚህ እሳቤ ውስጥ ያሉ ወሳኝ የሚባሉ የተወሳኝነት መከራከሪያዎችን እንመለከታለን። ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
11፩. ሐሳቦቻችንን መምረጥ አንችልምበአእምሮአችን ውስጥ የሚፈጠሩትን ሐሳቦች መርጠን ልናመጣቸው/ልናምጣቸው አንችልም። ምክንያቱም እንድንመርጣቸው ከማሰባችን በፊት ልናስባቸው ነው። አስቀድሞ ያልነበረ (አእምሮአችን ከሚያቀርብልን ውጪ) ነገር ደግሞ ማሰብ አንችልም። ለምሳሌ: “ፀሐይ በምስራቅ...” ወይም “2 + 2 = ...” የሚሉ ያልተቋጩ ጅምር አረፍተ ነገሮችን ስናነብ፤ መቋጫ ሐሳቦቹን አእምሮአችን ላይ ሲከሰቱ እንጂ መርጠን ስናመጣቸው አናስተውልም። እንግዲህ ጥያቄው በማሰብ ሂደት ውስጥ ቀጥሎ የሚመጣ ሐሳባችንን መቆጣጠር ወይም መምረጥ የማይቻለን ከሆነ፣ ቀጣዩ ሐሳባችን ከመከሰቱ በፊት ምን አይነት ሐሳብ እንደሚሆን መወሰን የማይቻለን ወይም ደግሞ እንዳይከሰት መከላከል የማይቻለን ከሆ፣ ሐሳብ የመምረጥ ነፃነታችን የት አለ? የሚል ነው። የዚህን መከራከሪያ ሐሳብ አፅንኦት ለመስጠት ያክል የSam Harris ምሳሌ እንጠቀም። ሐሪስ ስለሆነ ዋና ከተማ እንድናስብ ይጠይቀንና፣ “አለም ላይ ካሉ ዋና ከተሞች መካከል ልንመርጠው የምንችለው ከተማ ላይ የምንደርስበትን ሂደት ስናስተውል ለነፃ ፈቃድ ማስረጃ የሚሆን ነገር ልናገኝ አንችልም። እንግዲህ ነፃ ፈቃድ የሚባል ነገር ቢኖር ኖሮ ግን እዚህ ላይ ነው ማግኘት የነበረብን” ይለናል ሐሪስ። ሐሪስ ነገሩን (ዋና ከተማ የመምረጥ ሂደቱን) ዘርዝሮ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል:-ሄዳችሁ ሄዳችሁ፣ “ፓሪስን እወዳታለሁ፣ ፓሪስን ነው የምመርጥው“ ብላችሁ ባሰባችሁበት መጨረሻ ቅፅበት ላይ ፣ “አይ ቶክዮ ይሻላል ቶክዮ ይሻለኛል” ብላችሁ ወሰናችሁ። ይሄ አይነቱ የመምረጥ ሂደት ነው እንግዲህ ሰዎች ነፃ ፈቃድ አለ እንዲሉ የሚያደርጋቸው።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
12“ነገር ግን፣ ነገርየውን በደንብ ቀረብ/ጠለቅ ብላችሁ ብትመረምሩት” ይለናል ሐሪስ:-“የመረጣችሁትን ነገር—ከፓሪስ ይልቅ ቶክዮን የመረጣችሁት—ለምን እንደመረጣችሁት የምታውቁበት ምንም መንገድ የለም። ምናልባት ‚በትናንትናው ዕለት የጃፓን ሱሺ (sushi) በልቼ ነበር‘ ልትሉ ትችላላችሁ። ነገር ግን ይሄን ለምን እንዳስታወሳችሁት ወይም ደግሞ የጃፖን ምግብ መብላታችሁ በአእምሮአችሁ ሜሞሪ መመዝገቡ ቶክዮን እንድትመርጡ ለምን እንዳስቻላችሁ ማብራራት አትችሉም። ለምሳሌ፣ ‚ትላንት የጃፓን ምግብ ስለበላሁ ከጃፓን ከተማ ውጪ የሆነ ሌላ አዲስ ነገር ልምረጥ‘ ብላችሁ ለምን አልወሰናችሁም?”“ጉዳዩ ያለው” ይላል ሐሪስ፣ “የንቃተ ህሊና ባለቤት እንደመሆናችሁ መጠን የውሳኔውን ሂደት መታዘብ ትችላላችሁ እንጂ ውሳኔዎችን እየሰጣችሁ አይደለም። ቶክዮን የመምረጣችሁ ነገር ሌላ ሰው መርጦ ከሚሰጣችሁ ምርጫ ጋር ምንም ልዩነት የለውም።”ሐሪስና መሰል ተወስኖታውያን ከዚህ የሚደመድሙት ነገር፡ ሐሳቦች ከእኛ ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ኃይሎች መንስኤነትና አስገዳጅ መግፍኤነት የሚፈጠሩ መሆናቸውን ነው። “ሐሳቦቹን የሚያስባቸው አካል እኮ እኔ ነኝ ልትሉ ትችላላችሁ ግን ይመስላችኋል እንጂ አይደላችሁም፤ ሐሳቦች እንዲሁ ነው አእምሮአችሁ ውስጥ የሚከሰቱት። ‚እንዴ ሐሪስ ምንድን ነው የሚለው? እኔ አለሁ እኮ አሳቢው?‘ የሚለው ሐሳባችሁ ራሱ በአእምሮአችሁ ውስጥ እንዲሁ የተከሰተ ሌላ ሐሳብ ነው” ይለናል ሐሪስ። በዚህ ዓይነቱ የሐሪስ እይታ እንግዲህ እኛ ሰዎች ግብረ-መልስ ሰጪዎች (reactors) እንጂ አሳቢዎች አይደለንም—የዩኒቨርሱ መጫወቻ አሻንጉሊቶች ነን—you are a puppet being played by the universe. ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
13፪. አንድን ድርጊት የምናደርገው ልንሰራው/ልናደርገው ስለፈለግን ወይም እንድናደርገው ስለተገደድን ነውይህ የነፃ ፈቃድ መቃወሚያ ሐሳብ ደግሞ ድርጊቶችን ሁሉ በፍላጎቶቻችን መግፍኤነት የሚከናወኑ ወይም ደግሞ ፍላጎቶቻችን አስገድደውን የምናከናውናቸው ናቸው ይላል። ከፍላጎቶቻችን ውጪ በአስገዳኝነት የምናደርገው ነገር ከቁጥጥራችን ውጪ ነው፤ ፈልገን የምናደርገው ነገር ደግሞ ፍላጎቶቻችንን መቆጣጠር ስለማንችል ድርጊቶቻችንን በቁጥጥራችን ስር ናቸው ማለት አንችልም።ሐሪስ እንዲህ ይገልፀዋል:-“አሁን በዚህ ስአት የትየሌለ ዓይነት ነገሮችን ለማድረግ የሚያስችለን ነፃነት አለን—ነፃነት ሲባል ማንም መጥቶ በኃይል አስገድዶ እንድናደርጋቸው የሚጫነንን፤ ወይም ካደረግናቸው የሚያስረን አካል በሌለበት ሁኔታ ማለት ነው። እንዲያም ሆኖ የማንፈልገውን ነገር የመፈለግ ወይም ደግሞ የምንፈልገውን ነገር ደግሞ ከምንፈልገው በላይ እንድንፈልገው የሚያስችል ነፃነት የለንም። እናስ ታድያ ፍላጎቶቻችን ከእኛ ቁጥጥር ውጪ አእምሮአችን ውስጥ አስቀድመው የተከናወኑ ኩነቶች ውጤት ከሆኑ፤ የምንፈልገውን የማድረግ ነፃነታችን የት ነው ያለው?”፫. ነፃ ፈቃድ የመንስኤነት ህግን የሚቃረን/የሚጥስ ነው (Free Will would violate the law of causality)የዚህ ሐሳብ ዋና መከራከሪያ፡ ሁሉም ኩነቶች አስቀድመው ከነበሩ ኩነቶች መንስኤነት፣ ሁሉም ድርጊቶች ደግሞ ከዚያ በፊት ለነበሩ ድርጊቶች ግብረ-መልሶች በመሆናቸው ነፃ ፈቃድ የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም የሚል ነው። በዚህ እይታ መሰረት በመንስኤ እና ውጤት ህግ አስቀድመው በነበሩ ኩነቶች አስገዳጅ መግፍኤነት የማይከሰት ኩነት መንስኤ አልባ፣ የዘፈቀደ ኩነት ነው የሚሆነው። የዘፈቀደ ኩነት ደግሞ በእኛ ፈቃድ የተደረገ ሳይሆን በአጋጣሚ ወይም ደግሞ በእድል የሚከሰት ነገር ነው የሚሆነው። በዚህም አለ በዚያ እኛ መንስኤ አይደለንም፤ ስለዚህ ኩነቱ በኛ ቁጥጥር ስር አይደለም ማለት ነው።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
14ሐሪስን ጨምሮ አብዛኞቹ ተወስኖታውያን፣ “ምርጫዎች”፣ “ጥረቶች”፣ “ዓላማዎች”፣ “አመክንዮዎች”...ወዘተ የሚባሉ ነገሮች ባህርያቶቻችን ላይ ተፅዕኖ እንዳላቸው ወይም ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ይቀበላሉ። ነገር ግን እነዚህ ተፅዕኖዎች ራሱ ከአእምሮአዊ ንቃት በፊት የነበሩ የመንስኤ-ውጤት ሰንሰለቶች አካል ስለሆኑ በነርሱ ላይ ቁጥጥር የለንም፤ ስለዚህ ቁጥጥር የሚባል ነገር ስሁት የምናብ ምስል (illusory) ነው ይላሉ። ሐሪስ እንደሚለው:-“በማሰብ ሂደት ውስጥ ቀጥሎ የሚመጣ ሐሳብና ድርጊት በአእምሮአችን ውስጥ ሊፈልቅ የሚችለው ከነዚያ አስቀድመው ከነበሩ የመንስኤ-ውጤት ሰንሰለቶች ድምር ውጤት ብቻ ነው። ሊከሰት የሚችለውም ከሁለት መንገዶች በአንዱ ብቻ ነው። ህግ ተከትሎ—ልክ እንደ ዶሚኖ አንዱ በሌላላኛው ላይ ግፊት እያሳረፈ፤ ወይም ደግሞ በዘፈቀደ።”የዚህን መከራከሪያ ሐሳብ አፅንኦት ለመስጠት ያክል ስለ አንድ ነፍሰ ገዳይ በምሳሌነት እንድናስብ ይጠይቀናል—ሐሪስ። ይህ ገዳይ ለመግደል የሚነሳሳው አንጎሉ ውስጥ አስቀድመው በሚፈጠሩ መንስኤዎች—መጥፎ ጂኖች፣ የልጅነት አስተዳደጉ ሁኔታ፣ የእንቅልፍ እጦት ምክንያት (ለምሳሌ ማታ ላይ የሆነ የአምቡላንስ ሳይረን እየጮኸ እየረበሸው ስላደረ) ...ወዘተ—የሚወሰኑ ኒውሮፊዚዮሎጂያዊ ኩኖቶች አማካኝነት ነው። እነዚህ ኩነቶች ከማንኛውም የንቃት ውሳኔዎች በፊት ቀድመው የሚከሰቱ ኩነቶች ናቸው። ታዲያ ይህ ነፍሰ ገዳይ ወንጀሉን የፈፀመው በራሱ ፈቃድ ነው ማለት ምን ማለት ነው? ይህ አባባል አንዳች ትርጉም ሊኖረው ከሆነ ነፍሰ ገዳዩ ከግድያ ድርጊቱ የተለየ ሌላ ድርጊት መፈፀም ይችል ነበር ማለት ነው። ማለትም ግድያውን ለመፈጸም የሚገፋፋውን ግፊት መቋቋም ይችል ነበር፣ ወይም ግደል ግደል የሚለውን ስሜቱን ከነአካቴው አፍኖ ማስቀረት ይችል ነበር ማለት ነው። ይህን ማድረግ የሚችለውም ንቃተ ህሊናው በማይቆጣጠራቸው አንዳንድ የዘፈቀደ ተጽዕኖዎች ስር ወድቆ ሳይሆን የሐሳቡ እና የድርጊቶቹ ንቁ ደራሲ መሆን ይችል ስለነበር ነው ማለት ነው። ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
15“ችግሩ ግን” ይለናል ሐሪስ፣ “ማንም ሰው ቢሆን እነዚያ አእምሯዊ እና አካላዊ ክስተቶች ሊፈጠሩ የሚችሉበትን እንዲህ አይነቱን ነፃነት ትርጉም ሊሰጥ በሚችል መልኩ ማብራራት የቻለ የለም። ነውጠኛ ወንጀለኞች እንዲህ ዓይነት ነፃነት እንዳላቸው ስናስብ፣ ስለ ድርጊታቸው በአጸፋዊ ስሜት እንወቅሳቸዋለን። ነገር ግን ይህንን ሰፊ የመንስኤያዊነት መረብ በምናስተውልበት ጊዜ ተወቃሽ ለማድረግ የሚያስችለን ያልነው ያ የፈቃድ መሰረት ተኖ የሚጠፋ ይመስላል። ወደ ልጅነት እና ከዚያም በፊት ወደ ተከናወኑ ኩነቶች ሚመዘዙ የመንስኤና ውጤት ጅረቶችን ማስተዋል በቻልን ጊዜ ደግሞ ‘ወንጀለኛ‘ ያልነውን ሰው በጥፋተኝነት የመክሰስ ስሜቱም ሆነ ሐሳቡ ተንኖ መጥፋት ይጀምራል።”የጉዳዩን ክብደት ለማሳየትም፣ “የእንደዚህ አይነት ሰው ባህሪ እጅግ የሚያሳምመኝን ያክል፣ ከእሱ ጋር ቦታ—አቶም ለአቶም—ብንቀያየር እሱን እንደምሆን ማመን አለብኝ። ምክንያቱም ንፁሀን ሰዎችን ለመጉዳት የሚገፋፋኝን ነገር መቋቋም የሚያስችለኝ ምንም ተጨማሪ ነገር አይኖረኝምና” በማለት ይገልፀዋል ሐሪስ።እንግዲህ ከተወሳኝነት ሀልዮት አኳያ ሞራሊቲን እና ኃላፊነትን በሚመለከት አለን የምንለው የመወሰን አቅም ትርጉሙ ይኼው ነው። ሁላችንም ከቁጥጥራችን ውጭ በሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች እና ኩነቶች ግፊት ውስጥ ሆነን ነው የምናደርገውን ሁሉ የምናደርገው ማለት ነው። ስለዚህ ማንም ሰው ስለ ማንኛውም ነገር—ለጥሩ ባህሪ፣ ለመጥፎ ባህሪ ወይም በጣም ጫፍ የወጣ መጥፎ ባህሪ—በትክክል ተጠያቂ ሊሆን አይችልም።ለብዙዎች እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ የተወስኖታዊነት መከራከሪያዎች ወሳኝነት ያላቸው መከራከሪያዎች ይመስላሉ። ነፃ ፈቃድ የሚባል ነገር ፈፅሞ ሊኖር የማይችል ነገርም ይመስላል። ነፃ ፈቃድ አለን ልንል ከሆነ ነፃ ፈቃድን ከልላይ ከፍ ብለን ከተመለከትናቸው መከራከሪያዎች አንፃር የሐሳቦቻችን፣ የፍላጎቶቻችን፣ እና የመንስኤነት (causality) ምንጭ እሳቤዎች ጋር ያለ ተቃርኖ ማስተፃመር የሚጠበቅብን ነው የሚሆነው። ይሄን ለማሳካት ደግሞ የተወሳኝነት መከራከሪያዎችን በተገቢ መንገድ ውድቅ ማድረግ ይገባል።****በሚቀጥለው ክፍል በተወሳኝነት መከራከሪያዎች ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶችን እንመለከታለን። ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
16ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰የቅድመ ሽያጭ ማስታወቂያየመጽሔታችን (የባይራ) አምደኛ የሆነው ሲራክ ወንድሙ በአዲስ መጽሐፍ እየመጣ ነው። ከእሱ የሚጠበቀውን ዝግጅት ጨርሶ በቅድመ ሽያጭ መጽሐፉን ለማሳተም ጥረት ላይ ነው!ቅድሚያ ገዝተን መጽሕፉን እናሳትም!በነጻ ሲያስነብበን ለነበረው እኛ ደግሞ መጽሐፉን ገዝተን እናሳትምለት!ሶምሶማ - መጽሐፍ ደራሲ:- ሲራክ ወንድሙSintayehu wondinu 1000207035967-CBE2955596074711 dashen bank 234194078 Abyssinia 7000067525049 Neb int. bank0987605821 Tele birrደረሰኙን በዚህ የቴሌግራም አድራሻ ያስቀምጡልን @somsomabookየአንድ የመጽሐፍ ዋጋ 400
17እውነትና ስሜትዘውዴ አለልኝቅጽ ፪ ቁጥር ፮ |ጥቅምት ፳፻፲፰
18እውነትና ስሜት ፩( በዘውዴ አለልኝ) ከጨለማ ዳስ - በመስኮቷ አጮልቃደመናን - እንደ ጭንብል አጥልቃቢያይዋት ጨረቃን...ፍንትው ያለ - ሽብረቃ አሸብርቃ፤ከዋክብት ተቁለጨለጩፍዝ ብርሃን አፏጩ፤አሻግረው ቢያይዋት - ማለሉእፁብ ናት - ብርሃን ናት አሉ።የብርሃን አመልማሏፀሐይ እንደኾነች ፀዳሏ፣እሷም አልተናገረች - እነሱም ይኼን ዐያውቁምለውበቷ ዘመሩ - ብርሃኗን አሉት እጉም።ጨለማ ድንኳን ዘርግቶፍጥረት ለሌቱ አንቀላፍቶ...ጭር ያለች የቅጽበት ዳና - ስትኾን - እልፍ ኦና ሙዚቃዋ! የፍጥረት ውበት - ዋ! አርምሞዋ ጨረቃ።፩ ይብላኝ እንጅ ለፀሐይ - ለዛች ቁጡ ውበታምለዛች ባይተዋር ዓለምብቻዋን ነግታ - ብቻዋን ለምትጨልም።( ጨረቃማ ጨረቃ ናት - የዝምታ ዝማሬቆፈኗን የምትስቅ - አሰልፋ እልፍ ጃግሬ።) ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
19መሰንበት ነው ደጉፍሬው ማዕሩፍቅጽ ፪ ቁጥር ፮ |ጥቅምት ፳፻፲፰
20‘ራስን ማጥፋት መብት ወይስ ጥፋት?’ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሑፌ ላይ (‘ጥያቄዎቹ’ በተሰኘ መጽሐፍ ላይ የሚገኝ)፣ የዓለም የጤና ድርጅት በ2010 በኢትዮጵያ የሞት ምክንያት ከሆኑት መካከል ራስን የማጥፋት ድርጊት 1.2% የሚሽፈን ስለ መሆኑ፤ ይኽም ማለት ከ100,000 ኢትዮጵያን መካከል 11.38 የሚሆኑት ድርጊቱን እንደሚፈጸሙ፤ በዚህም ከዓለም ሃገራት 60ኛ ላይ እንደተቀመጠች የሚያትት የጥናት ውጤት ተጠቅሜ ነበር። እንዲሁም በ2012ዓ.ም በኢትዮጵያ በየአመቱ ከ8000 በላይ ኢትዮጵያዋን ራሳቸውን እንደሚያጠፉ የሚገልጹ መረጃዎች መኖራቸውንም ጠቅሼአለሁ። ከአመታት በኋላ ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጀበት ወቅት በቅርብ የተሰሩ ጥናቶች ስመለከት ደግሞ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ብቻ 9% የሚሆነው ሰው በሀገራችን ስለ ራስ ማጥፋት ማሰቡን (Suicidal Ideation)፤ ከዚህም ደግሞ 4% የሚሆነው ሙከራ ማድረጉን የሚገልጽ መረጃ አግኝቼአለሁ። በሌላ በኩል በዓለም አቀፉ የሕክምና መረጃ ቋት ላይ በቅርቡ የወጣ አንድ መጠነ-ሰፊ ጥናት በሀገራችን ከ10 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎችና ወጣቶች መካከል ራስን የማጥፋት ሙከራ መጠን 12.38% እንደደረሰ ያሳያል። ይህ መረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ ከስምንት ታዳጊዎችና ወጣቶች መካከል አንዱ (1/8) ራስን የማጥፋት ሙከራ ያጋጥመዋል እያለን ነው።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰መሰንበት ነው ደጉ ፍሬው ማዕሩፍ
21ስታቲስቲክስ ሁልጊዜም ቢሆን ትክክለኛውን አሊያም እርግጡን እውነታ ያሳያል ተብሎ ስለማይጠበቅ ቁጥሩ ከላይ ከተገለጸው እጅጉን የበለጠ እንደሚሆን መገመት አይከብድም። እኔ እንኳን በቅርብ ወራት በአካል በማውቃቸውም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር የሰማሁትን ስቆጥር አሃዙ አስደንግጦኛል። ታዲያ የእነዚህ ግለሰቦች ማንነት መለያየት ድርጊቱ ማኅበራዊ ደረጃ፣ የዕድሜም ሆነ የኢኮኖሚ ሁኔታ የማይመርጥ መሆኑን አረጋግጦልኛል። ከጎበዙ ተማሪ ንቁ እስከሚባለው አስተማሪ፣ ከደስተኛው ጎረቤት እስከ ዝምተኛው የሥራ ባልደረባ፣ ተጫዋች ከምንለው ጓደኛ ጠንካራ ብለን እስከምንቆጥረው ወዳጅ ድረስ ይህንን ድርጊት በራሳቸው ላይ ፈጽመዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸውን እያጡ በመሆኑ፣ ራስን ማጥፋት በራሱ አሁን ላይ ጉዳይ መሆን አለበት ወይንስ የለበትም ብሎ መሟገት ይቻላል። ሌላው ቢቀር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ጉዳይ አሳሳቢ እና የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ደረጃ ላይ መድረሱን መናገር እንደ ቅንጦት መቆጠር የለበትም።ብዙዎቻችን በሆነ የዘመን ክፋይ አሊያም የጊዜ ዑደት ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ ሰዎች የከፋን ሲመስላቸው፣ አቅጣጫችንን የሳትን መስሎ ሲሰማቸው “መሰንበት ነው ደጉ” ብለው መክረውናል። እኛም ለራሳችንም ቢሆን ሰው ያላየው ሀዘን፣ የዐይናችን መርጠብ የማይናገረው እንባ፣ ሳቃችን የደበቀው መሰበር ሲያጋጥመን እንዲሁ እንላለን “መሰንበት ነው ደጉ”። ሰዎች ራሳቸው ላይ ይህን ውሳኔ ለመወሰን መድረሻ አልባ ሚመስሉ ብዙ ማሰላሰሎች፣ ማያልፉ ተደርገው የሚቆጠሩ ጭንቀቶች፣ መውጫ እና መፈናፈኛ የሌላቸው ተደርገው የተመዘገቡ ተስፋ ማጣቶች፣ ሚጠገን የማይመስሉ የኑሮ ስብራቶች፣ አልቆም ያለ እንባ፣ ማይነጋ የሚመስል ጨለማ፣ እውን ሊሆን የማይችል ሚመስል ህልሞች ውስጥ አልፈው እንደሆነ እረዳለሁ። ነገር ግን ከላይ የጠቀስኳቸው አሃዞች ነገን በዛሬ ስሜቶቻቸው በመተርጎም እና ጊዜ የሚያመጣውን ለማየት ትዕግስት በማጣት ከመጪው ጋር ላለመተያየት ሰዎች በብዙ እየጨከኑ ነው። ግን ለምን? ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
221. ከችግር ይልቅ ሞት የቀለለ ሲመስልየዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነቱ ለብዙዎች ፈተና መሆኑ ብዙ አከራካሪ አይደለም። በዚህ ተነሳ በዜጎች ላይ የሚፈጥረው ስነልቦናዊ ጫና በተመለከተ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያድግትም። የዓለም ባንክ በየወቅቱ የሚያወጣው “Macro Poverty Outlook: Ethiopia” የተሰኝውን ሪፖርት ብትከታተሉና የኢትዮጵያ የድህነት መጠን በዓለም አቀፍ የድህነት ወለል ሲሰላ ወደ የት እያመራ እንደሆነ ብትመለከቱ ነገሩ ይበልጥ አሳሳቢ ደረጃ እንደሚደርስ እርግጥ ስለመሆኑ መጠራጠር የትም እንደማያደርስ ትገነዘባላቹ። ራስን ለማጥፋት ከሚገፋፉ ቀዳሚ ምክንያቶች ደግሞ አንዱ መጥፎ የኑሮ ሁኔታ ነው። አንዲት ወጣት ትምህርቷን ጨርሳ ረዘም ላለ ጊዜ ስራ ማግኝት ሳትችል ስትቀርና የቤተሰብ ጫና እንደሆነች ሲሰማት፤ አንድ ቤተሰብ አስተዳዳሪ የልጆቹን የቀን ጉርስ ማሟላት ሲሳነው፣ … ወዘተ። ስለ ነገ ተስፋ ማድረግ እና የኑሮ ፀሐያቸው ይወጣል ብሎ ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም ቢርቃቸው የሚደንቅ አይሆንም። ዜጎች በተለያየ ምክንያት ጉርሻ የሕልውና ጉዳይ ሆኖ “ነገ ምን እበላለሁ?” የሚለው ጥያቄ መልስ ሳያገኝ ቀርቶ፣ የምግቡ ጥያቄ የሕይወት ትርጉም ወደ መፈለግ ይቀየርና “ነገ ለምን እኖራለሁ?” የሚል ይሆናል። የዚህ ጥያቄ ምላሽ በቶሎ መፍተሔ ካልተገኝለት ራስን ማጥፋት እንደ “ብቸኛ መውጫ” ተደርጎ ጥቂት የማይበሉ ወገኖቻችንን ይቺን ዓለም በገዛ እጃቸው እንዲሰናበቷት ያደርጋል።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
232. የማኅበራዊ ሚዲያ አርትፌሻል ኑሮየማኅበራዊ ሚዲያ መልካም ያልሆነ አጠቃቀም ከከፍተኛ ድብርት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው አንድ ሺህ አንድ ጥናቶችን መዘርዘር ይቻላል።ወጣቶች ተመርጠው እና ኤዲት ተደርገው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጠፉ ጥቂት ፎቶዎች እና የደቂቃዎች ርዝማኔ ባለው ቪዲዮ በመመልከት፤ ይህንንም የራሳቸውን ሕይወት ከሌሎች በማወዳደር “እኔ አልረባም” የሚል የበታችነት ስሜት― በተለይ በወጣቶች ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል። ከዚህም በላይ የጥላቻ ንግግሮችና ትንኮሳዎች ሁኔታ በሀገራችን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በአንድ ቪዲዮ ወይም ፎቶ ምክንያት የሚሰነዘሩ የጥላቻ አስተያየቶች የብዙሃኑ ድምዳሜ እና የማይለወጥ ምልከታ ነው ብለው ሰዎች እንዲያስቡ ያደርጋል። የአንድ ሰው የ24 ሰው ኑሮ ከአራት ደቂቃ በማይበልጥ አርቴፊሻል የዲጂታል ዓለም ጋር በማወዳደር ሰዎች ሕይወታቸውን ይጠላሉ። ይህ ደግሞ መጨረሻው የመኖርን እርባናነት ትርጉም አዛብቶ ራስን ወደ ማጥፋት እንዲያመራ በማድረግ በኩል ተወዳዳሪ የለውም።3. የጦርነት ጥላ የጦርነት እና የግጭት ክፋቱ ኹነቱ በሚከናወነበት ጊዜ የሚፈጸሙ ድርጊቶች እና የዛ ውጤቶች ብቻ አይደሉም። ከዛ በኋላም በተረፉት ሰዎች ላይ አድርሶ የሚያልፈው የሥነ ልቦና ጫናም እጅግ አስከፊ የሚባል ነው። ምንም እንኳን ጦርነት ማኅበራዊ ትስስርን ስለሚፈጥር ራስን ማጥፋትን ይቀንሳል የሚለው መከራካሪያ ቢነሳም፣ በሀገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ይህንን የሚያሳይ አይደለም። ጥቂት መረጃዎችን ልስጣቹ፡-ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
24• በደሴ ከተማ ራስን የማጥፋት ባሕርይ 15.3% መድረሱ ሲረጋገጥ (Asrat et al., 2024)፤ በወልድያ ደግሞ በትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ በተደረገ ጥናት፡ 16.3% የራስን የማጥፋት ሃሳብ፣ 12.9% ደግሞ በተግባር ሙከራ ተደርጓል። (Tadesse et al., 2023)• በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ወገኖች መካከል 22.4% የራስን የማጥፋት ሃሳብ እንዳላቸው በPLOS ONE (Alemu et al., 2022) የታተመው ጥናት ያመለክታል።• በትግራይ ክልል በጾታዊ ጥቃት የተጎዱ ሴቶች መካከል ከ 60% - 70% የሚሆኑት ራስን የማጥፋት ሃሳብ እንዳላቸው ተመዝግቧል (Gebremedhin et al., 2023)። በተጨማሪም በክልሉ ባሉ መጠለያዎች የሚገኙ ወገኖች መካከል ከ 25% - 30% ራስን የማጥፋት ሃሳብ እንዳላቸው የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና EPHI (2022) በጋራ ያደረጉት ግምገማ ይጠቁማል።ዜጎች በሀገራቸው ተስፋ ሲቆርጡ፣ የሕግ የበላይነት ሲጠፋና የነገው ቀን እርግጠኝነት ሲጎድል፣ ራስን የማጥፋት መጠን ይጨምራል። ፖለቲካዊ አለመረጋጋቱ ዜጎችን “የመኖር ዋስትና” ስለሚነፍጋቸው፣ በገዛ ሀገራቸው ባዕድና ተስፋ ቢስ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ በዝምታ ለሚረግፉ ነፍሶች ዋነኛው ገፋፊ ምክንያት ነው።ከላይ የጠቀቃስኳቸው እና ሌሎችም ምክንያቶች ተደምረው ራስን ማጥፋት በኢትዮጵያ ተስፋፍቷል። ታድያ ምን ይደረግ? ቅድሚያ እስቲ የአንድ ሀገር ተሞክሮ እንውሰድ―የቺሊን። ቺሊ ዜጎቿን ከዚህ ቀውስ ለመታደግ ያደረገችው ጥረት ትምህርት የሚወሰድበት ነው። በቺሊ የጤና ሚኒስትር የአእምሮ ጤና በተመለከተ የሚሰራ ክፍል ያለ ሲሆን ይኸው የስራ ክፍል ራስን የማጥፋት ድርጊት መከላከልን በተመለከተ በሀገር ደረጃ ላዘጋጀው እቅድ አምስት መሰረታዊ መርሆችን በማስቀመጥ የሚጀምር ነው። ይህን እቅድ ውጤታማ ለማድረግ የቺሊ መንግስት ስራውን እስከታችኛው ደረጃ የሚገኙና ከጤና ጉዳይ ጋር ተያይዥነት ያላቸውን ተግባራትን ለሚያከናውኑት አካላት ድረስ ያወረደው ሲሆን ስራውን ለመስራት የሚያስችሉ ፈርጆችንና ሂደቶችን በመለየት በእቅዱ ላይ በደረጃም ተቀምጧል። ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
25በዚህም ቀዳሚው ራስን የማጥፋት ድርጊት ለመፈጸም በሃሳብ ወይም በዝግጅት ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎችን የመለየት ሥራ እንዲሰራ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት፣ ድርጊቱን የሞከሩ እንዲሁም የፈጸሙ ግለሰቦችን በማጥናት ገፊ የሆኑ ምክንያቶችን መለየት፣ በመቀጠልምድርጊቱን ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ ከየአካባቢው ተጨባጭ ኹኔታ ጋር መቅረጽ፤ በመቀጠል የተሰበሰቡ መረጃዎችን በማቀናበር እቅዶችን ከተለያዩ አካላት በመቀናጀት ማዘጋጀትን የሚየካትት ነው።በሦስተኛ ደረጃ ጉዳዩን በተመለከተ ለጤና ባለሙያዎች አቅም የሚያጎለብቱ ስልጠናዎችን መስጠት፤ ባለሙያዎችም ድርጊቱን ለመከላከል እንዲያስችላቸው የሚያደርጉ ግብዓቶችን ማቅረብና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጉዳዩን በተመለከተ የትምህርት ሥርዓቱ አንድ አካል እንዲያደርጉት ማስቻልን የሚያካትት ነው። በአራተኛነት በትምህርት ተቋማት ያሉ ተማሪዎች በራስ መተማመንን የሚያጎልብቱ ተግባራትን እንዲተገብሩ እና የተለያዩ ክህሎት እንዲያዳብሩ በማበረታታት ችግሮችን የመፍታት አቅም እንዲኖራቸው እና ውሳኔ በሚወስኑበት ጊዜ መከተል ያላበቸውን ሂደቶች እንዲጠብቁ ማስቻል ነው። ራስን የማጥፋት ድርጊትን ማእከል አድርገው አገልግሎት የሚሰጡ የስልክ መስመሮች እና የዌብሳይት አድራሻዎችን ማዘጋጃት በአምስተኛነትየተቀመጠ ነው። በመጨረሻም የተቀመጠው የሚዲያ አካላት በማኅበረሰቡ አባላት ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ትልቅ በመሆኑ፣ በመከላከሉ ስራ ላይ ትልቅ ድርሻ ኖሯቸው እንዲቀንሳቀሱ ማድረግ የሚል ነው። ቺሊ ላሳበችሁ እቅድ ተፈጻሚነት ከላይ የተመለከትነውን ተግባራትን በማከናወን እንዲሁም ለመርሃ ግብሩ መሳካት ድርሻ ያላቸውን ባለድርሻ አካላትን በመለየትና በማሳተፍ መልካም የሚባል ውጤት አስመዝግባለች።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
26በሀገራችንም ይህ እንዲሆን እየተሰራ ያለው ስራ ካለ እሱን ማስቀጠል፤ ካልሆነም ከሌሎች ሃገራት ልምዶችን በመቅሰም እንቅስቀሴ ሊጀመር ይገባል። ለዚህም የመጀመሪያውና ዋነኛው መፍትሔ የአእምሮ ጤናን እንደ አንድ መደበኛ የጤና ዘርፍ መመልከት ነው።የፌደራል ጤና ሚኒስቴር የአእምሮ ጤና አገልግሎትን እስከ ታችኛው የጤና ጣቢያ ወይንም የጤና ኬላ ድረስ ማውረድ ይኖርበታል። ራስን የማጥፋት ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ሳይገለሉና ሳይፈሩ የሥነ-ልቦና ድጋፍ የሚያገኙበት ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል። በሌላ በኩል ትምህርት ቤቶች በሰፊው ይህን ጉዳይ ትኩረት አድርገው መስራት አለባቸው። ውጤት ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ የተማሪዎችን ሥነ-ልቦናዊ ጽናት የሚያጎለብቱ የምክር አገልግሎቶችን ማጠናከርም አለባቸው። ከማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር ተያይዞም የጥላቻ ንግግሮችንና ትንኮሳዎችን መከላከል የሚቻልበት የሕግና የቴክኖሎጂ ሥርዓት ሊጠናከር ይገባል። በተጨማሪም ሚዲያዎች ራስን የማጥፋት ዜናን በሚዘገቡበት ወቅት ድርጊቱን ሌሎች እንዲለማመዱት የሚያደርግ አቀራረብ እንዳይከተሉ፣ ይልቁንም ሰዎች ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ የሚያስችሉ መንገዶችን የሚጠቁሙ ዘገባዎች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል። በተጨማሪም ሃይማኖታዊ ተቋማት ራስን ማጥፋትን እንደ “ኃጢአት” ብቻ ፈርጆ ከማግለል ይልቅ፣ በጭንቀት ውስጥ ያሉትን በመደገፍና በማዳመጥ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል። በሌላ በኩል ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠርና የኑሮ ውድነቱን ማቃለል፣ የፖለቲካ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የአእምሮ ጤና ጥያቄም ጭምር በመሆኑ በዚህ ላይ ስራዎች መሰራት አለባቸው። ዜጎች በሀገራቸውና በነገው ቀናቸው ላይ ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን መፍጠር፣ ዜጎች ራስን የማጥፋት ድረጊትን በራሳቸው ላይ እንዳይፈጸሙ ለማድረግ ትልቅ ድርሻ አለው። በየትኛውም ጥሩ ባልሆነ የሕይወት ሂደት ውስጥ ብንገኝ፣ በኑሮ መመላለሳችን ውስጥ ነገን የማያስናፍቅ ስቃይ ወዲህ ወዲያ ቢያንገላታን፣ ከሰፈር እስከ ሃገር ያለው ሁኔታ ተስፋ የሚለውን ቃል ከመዝገብ ቃላት ውስጥ መጥፋት አለበት የሚል ድምዳሜ ቢያሰጠን፣ መልካም ተዘርቶ ሰናዩ የሚታጨድበት ዘመን ላይመጣ ያለፈ ቢመሰልንም ውሉ አንዳች ምንኖርበት ትርጉም የሚሰጥ ነገር ብንፈልግ አይጠፋምና እሱን መሰረት አድርገን፣ የዛሬን መከራ ሳያሳልፈን እንሳልፈው። ደግሞም መኖሬ ትርጉም እንዲኖረው የሚያስችል ምንም የለም ምትሉም ከሆነ ሕይወት የቱንም ያህል ትርጉም አልባ ብትመስልም፣ “እኖራለሁ!” ብሎ መጋፈጥ ትልቁ አመጽ ነውና በመኖር አምፁ!ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
27በመጨረሻም ጽሑፌን የማጠቃለለው ራስን የማጥፋት ድርጊትን በተመለከተ ቁብ ሰጥቶ በጥበብ ድርጊቱን የተቃወመው ኤልያስ መልካ ያዘጋጀውና በዘሪቱ ከበደ፣ በአብነት አጎናፈር እና በጆኒ ራጋ የተቀነቀነው “መኖርህን ሰዎች ይሻሉ” ከሚለው ስንኝ ጥቂት ስንኝ በማስቀመጥ ነው። “ኑር ባታምንም ላንተ ባይመስልምለከንቱ አልተፈጠርክምየዛሬ ሕይወትህ ባይደምቅምነገም ካንተ ውጪ አይደምቅምድፈር ክረም፣ ኑር በሂወት ለሌሎች አቆያትፈሪ ነው የሰው ያልሞገተ ሳይገሉት ቀድሞ የሚሞተው።”………በቸር ቆዩኝ!ማጣቀሻዎች• Asrat, B., et al. (2024). Suicidal behavior in war-affected Dessie. Scientific Reports.• Tadesse, M., et al. (2023). Suicide ideation/attempt in Woldia students. BMC Psychiatry.• Alemu, W., et al. (2022). Suicidal ideation among IDPs in NW Ethiopia. PLOS ONE.• Gebremedhin, H., et al. (2023). Mental health of SV survivors in Tigray. Conflict and Health.• WHO/EPHI (2022). Psychosocial needs assessment in Tigray. Addis Ababa.• WHO (2018). Global Health Estimates: Suicide mortality (Ethiopia). Geneva.• Bifftu, B., et al. (2021). Suicide prevalence in Ethiopia: Meta-analysis. Int J Ment Health Syst.• Ferede, Y., et al. (2025). Suicide among youth in Ethiopia: Meta-analysis. BMC Psychiatry (PMID: 39979820).ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
28ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰እፉዬ!አዲስ መጽሐፍ - በነቢል አዱኛ የመጽሔታችን (የባይራ) አምደኛ የሆነው ነቢል አዱኛ በመጽሐፍ መልክ መጥቷል!እፉዬ ሲል የሰየማትን የበኩር መጽሐፉን እየገዛችሁ ታነብቡ ዘንድ እንጋብዛለን!መጽሐፏንኤዞፕ መጻሕፍት መደብርAbdu Book Delivery Seblework Books Delivery ጋ ማግኘት ትችላላችሁ።
29የሞት መልስ ቅኝቶች!ውብአረገ አድምጥቅጽ ፪ ቁጥር ፮ |ጥቅምት ፳፻፲፰
30መንደርደሪያ…ሞት በአጀባው የታደለ ነው ያስብላል። በዘመናት የተነሱ ከያንያንና ጸሐፍት ስለ ሞት እልፍ ብለዋል። አንዳንዶቹ ሞት የማይቀለበስ ናዳ መሆኑ ህይወታቸውን ውል አልባ አድርጎባቸው እየታመሙ ጽፈዋል።አንዳንዶቹ በሩቅ እያዩ እንዳልናቁት፤ ፊት ለፊት ሲያገኙት ደግሞ መሸሸጊያ ሲቸግራቸው ተመልክተናል።ከሞቱ በፊት ስለ ሞትና መለኮት፣ ብሎም ስለ ህይወት ውዳሴና ስለ ሞትም ህያውነት በብዙ ከጻፉ ሰዎች ውስጥ አንደኛው ታላቁ የህንድ ባለቅኔ ራቢንድራናት ታጉር ነው። ታጉር ደራሲ፣ ገጣሚ፣ የሙዚቃ አዘጋጅና ጸሐፌ ተውኔት ነው። የ1913 እ.አ.አ የስነ ጽሑፍ ኖቤል ሽልማት አሸናፊ ነው።ታጉር ያረፈው እ.አ.አ በነሐሴ 07፣ 1941 ዓ.ም ነው። የመጨረሻ ግጥሙን የጻፈው ከመሞቱ ከሰባት ቀን በፊት እ.አ.አ ሀምሌ 31፣ 1941 ዓ.ም ነው።ታሞ አልጋ ላይ ሆኖ ሞቱን እየጠበቀ የጻፋቸው ግጥሞቹ ታጉር ካረፈ በኋላ Shesh Lekha በሚል ርዕስ ታትመዋል። ወደ 15 የሚሆኑ ግጥሞች ናቸው። ምንም ርዕስ አልተሰጣቸውም። ግጥሞቹ እንደ ሌሎቹ የታጉር ስራዎች ውበትና ቋንቋ ላይ አይምነሸነሹም። በችኮላና ፊት ለፊት እየተወረወሩ በስሜታቸው ግን የሚናደፉ ግጥሞች ናቸው።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰የሞት መልስ ቅኝቶች! በውብአረገ አድምጥ
31በእነዚህ ግጥሞቹ ውስጥ ህይወት፣ ሞትና መለኮት ደጋግመው ተነስተዋል። በተለይ እያንዣበበት ካለው ሞት ጋር ፊት ለፊት መጋፈጡ ቁጡ ያደረገው ይመስላል። ከሞት በኋላ ያለውን ዘላለማዊ ህይወት መጎናጸፍ በሚቃጣው ድምጸት ይቀኛል።በአንደኛው ግጥሙ እንዲህ ይላልMay mortal bonds decayMay the great universe embrace meAnd in my heart know without fearThe great unknown.1 ይሄን ግጥም በደምሳሳው እንዲህ መተርጎም ይቻላል።(ምናልባትያስተሳሰሩን ሙት ሰንሰለቶች ይበጠሳሉያቅፈኝ ይሆናልይህ ሰፊ ህዋ ጽንፈ ዓለም ሁሉያለ አንዳች ፍርሃት ያላንድ ዋሾ ቃልታላቁን ምስጢር ይህ ልቤ ያውቃል።)በዚህ ግጥሙ ታጉር ስለ አይመረመሬውና አይታወቄው ታላቅ የሞት ዓለም በእርግጠኝነት አውቃለሁ እያለን ነው። ሞት ባይመረመረም ለታጉር ነፍስ ግን ቅርብ ነውና።እንዲሁም በሌላ ግጥሙDeath like Rahu Casts shadows onlyBut cannot sap life’s divine ambrosia:Entrapped by this material worldThis I know for sure ይሄንና በመሳሰሉት ግጥሞች ስለሞት፣ ስለማይታወቀው ዘለዓለማዊ እውነት ይቃትት ነበር።1. Rabindranath Tagore Omnibus II page 403ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
32Dr Sultana Jahan ታጉርና ሩሚ ሞት ላይ ያላቸውን አተያይ ባተተበት ጽሑፉ Radice (1987) እና Bhattacharya (2006) የሚባሉ ደራሲዎችን እማኝ አድርጎ እንዲህ ይለናል።“Tagore’s approach to death in Shesh Lekha is deeply meditative, tender, and accepting, rooted in Hindu Vedantic thought, particularly the Upanishadic concept of the eternal soul (Atman) and its union with Brahman (the Supreme Reality). Tagore perceives death not as annihilation but as a return to cosmic unity, a continuation rather than a cessation of existence. His philosophy resonates with the Hindu belief in the cyclic nature of life, death, and rebirth (samsara).” 3ታጉር ሞትን እንደ መጥፋት አይመለከተውም። በጥንታዊ የቬዳ አስተሳሰብና በአፕናሻድ ፈትለ ነገር የመንፈስን ዘለዓለማዊነትና ከታላቁ እውነት ጋር ያላትን ስሙር ህብረት ይፈክራል። ለታጉር ሞት መበስበስ አይደለም። ሞት ከጽንፈ ዓለሙ ጋር ህብረትን ፈጥሮ እያረገዱ የመቀጠል እንጂ አፈርና ትቢያ ሆኖ መቅረት አይደለም።ስለዚህም ሞቱ ላይ ይመሰጥበታል። ያላየውን እውነት በነቃ መንፈስ ሊቀበለው ይታትራል። ግጥሞቹን በፍጥነት ከህሊናው ዲብ እያስፈተለከ በቀጥተኛ ድምጸት ያወርዳቸዋል። የቸኮለ የመንፈስ መንገደኛ በቃል ልሳኑ ይወረወራቸው የመጨረሻ ትንፋሾች ናቸው። 3. Beyond the Veil: A Comparative Journey through Tagore’s Shesh Lekha and some of Rumi’s Verses. By Dr Sultana Jahan, Department of English Language and Literature International Islamic University Chittagong. International Journal of Islamic Thoughts (IJITs), 12(1&2), 12-23; 2023ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
33ጊዜን መሸከም“ጊዜ በረርክ በረርክግና ምን አተረፍክግና ምን አጎደልክ”እንዲል ታላቁ ደበበ ሰይፉ የዘውዴ አለልኝ ግጥሞችም በጊዜ ሚዛን ውስጥ እየተሰፈሩ ለመትመም መሆንን መሸከም የገደዳቸው ናቸው።የዘውዴን ግጥሞች ለመረዳት ራሱ ገጣሚው እንደ መግቢያ፣ እንደ ቀዳሚ ቃል ብሎም በየመጽሐፉ መካከል እንደ መክፈያ ያስቀመጣቸው ማብራሪያዎች ከበቂ በላይ ናቸው። እንዲያውም ሌላ ለማሰብም እድል አይሰጡም ማለት ይቻላል። ራሱ የራሱን ስራ ሂሶታል ቢባል ያስሄዳል።ለአብነት እንይ ቢባል እንኳን ግጥሞቹን በጥሪአችው አማካኝነት በቀለማትና በሙዚቃ መሳሪያዎች ከፋፍሏቸዋል። ጥቁር፣ ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ነጭ ሲል ሰይሟቸዋል። እንዲሁም በድምጸታቸው አማካኝነት በዋሽንት፣ በክራር እንዲሁም በነጋሪት መስሏቸዋል። ምን ማለት እንደሆነና ትርጓሜአቸውንም አስቀምጧል። የግጥሞቹን መንፈስ ብሎም ገፊ ምክንያት በአንዳንድ ምልክቶች አማካኝነት ግን የራሳችንን ብያኔ መስጠት እንችላለን። ከቀዳሚ ቃሉ ጀምሮ በግጥሞቹ ቀለም ሳይቀር የሚስተዋል አንዳች ደብዛዛ ብርሃን አለና እሱን እንከተል።“ምስጋና አይደለም የደበዘዘ መተጣጣት ነው” ሲል በቀዳሚ ቃሉ ባስቀመጠው ጽሑፍ ላይ ሆነን የግጥሞችን መንፈስ ለመገርመም ብንሞክር ቃል ገደፋችሁ አንባልም።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
34በቀዳሚ ቃሉ “ራሴን ከማጥፋት ውጭ ሌላ ማምለጫ እንደሌለኝ ተረድቻለሁ። ሆኖም ሞቴ ከሕይወት የተሻለ ላይሆን ይችላል።” ይለናልበህይወት የደከመ፣ በመሆንና ጊዜን በመሸከም የተሰላቸ መንፈሱ ሞትን ሁሉ እንዳስመኘው ይነግረናል። ደጋግሞ ሞትን ሊጎነጭ ሞክሮ በፍርሃቱ እንደተወው እንዲህ ይናዘዝልናል።“ወደ የትኛው አድማስ ብሰደድ ሕመሜን እሸሸው ይሆን? መከራዬን እንዴት ላመልጠው እችላለሁ? እኔ እንጃ! ምናልባት ደፋር ከሆንሁ ሞቴ ከነዚህ ሁሉ መከራዎች ሊሸሽገኝ የሚችል ዓለሙ የሚሸሸው ስርቻ ይመስለኛል። ሆኖም ወደ ሞት የተጓዝሁባቸው መንገዶች ሁሉ ከታዛው ሲደርሱ በፍርሃት ክብ መንገድ ዳግም ከህይወት ደጅ ያደርሱኛል።’’ ለዚህም ነው ርዕሱን የሞት መልስ ቅኝቶች ለማለት የወደድነው። ፍርሃቱ ባይሸብበው ሞቶ ነበርና። ሞትን ሞክሮ ወይም በመሞት ላይ ወስኖ የተመለሰን እንዴት አልሞተም ይሉታል? አንድ ሰው ቁርጥ ሃልዮ ከደረሰ ያሰበውን ድርጊት አድርጎታልና። አንድም አንድ ደራሲ ስራውን ካቀረበ በኋላ ደራሲው ሞቷል ይባላልና። ጊዜን መሸከም ከምንምነት ተነስቶ በመሆን አልፎ ወደ ምንምነት የመንደርደርን የህይወት አዙሪት የፈከረበት ስራ ነው። ምንምነቱ ባለው የተፈጥሮ የመሆን ሀቅም ወደ ህይወት አደገ። ያ ህይወትም በመውጣትና መውረድ እሽኮለሌ ተንፏቅቆ ወደ ምንምነት ይደርሳል።እስኪ ይሄን የምንምነት መንገድ ሰፋ አድርገን እንየው።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
351.በመጀመሪያ ምንም ነበርየህይወትን ጽንስ ለመረዳት የማይቃትት የለም። ህይወት እንዴት ተጀመረ? ይሄ ሁሉ መሆን ከየት ተነሳ? አስገኝው ማን ነው? ለመሆኑ ከመፈጠራችን በፊት ምን ነበር? ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም ይሄን ጥያቄውን “ለምን አልፈጠርህም እስክትፈጥር ድረስ?” ሲል ይጠይቃል።ከሳይንስ እስከ ሃይማኖት ብሎም እስከ ሚት ድረስ ይሄን ጥያቄ ለመመለስ ያልሞከረ የለም። ብዙዎች ግን ከመሆን በፊት ምንምነት ነበር ይላሉ። ምንምነት ባዶነት ወይም ኦናነት ማለት አይደለም። ምንምነት ማለት መሆንን የመሆን ጉልበት የታጠቀ የፍጥረት ሁሉ የመጀመሪያ ወይም የጋራ መልክ ነው ይላሉ።መጽሐፍ ቅዱስ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ ቁጥር 2 ላይ “ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ።” በማለት አንዳችም አልነበረም በሚለው ቃል ምንምነትን ሊነግረን ይሞክራል።ጊዜን መሸከምም ተመሳሳይ መልክ አላት። የህይወትን ውል ለመፍታት ከጽንፈ ዓለሙ ጥንስስ ለመነሳትና ሀዘንና መከራ ብሎም ሞት የህይወት አይነተኛ መልኮች ናቸው የሚል መሰረት ለማስያዝ ይቃትታል።ምንምነትን በኦናነት ብሎም በጨለማነት ይመነዝረዋል። ያ ምንምነት መልኩ ጥቁርና በፈጣሪውም ልቦና ውስጥ ህይወት ይሁን የማለት ቁዘማ ነበር ይለናል።“ያልተጀመረች ህይወት በኦናው ውሰጥ ርቃኗን ከነፋሰ ጋር ትደንስ ነበር።’’ ይለናል። “በኦናው ውስጥ ይተክዝ የነበረ ሃሳብ ትካዜውም ቃል ሆነ። ቃልም ትንሳኤ ይሁን አለ። ፈቃዱም ሆነ።’’ በማለት የህይወትን አጀማመር ከራሱ ዘፍጥረት ይተርክልናል።በኦና ውስጥ የተደበቀ የትካዜ ቃል የፈጠረውን ህይወት እንዲህ ይኖረዋል። በዚህ የህይወት መነሻነት ላይ ቆመን ዘመንን እንታዘባለን። እየኖርነው ያለነውን ህይወት ከጥንስሱ አንዲህ ያስጀምረናል።የኦናነት ትካዜ የፈጠረው ህይወት እንደምን ያለ ነው? በጊዜን መሸከም ገጾች ውስጥ አብረን እንመልከት።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
362.ምንሙ ህይወት ሆነሁሉም ምንም ነበር ብለን መንገዳችንን ጀመርን። ያ ምንምነት ግን በትካዜ ቃልነት ህልው ሆነ። በዚያ ህልውነት ውስጥ የፍጡራን ሁሉ መተራመስ በገሃድ ይታያል። በዚህ መተራመስ ውስጥ ያለ ገጣሚ ትርምሱን በቃላት ይቀርጸዋል።በግጥሙ ተመሳሳይ ቁጡና ጸሊም ስንኞቹን ከቀለማትና ከዜማ ጋር እያዋሃደ የህይወትን መልክ መንቀስ ይጀምራል። በዚህ የህይወት ነቀሳው ውስጥ በመጀመሪያ መለኮትን በመሞገት ይጀምራል። ከዚያም ልጅነቱን፣ ቀጥሎም ህይወት ይሉት መትበስበስን!አሐዱ- መለኮትስነ ፍጥረት የመለኮትን ታላቅነት ሊመሰክር ሲሻ ሁሉንም ውብ አድርጎ ሰራው ይለናል። ዘውዴ ግን ይሄን አይቀበልም። የሆነ የተሳተ መንገድ እንዳለ በማመላከት መለኮትን ሙግት ይጀምረዋል። “የባካኙ ምልጃ” በሚለው ግጥሙ የእኩይንና የሰናይን አብሮነት ብሎም ትብስብስ እየታዘበ መታገስ ይቸግረዋል። ካለህበት ሆነህ ስማኝ ይለዋል።“አምላክ ወደየት ነህና ጅምርህ ይቋጭ ይፈጸም የሰው ልጅአውሬና መለኮትአያድሩም ባንድ ልብ አይኖሩም በአንድ ደጅ።”እያለ የጀመረውን ይቋጭ ዘንድ ሽቅብ ለመለኮት ያመላክታል። ጅምርህን ጨርስ እንጂ፣ ምንድነው እንደ ድሃ ቤት አትበስብሶ መሄድ ይለዋል። በገጣሚው ምናብ ይህቺ ዓለም ያላለቀች ውግርግር ቤት ናት። የተሳተ፣ የተረሳ፣ የተተወ ነገር አለ እያለን ነው።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
37“ይግባኝ ለፈጣሪ” በሚለው የግርጌ ግጥም ላይ ደግሞ ከበድ ያለ ጥያቄ ይዞ ይነሳል።“ከመፈጠር በላይ በደል ከየት አለ?የሰው ልጅ ነው በግፍበማያውቀው ዓለም የትም የተጣለ።”በማለት ህይወት ይሉትን እጣ በደል ነው፤ እኛም የትም ተጥለናል ይላል። አቤቱ የሆነብንን አስብ እንዳለው ዳዊት በመዝሙሩ የዘመናችን ዘውዴ መፈጠርን የመሰለ መከራ የለም ብሎ ፈጣሪውን ይጋፈጠዋል።ገጣሚው ፍጥረትንና ፈጣሪን በቃል ፍላጻ ጎሽሞ ዝም አይልም። እጁ ሲዝል፣ ጥጋት ሲፈልግ፣ ነፍሱ አንዳች ማረፊያ ስትሻ ወደ መለኮት ማማተሯ አልቀረም። ጆሮ እየፈለገ ሰሚ ሲቸግረው፣ ሰላም እየናፈቀው ሁከት ሲያደናብረው፣ ለጥያቄው መልስ የሚሰጠው ስጋና ደም የለበሰ ሳይሆን አንዳች ሃይል እንደሆነ ሲሰማው እጁን ሽቅብ ይዘረጋል። ያኔ ግን ሰሚ የለም። አለሁልህ የሚለው መከታ ዳናው ይጠፋል። ከአባትም በላይ፣ ከነገስታትም በላይ፣ ከቅዱሳንም በላይ የሆነውን አምላክ ተስፋ አድርጎ አቤት ቢል ሰሚ ያጣል። ያኔ በድርብቡም ቢሆን ተስፋ ያደረገውን አምላክ አለቅህም ሲለው እናገኛለን።“ከርታታ ጥሞና” ሲል በሰየመው ግጥሙ እንዲህ ሲል ምሬቱን ሽቅብ ይበትናል።“አንጃበበ በላዬ ዶፍ ያረገዘ ደመናእሸሸግበት ዋሻ የለም ዙሪያዬ ወናእንዲሸሽገኝ፣ ከዶፍ ከውሽንፍሩለጋ እጆቼ፣ ወደ አምላኬ ቢንጠራሩየለም ጌታ ከመንበሩ።”ሲል ህልውናውን ሳይቀር ይፈትነዋል። እውን ጥሪን ያልሰማ መለኮት፣ ጩኸትን ያልተመለከተ ፈጣሪ እንደሌለ ቢቆጠርስ? በዋይታ ውስጥ ለሚኖሩት ህይወት ፈጥኖ ደራሽ የምንለው መለኮት ህልውናስ ምን ድረስ ነው?ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
38ክልኤቱ-ልጅነትየዘውዴ ልጅነት ሲበዛ ጨፍጋጋ ነው። በተስፋ የተሞላ ነበር። በልጅነቱ የነበረው የተስፋ መዓት በወጣትነቱ ሳይቀር ጸይም ጥላ አጥልቶበታል። ይሄን ተስፋውን “አባቴ እኔ ልጄ” በሚለው ግጥሙ እንዲህ ይለዋል።“ያጓጓኝ ነበር መግለጥ የነገን ገጥወደ ተስፋ ነበር ልቤ የሚያንጋጥጥእፈራው ነበረ የናላዬን ትካትየተስፋዬን ጀምበር ብዬ እንዳይጋርዳት።”ይለናል።ሰንቆት የነበረው ተስፋ በወጣትነት መጅ ደቅቆ እንደወደቀም ሳይቀር ሹክ ይለናል። ለዚህም “ለልጅነታችን” በሚለው ግጥሙ ከህዳግ የተዘረጉ ቃላትን ማየት ይበቃል። “ልጅነቴማ ወፍ ነበርበህልም ሰማይ የሚበርበወጣትነቴ የመታከት ጠጠርክንፉ ባይሰበር።”ይላል። እንደ ገዴ ሲቀማጠል የነበረው ሁሉ አገርሽ ወፋዊ ልጅነቱ መታከት በሚሉት የማዎቅ ወይም የወጣትነት ጠጠር እንደተቀለጠመ የልቡን ያዋየናል።ይሄን ትልቅ ተስፋ በመሰነቅ ያለፈውን ልጅነቱን ዛሬ መልሶ ያገኘው ይመስል ወይኔ እያለ ያባብለዋል። ለጠፋ ልጅነቴ ለባከነ ህልሜበዘበት ለሸሸሁት ጋሜ ላንቀላፋሁት ውርዝው እድሜስንት ዓመት ልመንኩስ ስንት ሱባይ ልያዝየባከነ ህልሜ ዳግም ተስፋ እንዲያረግዝ?ብሎ ጠይቆእንጃሲል ራሱ ለጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ያጣል።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
39ታላቁ ሃያሲ ሃሮልድ ብሉም (Harold Bloom) አርትኦት በሰራው “Modern critical views Contemporary poets” በሚል መጽሐፍ ውስጥ አንድ ጽሑፍ አለ። ጸሐፊው ሪቻርድ ሀዋርድ (Richard Howard) ነው። ሀዋርድ ስለ ገጣሚ ጀምስ ራይት (James Wright) አጻጻፍና ስለ ግጥሞቹ ፈትለ ነገር “The body wakes to Burial” በሚል ርዕስ እንዲህ ሲል ይናገራል። “a dialect of dispossession and deprival, a vowel of longing, unique among his contemporaries for its final bleakness, singular in its ultimate solitude.”4 (ማጣትንና ችግርን ዘዬ ባደረጉ፣ የቁዘማን ልሳን በተሸከሙ፣ ብሎም ፍጹም ጸሊም መንፈስ በተላበሱ ግጥሞቹ ከዘመነኞቹ ሁሉ ልዩ ነበር።) ጀምስ ራይት ልጅነቱን በትልቁ የኢኮኖሚ ድቀት ወቅት ነው ያሳለፈው። አባቱ የመስታውት ፋብሪካ ሰራተኛ ነው። እናቱ ደግሞ የቆዳ ፋብሪካ ሰራተኛ። የልጅነት ህይወቱ ጸሊም ነበር። ህጻን ሆኖ በአባቱ ላይ ጥልቅ ቂም ነበረው። ምክንያቱም በዚያ የችግር ወቅት የራይት ቤተሰብ ሰለባ ነበርና። ልጅነቱን በእርዛት ያጣ ልጅ እንደምን ለወላጆቹ ፍቅር ሊኖረው ይችላል። ጠኔ ያጥመነመነው ቤትስ እንደምን የፍቅር መድረክ ይሆናል?ለዚህም ነው የራይት ግጥሞች ጥልቅ ሀዘንና ቁዘማ የሚታይባቸው ከዘመነኞቹ በተለየ የግጥሞቹ መልክ ጨፍጋጋ ነበር። እኛስ የራይትን ግጥሞች መንፈስ ይዘን የዘውዴን ልጅነቱን ለመፈተሽ ብንሞክር ማን ይከለክለናል? ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰4. Modern critical views Contemporary poets edited and with an introduction by Harold Bloom page 251.
40ሰለስቱ- ዘመንና ሕይወትበዘውዴ ግጥሞች ውስጥ ዘመንና ህይወት ጥቁር ለምድ ለብሰው በሰብዓለሙ ላይ የተዘበቡ የዛር ውላጆች ናቸው ያስብላል። የህይወት ወለፈንዴነት ውሉ ያሟልጨዋል። የዘመን ንቃቃት ያስጸይፈዋል።ህልውናውን ስግትር ይገጥማል። እጣው ያንገሸግሸዋል። የሚፈልገው አንዳች ስሙርና አምሳለ ዩቶፒያ ሀገር ይናፍቀዋል።ከሞት ወደ ሞት የሚባዝነው ህይወት ዋይለልስ ያስብለዋል። ሞት ለገጣሚው መጥፋት ነውና። ‘‘ከራስ ሽሽት’’ በሚል ግጥሙ“ነጋ ስንል መሸ፣ መሸ ስንል ነጋሕይወት መንገዷ ክብመድረስ መመለስ ነው፣ በሄዱበት መንገድ ትርጉምን ፍለጋ።”ሲል የህይወትንና የትርጉምን አዙሪት ይፈክራል። በዚሁ ግጥሙ የመጨረሻ ስንኞች ላይ‘‘አሜን አሜን ቀርቶ የእውነት ገበናዋ በእውነት ሲበረበርእንኳንስ ታሪኩ ራሱ ከንቱ ነው፣ የሰው ልጅ ሲፈከርዋጋው ዜሮ ብዜት ከአፈር ተሰርቶ አፈር።’’በማለት ይሄን ሁሉ መባዘን የዜሮ ብዜት ያደርገዋል። ከምንምነት የተነሳውን ህይወት ሀሰሳውን ሳይቀር ዜሮ ያደርገዋል።ሲል በሰየመው ግጥሙ ላይም ተመሳሳይ ወለፈንዲነት ይፈከራል። አኗኗራችን እንደ አንዲት አበባ አብቦ መክሰም ነው። አብቦ መክሰሙ የወል መገለጫችን ቢሆንም አሟሟታችን ግን እልፍ ነው ይለናል። ‘‘አንድ ፍሬ እልፍ አበባመልክ ብዙ እልፍ አሟሟትትርጉም አትሰጥም ሕይወት’’ህይወትን ለማቃናት ፍጡር በየፊናው ይማስናል። ግን ጠብ ያለለት የለም። የነፍሱ መሻት የሞላለት አንድም አልታየም። ሁሉም በፍለጋና በተስፋ ይማስናል። ይሄን ተሃዝቦቱንም በ ‘‘መልክዓ ህይወት’’ ይሄን ይለናል።‘‘ብታንጓልለን ሰርክ፣ሕይወት በሰፌዷተበጥሮ አይጠራም፣ ኑረት እንክርዳዷ።’’ይለናል።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
41“ኮብላይ ተስፋ” በሚለው የግርጌ ግጥሙ ውስጥም ይሄን ህይወትና ዘለዓለማዊነት መሞገቱን ይቀጥላል።“ሕይወት የሚያደርሰው ከሆነ ከሞት ደጅምንድን ነው ዓለሙ፣ ምንድን ነው የሰው ልጅ?”ሲል ይጠይቃል። መልስ ስለማግኘቱ ባናውቅም ጥያቄው ግን በህይወት ላይ የተሰነዘረ አንዳች ሙግት ነው።ገጣሚውን የራሱ የግል ህይወት ብቻ አይደለም የሚያንገበግበው። እንደ እርግማን የተጫነብን የእርስ በእርስ መነካከስ መርግም ያስጨንቀዋል እንጂ። እንደ ሸማ የለበስነው የጭካኔ መልካችን ያስፈራዋል። እንደ ትውልድ የተሰበርነው መሰበር፣ እንደ ሀገር የከሰርነው መክሰር ያንገበግበዋል። ከቀዳሚ ቃሉ እንደነገረን በሄዱሁባቸው የሀገሬ ክፍሎች ሁሉ ከሰውነቴ ይልቅ በእንባዬ ያለፍኋቸው ኬላዎች እልፍ ናቸው ብሎናልና። እንደ አርማ የሰቀልነው የጸብ ሀውልታችን መቆሙ ልቡን አስነብቶታልና።ለዚህም ምስክር የሚሆኑ የቅኝት ቆሎዎች ከጊዜን መሸከም ሰፌድ ውስጥ ጥቂት ለቅምሻ እንቆንጥር።‘‘እኔም ጉዳይ አለኝ’’ ሲል አቤት ባለው ድምጸቱየሀገር ጣይ ጠልቃብን ዘርግተን ጥቁር ጨርቅስንት ዓመት እናልቅስ፣ ያለ ቤት ያለ ስንቅ? ሲል ይጠይቃል። እንባችንን ለሚታዘብ፣ ሲቃችንን ለሚመለከት ይሄ ጥሪ የአንድ ግለሰብ ብቻ አይደለም።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
42እንደ መርገም ጨርቅ የለበስነው የጦርነት አውሊያ ለገጣሚ ተጨማሪ አንጎሉን የሚያናጋ ክስተት ነው። የአባትንና የልጅን የሞት መፈላለግ “ሀገር ያጣ አዝማሪ” በሚለው ግጥሙ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል።“ቁንጮውን ሳይላጭ ማርዳውን ሳይፈታልጅ ያባቱን ጥላ ያልማል ለቃታ።”እያለ የጦርነት አዙሪታችንን ይግተናል።“ሳንፈልግ መፈለግ (እየፈለጉ አለመፈለግ)” ከሚለው ግጥሙ ህዳግ ላይ ሌላ ቅምሻ ጣል አርገን እንለፍ።“የሳባ መንገድ አደረሰን ከዛሬጥበብን ፍለጋ ባከንሁ የሀገሬን ጥበብ ቀብሬትውልድ በወረፋ ለጥበብ ሲሰደድዕውቀቱ አገር ማፍረስ ሲመለስ የእናት ባድይሄው ነው የሳባ መንገድ።”3. ይህ ሁሉ ምንድን ነው? ኑዛዜእንዲህ ነፍስን ሰቅዘው የሚይዙ፣ ለሙሾ የሚያስደገድጉ ግጥሞች ስለምን በአንድ መድብል ታጭቀው ተገኙ ብሎ መጠየቅ የሚያስመኝ ይመስለኛል። ከዘመኑ ነው የሚል መልስ ሰጥቶ ማለፍ ይቻላል። ከዘመኑ ብቻ ሳይሆን ከገጣሚው የግል ቅምምስ ነው ማለትም ይቻላል።አይ ኑዛዜ ነው! ማለትም ይቻላል!የሰው ልጅ በቦታና በጊዜ ቢራራቅም አንዳንዴ በስሜትና በምናብ መወራረስ ይኖራል።ከዛሬ 60 እና ሰባ ዓመት በፊት በአሜሪካ አንድ የግጥም አብዮት ነበር። ሃያሲዎቹ “confessional poetry” (ኑዛዜአዊ ግጥሞች) በማለት ይጠሩታል። ብዙዎቹ ገጣሚዎች በስያሜው ባይስማሙም እንቅስቃሴው ግን ነበር። ዛሬ ድረስ በግጥም ስራቸው የሚወሱና በዘመናቸውም ታላላቅ የስነ ግጥም ሽልማትን የወሰዱ ብዙ ገጣሚዎች ከዚህ የኑዛዜአዊ ግጥም አጻጻፍ ውስጥ ይመደባሉ።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
43የኑዛዜአዊ ግጥም ዋና መገለጫው ጥልቅ የሆነ የገጣሚውን የግል ቅምምስ (experiences) የሚያንጸባርቅ መሆኑ ነው። የገጣሚውን የህይወት ገጠመኝ፣ የኑሮ ከፍና ዝቅ፣ የቤተሰቡን ጉዳይ፣ የትውልዱን መከራና የህሊናን ጩኸት ወይም የአእምሮን ህመም ሳይቀር በግልጽ የሚያሳይ ነው።በ1959 እ.አ.አ የታተመው Robert Lowell የግጥም መጽሐፍ Life Studies ለኑዛዜአዊ ግጥም መነሻ ነው ይባላል።ከእሱ በኋላ ብዙ ታላላቅ ገጣሚዎች ከዚህ ምድብ ውስጥ ይካተታሉ። ለአብነትም እነ ሲልቪያ ፕላት (Sylvia Plath) ፣ አነ ሴክስተን (Anne Sexton) ፣ ስኖድግራስ (W. D. Snodgrass) እንዲሁም ሮበርት ሎዌል (Robert Lowell) ይጠቀሳሉ።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
44እነዚህ ገጣሚዎች የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገር አለ። ሁሎችም በሚባል ደረጃ በድብርትና በምስቅልቅል ህይወት የኖሩ ናቸው። ሁለቱ ራሳቸውን አጥፍተዋል።ሁሉም የተወለዱት በሚቀራረብ ዘመን ነው። ትልቁን የኢኮኖሚ መዳሸቅ በልጅነታቸው ተጋፍጠውታል።እናም በግጥማቸው ውስጥ የነፍሳቸውን ስብራት ይናዘዛሉ። በዚያው ዘመን የተነሳው የሂስ አብዮት (New Criticism) እነሱ ግጥም ላይ ለመተግበር አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ገጣሚውንና ግጥሙን ለያይቶ ማየት ያስፈልጋል ይላልና።የእነዚህ ሰዎች ግጥም ግን ከህይወታቸው እጅግ የተቆራኘ ነው። እንደ ምሳሌ የሲልቪያ ፕላትን “Daddy” የሚሰኝ ሽንጣም ግጥም ብናይ በሞተ አባቷ ላይ ያላትን ጥላቻና ቁም የምትገልጽበት ነው። ጀርመናዊውንና በ10 ዓመቷ በሞት ያጣችውን አባቷን እልህ በሚተናነቀው ድምጸት“Daddy, I have had to kill you.You died before I had time.”ጊዜ ሳይኖረኝ ሞትህ እንጂ አሁን ቢሆን እገድልህ ነበር! ትለዋለች። ሌሎችም መሰል ኑዛዜ ግጥሞች አሏቸው።ይሄን እያሰብን የዘውዴን ግጥሞች ስንታዘብ የራስ ወደራስ እሪታዎች ናቸው። እንደ አብነትም ከግጥሞቹ ጥቂት እንጥቀስ።“ሰቆቃዎ ዘውዴ” በሚለው ግጥሙ ይሄን ይለናል።“እናት የለው አባትአልተቆነጠጠ አልተማረ ምግባርበየትም አደገ እንደ መሻቱ እግዜር።”እያለ ንጡል አስተዳደጉን ይነግረናል። ዝቅ ይልናም።“በደካማ አካሌ ጊዜን ተሸክሜላልድን መባከኔ፣ ኧረ በምን አቅሜ?”በማለት ይጠይቃልቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
45እንዲሁም “የልጅነት ቀለም” በሚለው ግጥሙ የትናንቱን ድፍርስ ትዝታ ከዛሬ ምንምነት ላይ ቆሞ እንዲህ ይተክዛል።“ከትዝታ እልፍኜ በግብብ መስኮቴአሻግሬ አየኋት ያቻት ልጅነቴከቡናው ስር ተቀምጣ፣ ትዝታዬ ቀዘባዋአየኋት ልጅነቴን ጠውልጋለች አበባዋበለጋ ጀርባዋ እንቅልፋም ጊዜ አዝላአንገት ደፍታ አየኋት፣ ያቺን እንቡጥ አዝላምን አሸከማት እድሜጠውልጋለች የልጅነት ቀለሜ።”እያለ አንጀታችንን በዋይታ ማዕበል ይመታዋል። በልጅነቱ አሻግረን ጠውልጎ መጥፋትን እየታዘብን እብረነው እንድንተክዝ ያደርገናል።በሌሎች ግጥሞቹም ላይ እንዲሁ ከልጅነቱ በተሰደደ መንፈሱ ከአምባ ላይ አንገቱን ደፍቶ የትውልድ እንባ ሲያወርድ እናየዋለን።እዚህ ጋር አንድ ነገር ማንሳት ይቻላል። ታላቁ ገጣሚ፣ ሃያሲ እንዲሁም ጸሐፊ ተውኔት ቲ ኤስ ኢሌት (T.S. Eliot) በ1919 እ.አ.አ “Tradition and the Individual Talent” በሚል ርዕስ በጻፈው መጣጥፉ ሁለት ነገሮችን ያነሳል። የጽሑፍ ባህል (tradition) እና Objectivity። በዋናነት እዚህ ላይ ማንሳት የፈለግሁት Objectivity የሚለውን ነው። እንደ ኢሌት አባባል ከሆነ አንድ ግጥም ከገጣሚ ማንነት ጨርሶ በተለየ መልኩ መታየት አለበት ይለናል። የገጣሚ የግል ህይወት ብሎም አኗኗር ከስራው ጋር መያያዝ የለበትም እንደማለት ነው።ነገር ግን እንደ ጊዜን መሸከም ገጣሚው የህይወት ቅምሱን እየነገረን በየመሃሉም ኑዛዜ የመሰሉ መቃተቶችን እያስነበበን የግል ህይወቱን ችላ ልንለው አይገባም እላለሁ።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
464. በጨረሻም ሁሉም ምንም ይሆናል!ከምንምነት የተነሳ ህይወት ወደ መሆን ያድጋል። በትካዜ ወደ መሆን የተወረወረ ህይወት ከሰከም ሰከም በኋላ ወደ ዘለዓለም ዝምታ ይምዘገዘጋል። ከምንም ወደ ምንም የፍጡራን ሁሉ ኡደት ነው።ገጣሚው ጊዘ ከማይሰፈርበት፣ ቦታ ከማይመተርበት ምንምነት ጊዜን ተሸክሞ ብቅ አለ። በጊዜ ብርቱ ክንድ ጎብጦ በጸሊም ምድር ላይ ይንከራተታል። ከዚያም ጊዜን ተሻግሮ ወደ ህያው ጨለማ፣ ወደ አይመረመሬው መሻገርን “ጊዜን መሻገር” በሚለው ግጥሙ እንዲህ ሲል ያልማል።“ራሴ ላይ ልጥፋ ራሴ ላይ ልፍሰስያለ መንገድ ምራኝ ወናውን እንጣስከየትም እንዳልደርስ አንት የሰሜን ንፋስ።”ሲል የመጨረሻ ምኞቱን ይተነፍሳል።እርግጥ ነው ወደ ምንምነቱ፣ ወደ ዘለዓለማዊነቱ መንጠራራቱ አንዳች ተስፋ ያጭር ይሆናል። በዚያም ተስፋ እንደሌለ ግን “ተስፋ” በሚለው ግጥሙ በግጥሙ አስቀድሞ ያስገነዝበናል።“ደበዘዘ ለትውስታ ቀለም አጣ ቀለሙጊዜ ትናንቴን ከፋቀው፣ ምንድን ነው ነገስ ትርጉሙ?”ሲል ይጠይቃል? ይሄን ተስፋ ማጣቱ በህይወቱ እንዲቆዝም የሚያደርገው ሞትን ያህል እጣ ፋንታ ማንዣበቡ ነው። በዚያው ግጥሙ ላይ እንዲህ ይለናልና።“ተስፋ ያደረግነው ተስፋ መድሃኒት ይሻል ራሱከሕመማችን ብንድን እንኳን፣ አይፈርስም የሞት ዳሱ።”ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
47በመጨረሻም ከሞት በኋላ አለ የምንለውን ዘለዓለማዊነት ሳይቀር ብላሽ ነው ብሎ ህይወትን ኦና ያደርግብናል። “አባቴ፣ እኔ ፣ ልጄ” በሚለው ግጥሙ ዘለዓለማዊነት ሳይቀር ባዶነት ነው ይለናልና።“ቢዥጎረጎር ህይወት፣ ቢቀየጥ ቀለሙአንድ ባዶነት ነው፣ ዘለዓለም ትርጉሙ።”እኛም የጊዜን መሸከም ውል በአጭሩ እንዲህ እንረዳዋለን።መጀመሪያ ምንም ነበር!ያ ምንም በትካዜ ወደ መሆን ተሸጋገረ።በመሆን ውስጥ ፍጡር ጊዜን ያህል ቀንበር ተሸክሞ ዳከረ፣በመጨረሻም ፍጡር ሁሉ ወደ ቀድሞ ምንምነቱ ይንጠራራል።በዚህ አፍታ የሚመስል ኡደት ውስጥ ግን ከላይ ያየናቸውን ስንኞች የሚመስሉ መባከኖች የሰርክ ተግባራችን ናቸው።መልካም ጊዜን መሸከም።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
48አብረን እንውደቅ?ቴዎድሮስ የማነብርሃን ለማቅጽ ፪ ቁጥር ፮ |ጥቅምት ፳፻፲፰
49አብረን እንውደቅ?ቴዎድሮስ የማነብርሃን ለማ...የሰው ልጅ አስተሳሰብ ቋ...ቋ…ቀጭ ሲል እንደ እንጨት ስባሪ ውስጤ ድረስ ይሰማኛል።ጥቃቅን ጭላንጭል ሀሳቦች እንዲወለዱ የተማማለ የሚመስል ስንኩልነትን የሙጥኝ ያለ አንድ ወጣት የነገውን ግርማ ገፍፎ ባዶ ቅርፊት መስሎ መሃላችን ቁጭ ብሏል።የዚህ ምንዱብ ወጣት መለያው ብዙ ነው...ወጣት፣ የማያወላዳ ነገን ያለመናፈቅ ትብታብ የሚታይበት ሆኖ ሁሌም ከታች ለብሶ ከላይ ሰውነቱ ለፀሐይ የተጋለጠ እርቃን ማንነት አለው።ወጣ ወረደ፣ተቀመጠ ተነሳ። ዘወትር ከእጁ የማይለያት የትምባሆ ማጨቂያ ብልቃጥ አለው።የአካባቢው ሙቀት ተደምሮበት እንኳን በብልቃጥ እፅ መያዝ ይቅርና እርቃን መሆንን ያስናፍቃል።ከዚያች ብልቃጥ በደቂቃ ለሁለትና ለሶስት ጊዜ መዳፉ ላይ እየተመተመ ዱቄት መሰል እፅ እየበተነ ወደ አፍንጫው እየላከ ሽቅብ ይስበዋል።እንዲያ የአፍንጫው ቀዳዳ በአቧራ ብናኝ የተደፈነ እስኪመስል ሲስብ አብሮት ኑሮውንም የሳበ ይመስለኛል።በዚህ መሃል... እኔን...የሀሳብ ደራሽ ጅረት ደርሶ ከብዕርና ከብራና ጋር አስታርቆ፣ ከሞትኩበት ሊያነቃኝ የፍትሃት መስቀል አውጥቶ ካላሳለምኩህ ሊለኝ ሲዳዳ፣ ልማደኛው የብየዳ ማሽን ከበስተ ቀኜ ሆኖ የጆሮዬን ግንድ ግመኛ ይጠልዘዋል።የሰው ሀሳብ በራዥ ባልታጣበት በዚህ መከረኛ ጊዜ የኔን እንቁ የሆነ ሀሳቤን ወሳጅ አጠገቤ መፈጠሩ አልገረመኝም።አልባሌ መሄጃ ያጡ የቃላት ጋጋታዎች ፍሬ በሌለ የንግግር ዘይቤ ታጅበው ውስጤ ካለው የመንፈስ መልአኬ ጋር ሊጋጩ ትከሻ ይለካካሉ...ይተሻሻሉ።የከበቡኝ የሰፈሬ ልጆች ያወራሉ፣ዙሪያዬን ኩራት ባጎበጠው አንቀልባ የታዘሉ ሰዎች የማያቋርጥ ንትርክ አዘል ወሬ ይዘው ይንጠራወዛሉ። ነገ የለሽ ወሬ ቅማል በበላው ምንጣፍ፣ ውድቀት በሰለጠነበት አንደበት ታጅበው በገረረ ድምፀት በወሬ ያንጎላጃሉ። እኔስ? ተደግፈው በጣላቸው የረብ የለሽ ውሎ ምርኩዛቸው ውስጥ አለሁበት ወይስ የለሁበትም? እላለሁ... እኔ እንጃ ብቻ አብሬአቸው ስላለሁ ሲወድቁ መውደቄ እቅድ የለሽ እቅድ ሲያወጡ፣የጅላጅል ተስፋ ሲሰንቁ መሰነቄ አይቀሬ ይመስለኛል።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰
50ብናኝን ከሙቀት አዳብሎ ያቀፈው የደረቀ ዓየር አካባቢውን ንዳድ አድርጎታል...ከታች ሰፈር አቅጣጫ የዝሁር ሰላት መስገጃ ሰዓት መድረሱን የሚጠቁም አዛን ከመስጊዱ በረዥም መስቀያ ላይ ከተሰቀለው ድምፅ ማጉያ ከፍ ብሎ ይደመጣል።አዛኑ ውስጥ ብዙ ነገር እንዳለ አውቃለሁ።የመስገጃ ሰዓት መድረሱን ማሳወቂያ አዋጅ እንደሆነ ባምንም ከፈጠረን ፈጣሪ ጋር በእልፍ ርቀት እንደተለያየን የሚነግረን፣ በስጋ ውድቀታችን አንጥፈን ከተጋደምንበት የርክሰት መደባችን በፅድቅ እንነሳ ዘንድ ቀስቃሽ ደወላችን ነው። በርክሰታችን ምክንያት ምን ያህሉን የመልካምነት ካባችን እንደተገፈፈብን እናስተውል ዘንድ የተሰጠን መቀስቀሻ የአስተውሎት መንገዳችንም ነው።ሰው በወል አበደ የእውቀት መጋረጃ ቁልቁል እየቀደደእያለ አንድ ጀብራሬ ሰካራም ወዳለንበት መጥቶ ሲቆም አጠገቤ ያሉት ደራሽ ጎርፍ ከመሰለ ወሬያቸው ተናጥበው ፀጥ አሉ።ጀብራሬው ሰካራም ሁሌም ስራ ፈትነታቸውን እቅድ የለሽ ውሎአቸውን ዘርግፎ ልክ ልካቸውን ስለሚነግራቸው አይወዱትም።በተናጠል ሳይሆን በወል ይሰድቡታል።ሰካራሙ ሰውዬ ለሚያወራው ወሬ ወሬኞቹ የሚያለብሱት የውርደት ካባ ግድ ሰጥቶት አያውቅም...አንዳንዴ እንደ እብድ እብድ ያጫውተዋል።ትንሽ እቅድ ይዘው ዕልፍ ለሚዘምሩ ለመንደሬ ልጆች ከስካር መጋረጃ ጀርባ ቆሞ ምግባራቸውን ስለሚነግርልኝ ግን እወደዋለሁ።በዚህች መንደር ሁሌም ውድቀት ይወራል። ወጣትነት ሰክኖ ተስፋ መቁረጥ ይነዛል። ነገን ለመኖር ዛሬን ማሻሻል ለሚፈልግ አንድ ምስኪን ፍጡር ይህንን መስማት ክስረት ነው። መኖርን በሚኖሩ ሰዎች መካከል አለመኖርን ማውራት ግለሰቡን ጠልፎ እንደመጣል ነው። እናም በዚህች ሰፈር ብዙ ይወራል ብዙ ይባላል። ትዝብት ያጠቆረው ገፄ ብዙ ይናገራል። ሽራፊ መንገድ ዳር ቆሞ የሚያንጎላጅ ወጣት ሳይ ህመሜ ያይላል።“አሁን ማን ነው ለዚህ ሁሉ ወጣት መነሁለል ተጠያቂው?” እላለሁ።ሌሎች እንደሚሉት “ለባከነው የወጣቱ ዕጣ ተጠያቂው የበላይ አካል ነው።” ማለትን አልሻም።ምክንያቱም አስተሳሰቡ ቀድሞ እንዳይላሽቅ እንደዜጋ ያደረግንለት ምን አለ? በስነ-ምግባር እጦት እንዳይወርድ የሰራነው ሥራ ምንድነው? የሀገርን ባህልና ቱፊት አውቆ እንዲያድግ ያደረግነው የዜግነት ግዴታችንስ ምን ነበር?... ወጣቱስ ቢሆን ላለመውደቅ የተፍጨረጨረበት የህይወት ምዕራፉ የቱ ጋር ነው? የአንድ ወገን ትችትና ጣት መቀሳሰሩ ከፊት ለተነሳብን የድህነት ማዕበል መርከብ አይሆነንም።ቅጽ ፪ ቁጥር ፰ |የካቲት ፳፻፲፰