ባይራ
ባይራ የማላቅፍህ ስለምሰስትህ ነው…። ከ ማሰሮ የዘገንከውን ትኩስ እፍኝ አሹቅ ወደ አፍህ ስታስጠጋው፣ አፍህ እዚህ የከንፈርህ ጥጋት ጋር ስታደርሰው፣ ብርር’ድ ብሎብህ ያውቃል? ወይ ደሞ መንገድ ላይ ለማታውቀው ሰው በፈገግታ ሰላምታ ሰጥተህ ስታልፍ ፈገግታህ በስንት ሰከንድ ይከስማል? የእግርህን አውራ ጣት የመታህ ትንሽ እንቅፋት ልብ ስር የሚገባ ህመም በስንት ደቂቃ በረደልህ? የጣቶችህን አንጓዎች እያጠፍህ ‘ቋ’ ለማድረግ የፈጀብህን ቅፅበት በቁጥር ታውቀዋለህ? በህልምህ ያየኸው ውብ ዓለም ልክ ዓይንህን ስትከፍት ለመጥፋት ከብርሃን ይፈጥን አይደል? ልክ እንደዛ ፣ ልክ እንደ ሁሉም ፍቅር ይበርድብኛል። በእጄ ሳልይዘው ይሰበርብኛል። ምን ላድርግ? በሩት ሃብተማርያም 1
ባይራ “ዘ ንድሮ ፍቅር የለም!” እያሉ በራሳቸው የፍርሃት ድንበር ውስጥ እንዳሉት ሰዎች አይደለሁም። ሰው የተባለ ፍጡር በህይወት እስካለ ድረስ ፍቅር የትም አለ። አይታየንም እንጂ ያያዘን ቀጭን መሳይ ጠንካራ ድር ፍቅር ነው። አለ ብዬ አምኜው እየኖርኹ ታዲያ ስይዘው ለምን ጥብቅ አያደርገኝም? ስዳስሰው ቁንጥጫው የሚብሰው ለምንድን ነው? ስስመው ለምን ጥርሱን ያገጣል? መጣ ብዬ “እሰይ! እሰይ! ከመጣህ ማርያም ታምጣህ!” ብዬ፣ ከንፈሬ ከማሰሪያው ተፈቶ ፈገግ ሳልል ወዴት ሄዶ ይጠፋብኛል? እንደ ማድጋ ሊጥ፣ ተሟጦ እንደሚጋገር፣ አሟጦ የሚያፈቅረኝ የት ነው? ሁላችንም፣ እኔም አንተም ሳንዘጋው የተውነው የትዝታ በር አለን። በቀጭን የምትነፍስ ትላንትን የምትናፍቅ ንፋስ የሚያሳልፍ በር አለን። አሁን ቁጭ ብዬ ሳስበው አጠገቤ የነበሩ፣ ያፈቀርኳቸው ፤ ያቀፍኝ ፤ ሳናይሽ አናድርም ልመናዎች ሁሉ የትዝታቸውን በር መሸጎሪያ እንጂ በእያንዳንዳቸው ልብ ውስጥ የራሴ የትዝታ በር የለኝም። ታዲያ ይሄ አያደክምም? በዓለም ያንተን አይነት ፈገግታ ያለው አይቼ አላውቅም። ፈገግ ስትል ፊትህ ላይ ያለውን ኃይል አልችለውም። እወድሻለሁ ስትለኝ እያንዳንዷን ፊደል ሰንጥሬ ባያት ምንም ማብለጭለጫ ቅመም እንዳልተጨመረበት አውቃለሁ። ፊቴ ስትመጣ የዋህነትን ብቻ ትሰዋልኛለህ። ደስ ትለኛለህ። ዓይኔን ከድኜ እጄን ልሰጥህ እፈልጋለሁ። ታዲያ ግን እፈራለሁ። ፍርሃቴን አሸንፌ ባቅፍህ በማግስቱ ትተወኛለህ። አነሳሴ ጋ አውግተን ሳንጨርስ ወድቄ እነቃለሁ። እንዲሁ ባይህ ይሻላል። እንዲሁ በሩቅ ብመኝህ ይሻላል። ምኞቴን ሸሽጌ ፤ ምኞትህን ሸፍኜ እንደ ሩቅ ዘመድ ብንተያይ ይሻላል። ላጣህ ስለማልፈልግ ነው ከጠረንህ አፍንጫዬን ያቀብኩት ፤ እቅፌን ያቀዘቀዝኩት ዘላለም በልብህ እንድታቅፈኝ ነዉ። የ40 ቀን እድሌ ትለኝ ነበር አያቴ። ያኔ ታዲያ እስቅ ነበር። 40 እና እድል ምን እንዳቆራኛቸዉ ይደንቀኝ ነበር። አሁን በየቀኑ ሳይገባኝ አልቀረም። የ40 ቀን እድል አለን ሁላችንም። በማይታይ ማተብ አንገታችን ላይ ያለ። ተራራው ሰው፣ ሆኖ ከንፈሬን ባይስመኝ ተራራው ሰው ሆኖ፣ ጡቴን ባይዳብሠው ተራራው ሰው ሆኖ፣ ዓይን ዓይኑን ባላይ ጸሀይ እሞቃለሁ፣ ወጥቼ ከላይ። እና ትወደኛለህ? 2
ባይራ ... ከናፍቆት ጋር ድብብቆሽ መጫወት ስጀምር፣ ልክ እንደማንኛዉም ተጫዋች ተናፋቂው ተደብቆ ሲቀር ጨዋታዬን አቆማለሁ ብዬ ነበር። የመፈለግ ፅናቴ ተሰብሮ ወይም ሟሙቶ ያለቀ መስሎኝ ነበር።እንደዚህ የተደበቀበትን ጋራና ሰርጣሰርጥ ሁሉ በልቤ አስሳለሁ ብዬ አልነበረም። ልቤ ኩስ ኩስ ብላ ከእግሬ ስር እየተራመደች የምትመራኝና የምታወራኝ ይመስለኛል። እንዴ እሱም ጋር እኔም ጋር ልቤ ልትኖር አትችልም። ሲፈቀር ልብ ይሰ’ጣል ይሉ የለ እንዴ? ታዲያ የኔ ልብ ይቺት ከፊቴ። ፍቅር ሳይሆን እልህ ነው እንዴ የያዘኝ? የጨዋታ አሸናፊ አለመሆኔ ተሰምቶኝ ነዉ እንዴ? እያልኩ አስባለሁ። “ ሰማሽኝ እቴ አካልሽ ሁሉም እዚህ ነው። ሀሳብሽ ፤ ህልምሽ ፤ እርካታ እና ስሜትሽ ሁሉም ሰዋዊ ስሜቶችሽ ናቸው እሱ ጋር የተደበቁብሽ። ሰው ሲያፈቅር ሰውነቱን ፣ ሰው የመሆኛ፣ ሰው የመባያ ነገሮቹን ነው አሳልፎ ለሚያፈቅረው የሚሰጠው። አብሬሽ ያለሁት ልብ ተብዬ እንድጠራ የሚያደርጉ ስሜቶቼን ስለወሰደብኝ ነው።” አለች ኩስ ኩስ እያለች። ... ለነገሩ ልክ ናት እላለሁ። ምን ታልሚያለሽ ቢሉኝ ከንፈሩ ስር የማርያም ስሞሹ መሆን አይደል? ምን ታስቢያለሽ ቢሉኝ ንፋስ የራሱን ፀጉር ስንቴ ዳበሰችው? ጨረቃ ለምን አዘቅዝቃ ታየዋለች? እንቅፋት መቶት ይሆን? አንዷ ቁሌታም ስታልፍ አይታ ተመኝታው ይሆን? አንድ ጤነኛ ሰው እንዲህ ያስባል? ...አስቀድሰው ሲጨርሱ እንደሚሰጥ ቁራሽ፤ቤቱ ቢሄድም የሚበላ እንደሌለው ሰው ያቺን ቁራሽ እንደሚያጣጥማት (እንደዛ ናፍቆቱ ይጣፍጠኛል) ፤ የመጨረሻ የጎለተችው ድንች ተሸጦላት ለልጆቿ ራት መግዛት እንደምትፈልግ እናት ገዢን በጉጉት እንደሚጠብቁ ዓይኖቿ (እንደዛ በየቀኑ ለፍቅሩ እጓጓለሁ ) ፤ ረጅም ዓመት በደዌ ተሰቃይቶ ጎኖቹ ሁሉ በቁስል ነደው መተኛት እንደናፈቀው ፣ፈውስ መጣልህ፣ ጎንህ አገገመ ተብሎ የነገ ፈውሱን አስቦ እንደሚጋደም ጎልማሳ (ልክ እንደዛ የፍቅር እፎይታን እናፍቃለሁ)። ... ዓይኔን አልነግረውም። ፍቅርህ ላይመጣ ይችላል ብዬ አልነግረውም። በሩቁ እያየነው እንደምንኖር አልነግረውም። ጉጉቱን አውቃለሁና ቢጠብቅ ይሻላል። እጄን “ደረቱን አትዳብስም ፤ አንገቱ ዙሪያም ላትሆን ትችላለህ እኮ” ብዬ እንዴት ላስረዳው? እግሮቼን “ወዳለበት አትሄዱም፣ ቁሙ!!” ማለት አልችልም። ከእግሬ ቀድሞ የእርምጃ ሀሳቤ የት እንደሚሄዱ ይነግራቸዋል። ማንንም ማዘዝ አልቻልኩም። ሀሳቤን ፤ ህልሜን ፤ ዓለሜን ሰጥቼ ነዋ የወደድኩት። ግን ትወደኛለህ? 3
ባይራ ዳሰሳ ይህ አንድ ወጣት ጀማሪ አንባቢ የደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ 16ተኛ መጽሐፍ የሆነውን ቤባንያን በማንበብ ሂደት ላይ የተሰማውን ስሜት ብቻ ያሰፈረበት ጽሑፍ ነው። ፕሮፌሽናል ዳሰሳም ሆነ ሂስ አይደለም። ከዙበይር ኢብራሒም 4
ባይራ ቀብድ ቢጤ ምንአልባት ጸሐፊው ራሱ ባላሰበበት መንገድ ተረድቼው ሊሆን ይችላል እና ቅር እንዳትሰኙብኝ አደራ እላለሁ። ለነገሩ ራሱ ጋሽ ዓለማየሁስ ቢሆን “መጽሐፉ አንዴ ከእኔ እጅ ከወጣ በኋላ የእኔ አይደለም “ብሎ የለ፤ በቃ እንደዚያ ውሰዱታ። *** በቅድሚያ ታላቅ ደራሲ የመሆን ጅማሬ ላይ ነኝ ሊል ሲፈልግ አጥቢያ ብሎ መጣ። ከዚያማ አንዴ በከፈተው ቀዳዳ በኩል ተከታታይ ጥበቦቹን ሲያቀብለን ቆየ። ከጊዜያት በኋላ ትሪሎጂ (Trilogy) ብሎ ደግሞ እንዳከበርነው እንድንኖር በፍቅር እና በእውነት ስም አስማለን። ሶስተኛውን “ይዞብን ይቀር ይሆን?” ብለን ስናስብ “መለያየትማ ሞት ነው” ብሎ ለመደምደሚያው አዘጋጀን። ትሪሎጂውንም በ”ሐሰተኛው” ደመደመ (ምንኛ ያማረ መደምደሚያ!)። ጋሽ አሌክስ ናፈቀን ስንል ደግሞ “ከሀያ ዓመት በፊት ፃፍኩት” ሲለን ባላመንነው “ የተጠላው እንዳልተጠላ” መጣልን። አሁን ደግሞ ቤባንያን ይዞ ተከስቷል። እንግዲህ መሰላሉ እዚህ አድርሶናል። የእውኑ ዓለማየሁ ገላጋይ አዲስ አበባን ለመጀመሪያ ጊዜ በመስክ ስራ ምክንያት በሰላሳ ዓመት እድሜው ለቀቀ። በድርሰቱ ደግሞ ከአዲስ አበባ ለመውጣት ሌላ ሰላሳ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ለመጠበቅ የተገደደ ይመስላል። ያው ወጣ ገባ ብሏል። ነገር ግን በቋሚነት አዲስ አበባን ለቆ ጠቅልሎ የወጣው በዚህ ስራው ይመስለኛል። (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ) መጽሐፉን እዛው ጋር ገጽ በገጽ እየተመላለስኩ እየደጋገምኩ አብሬ ከረምኩ። ሲያልቅብኝ ደግሞ እንደ አዲስ ጀምሬ ጨረስኩት። አሁን ምን አለፋችሁ ቅርርባችን “ከዘመድ በላይ ሆኗል ሁላ።” መጽሐፉን እንቶኔ የአፃፃፍ መንገድ ነው፤ እገሌ ኢዝም ነው ብዬ መፈረጅ አልፈልግም። አንብቦ እንዳለ ማጣጣም ሲቻል በሆነ ዘርፍ ውስጥ ለማሳቀፍ ያለ ሩጫ አይገባኝም። አንድ ጊዜ ጋሽ አሌክስ በአንድ መጽሐፉ ላይ ውይይት ለማድረግ እንግዳ ሆኖ መጥቷል። በመሀል ከታዳሚ አንድ ጥያቄ ተነሳ። 5
ባይራ እንዲህ ይላል “ይህን መጽሐፍህን በሆነ ዘርፍ ውስጥ ለማካተት ቸገረኝ ። ምን እንበለው? ገላጋይዝም እንበለው?” “ግራቪቲን ተውና የወደቀውን አፕል አርፈህ ብላ” ነው ያሉት ልጆቹ?(ሃሃሃሃሃሃ) ኳ ኳ ኳ ወደ ሸኖ! .... ደራሲው መጽሐፉን ከዘፍጥረት ነው የሚጀምርልን። “የሸኖ ሰማይ ገና መሬትን ያላወቀ አፍላ ነው።መሬት ከጎን አጥንቱ አልተፈለቀቀችም ።” ይለናል። ድንቅ ሜታፎር! ኳ ኳ ኳ ወደ አሁን! .... ለማን በገበያውም፣ በጓደኞቹም፣ በዘመዶቹም ህይወት ውስጥ እያመላለስን እንመልከተው እስኪ። *** ደራሲው በዚህ መጽሐፉ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተንተርሶ ጥበባዊ በሆነ መንገድ ምክር ቢጤ ማስተላለፍ ፈልጓል::ለዚህም እንደ ማሳያ የሚቀርበው አንዱ ገፀ ባህርያቱ የተሳሉበት መንገድ ነው::በጋሽ ይማም በኩል አማራ ገባ፤በአደዬ በኩል ትግራይ ዘለቀ፤በአባ ብሩ በኩል ወደ ኦሮሚያ ጎራ አለ፤በእሞ በኩል ጉራጌ ተሻገረ፤ይሄ አልበቃ ብሎት አስመራ ሁላ ገብቷል፤በቤላ በኩል። ሸኖ ላይ መከተሙ በራሱ በአጋጣሚ አይመስለኝም። ይቀጥልና አንድ ቦታ ላይ ምንምነታችንን ሊያስታውሰን ይፈልጋል። በሆሴእ በኩልም የዲዮጋንን የአጥንት ለቀማ ታሪክ ካነሳ በኃላ እንዲህ ብሎ ይዘጋል:- “ይሄ ያልገባው የሸኖ አፈር ሁሉ በብሔር ተቧድኖ ይለይልን ይላል” በሌላኛዋ ገፀ ባህሪ እሞ በኩል ደግሞ እንደዚህ ይለናል:- “ተዋደው ያደጉ ተጣልተው እንኳን ተያይዘው ይወድቁ” በዚህ ሀሳብ በኩል “ተዋደንም ይሁን ተጋምደን አብረን መጥተናል:: ከዚህ በኃላ ያለ’ ጠብ ተያይዞ ለመውደቅ ከሆነ እንጂ አሸናፊ አይኖረውም” እያለን ይሆን? ከዚህ ጋር ተያይዞ ያሳደጉት ሰዎች ያደገበትን ቤት የተቀባበሉበት ቅደም ተከተል በአጋጣሚ ነው ለማለት ቸግሮኛል:: ጋሽ ይማም አደዬን ተቀበለ።አለማምዶ ጥሎ ሄደ ፤አደዬ አባ ብሩን ተቀበለች። አለማምዳ ጥላ ሄደች... 6
ባይራ ቤባ ለእኔ እንግሊዝኛውን ቃል ልጠቀምና Desire(lust) ነች:: ዓለማዊ ፣ጊዜያዊ ደስታን ትወክላለች::”Attachment”ን ትወክላለች:: አብረቅራቂዋን፤ እንካ ግን አትንካ የተባልናትን በለስ(ዓለም) ትመስለኛለች:: የተጣበቅናት ጊዜ የድንጋይ መሰናክል ነች:: መንጭቀን የተላቀቅናት ጊዜ ደግሞ ወደ መንፈሳዊ መገለጥ የምትወስደን መሰላል ነች:: ዋና ገፀ ባህሪው መፍትሔ ከቤተ-ክርስትያን አፀድ በተገኘበት ቅፅበት ቤባንያ ከአእምሮው መዝገብ ስትጠፋ እናያለን:: ቆይታውን ጨርሶ ሊወጣ ባሰበበት ቅፅበት ደግሞ በሀሳብም በአካልም ትከሰታለች:: “ሂድ እያለች እየገፋች ትወስደኛለች”ይላል “ግንድ አደናቅፎኝ ስወድቅ ደግሞ ቁራጭ ሳቅ ይከተለኛል”ይላል ይህች ሳቅ በDesire ተገፍተን በዓለማዊ እንቅፋት ተጠልፈን ስንወድቅ ከምትሳቀዋ ቁራጭ ሰይጣናዊ ሳቅ ጋር አትመሳሰልም??? ከዚያስ:- በተከተልካት ቁጥር ታስደበድብሀለች(ልክ በወንድሞቿ ሲደበደብ እንደነበረው ማለት ነው)። እንዲያም ሆኖ መከተልህን አታቆምም:: የምታቀምስህ ነገር ጊዜያዊ ቢሆንም ውሸት አይደለማ:: ይሰማሀላ:: ታጣጥመዋለሃ:: በአንደኛው ቦታ ላይ መፍትሔ ተደብድቦ በተኛበት ቤባ ትመጣና እቅፍ ታደርገዋለች:: ቀጥላም እንዲህ ትለዋለች:- “ይህችን ፍለጋ ነው አይደል የምትደበደቢው?” እርሱም በዚያች ብልጭ በምትል እቅፍ ምክንያት ህመሙን ሲረሳ ይታያል:: ብልጭታ ብትሆንም ትጣፍጣለቻ:: መኖርን ታስመኛለቻ:: የታሪኩ ማጠንጠኛ የሆነችው ዋና ገፀ-ባህሪዋ ቤባንያን በሁለት አይነት መልኩ ተመልክቻታለሁ:: 7
ባይራ ሁለተኛው እይታዬ ሁሉም ሰው ያያት አይነት ቤባንያ ናት:: ያለ ልክ አፍቃሪዋ፤ ዘጠና ዘጠኙን ትታ አንዱን ፍለጋ የምትወጣዋ፤ በድፍረት ከእየሱስ ጋር የተነፃፀረችዋ ናት። (ይህችኛዋ ፊት ለፊት የቀረበችዋ ስለሆነች ማብራራት አይጠበቅብኝም) *** በመጽሐፉ ጥቅልል ያሉ ግን ደግሞ እንደ ሸማ መተርተር የሚችሉ አባባል መሳይ አረፍተ ነገሮች መሐል ጥቂቱን ላስቀምጥ “ከአንድ የጉም ማህፀን ተወለደ ወደ ሌላ የጉም ማህፀን ገባ ትእይንቱ ቅፅበት ብቻ ነበር።” “ራሳቸውን መግዛት ያቃታቸው መሪዎች ናቸው የመግዛት ጥማቸውን በእኛ በኩል የሚወጡት።” “አንዴ ሲሰደብ ያብራራ መስሎት አስር ጊዜ ራሱን ይሰድባል።” “ጫማህን የማሳየት ፍላጎትህ የሰው መጫሚያ ስመህ እንድታድር ያስገድድሀል።” “የታዘዘው መጣ ስኳር ጨምሬ አማሰልኩ። ሁሉም በታዘዘለት ተጠምዷል።” “ልጅነቱ አጥብቆ እንዳይዝ ሲያስገድደው ለስላሳውን አንዴ ከጠርሙሱ አንዴ ከብርጭቆው ይቀምሳል።” “አሁን ይሄ ኑሮ ጠላት የሚያስፈልገው ሆኖ ነው?”(እጅግ በጣም የወደድኳት) *** መጽሐፉ እንደ አጠቃላይ መንፈሳዊነትን(spirituality ) ይሰብካል። ከመጣበቅ(attachment )፣በቦታ ከመፈረጅ (labeling )መላቀቅን ሊሰብከን ሲፈልግ ዋናው ገፀባህርይ መፍትሔ ከየት እንደመጣ አይነግረንም። እንጀራ አባቶቹና እናቶቹ ሲመጡ ከየት እንደመጡ አይነግረንም። ሲሄዱም ወዴት እንደሚሄዱ አይነግረንም። ልክ ነዋ፤ ወደዚህች ዓለም ስትመጣም ከየት እንደመጣህ አታውቅም (You just exist ) ስትሄድም ወዴት እንደምትሄድ አታውቅም። ከጉዞ መሐል ትገኛለህ፣ ትጓዛለህ፣እየተጓዝክ ትጓዛለህ ይልሀል። “እንደው ልንገር እንጂ ታዲያ ለማን ልንገር ሁሉም ስደተኛ አንቱ ነሁ ባላገር” ይለናል ። “እኔና ዱንያ(ይህች ዓለም) ያለን ግንኙነት ረዥም ጉዞ እንደሚጓዝ እና ለማረፍ አንድ ዛፍ ስር እንደተጠለለ መንገደኛ እኮ ነው።” እንዲሉ ነብዩ ሙሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) በመጽሐፉ መጨረሻ አካባቢ ሁለቱም ብልጭልጭ አፍቃሪዎች ቤባንያን(እንቅፋቷን) ካጡ በኋላ ወደ መንፈሳዊ መገለጥ ሲጓዙ እናያለን። አንድ አንድ እያሉ መሰላሉን ይወጣሉ። ጫፉ ላይ ግን አይደርሱም። ምክንያቱም ዓለሙ የመጓዝ ዓለም ነው። ወደ ትክክለኛው መንፈሳዊ ፍቅር የመቅረብ ጉዞ ነው። እየተጓዝክ ታልፋለህ እንጂ አትደርስም ። ነገሩ ከመድረሻው ሳይሆን ከመንገዱ ጋር በፍቅር የሚወደቅበት ነው። 8
ባይራ “ህይወት ጉዞ ከሆነች አቅጣጫችን ከእርክስና ወደ ብፅዕና መሆን አለበት። ስንፈጠር አልታገዝንም። በራሳችን መፍጨርጨር በውልደት ከተነከርንበት ክፋት በሂደት ወደ ደግነት ማቅናት የህይወታችን ግብ ነው።” መንፈሳዊ ልህቀትን በተለየ መንገድ ለማሳየት ሲፈልግ ደግሞ አባ ጃርሳ የተባሉትን ገፀ ባህሪ ያመጣል:: እንስሳትን አሳድገው፣ አሰረጅተው ወደ መጡበት የሚሸኙትን አዛውንት ማለት ነው:: ይህችን የአባ ጃርሳ ድርጊት አንዳች መንፈሳዊ ከፍታን የምታሳይ ናት ካለ በኃላ በሌላ ገጽ መጥቶ ደግሞ እንደዚህ ይላል:- “የተዋለላቸውን የማያውቁ ምስጋናም የማይጠበቅባቸው..” ይላል። “ህይወትን ያለ አቋራጭ ጠግበው እንዲጠጡ ዓለም ላይ ካሉ እንስሳት ሁሉ ለእነሱ በረከቱ እንደተሰጣቸው ያውቁ ይሆን?”ይልና “አሁንም በዚህ የሚረካው ህይወታቸውን እያቋረጠ የሚደሰተው ያው ሰው ብቻ ነው” ይለናል:: ውስጥ ወይራ ልንላት እንችላለን? እንበላት ግድ የላችሁም በመጽሐፉ ስለ ፍርሀትና ፍቅር በተደጋጋሚ ተነስቷል:: “ሰውን የሚገዛው ፍቅር አልያም ፍርሀት ነው። ከሁለቱ ውጪ መሆን አይችልም” አይደል የሚባለው?ሁላችንምስ ሁለቱ ውስጥ በመዋለል አይደል ዘመናችንን የምንገፋው ?እሱንም እድለኛ ከሆንን:: የፈጣሪ አልያም የሰይጣን ነህ:: እንደ ፍጡር መሀል ሜዳ የሚባል ነገር አልተሰጠኀም ::ይህንን በገፀ ባህርያቱ በኩል በደንብ አሳይቶናል:: *** አሁን ደግሞ በተራ ምልልሶች መሀል በሽሙጥ ጣል ከሚያደርጋቸው ሀሳቦች ጥቂቱን... “ለወንበር ያለበስኩትን ኮት ገፍፌ ለበስኩ።” “አህያ ነው በአህያ እየተመራ ያለው በለኛ።” “ድንጋይ ድንጋይን እየገጨ ውጤት ሲያስመዘግብ እያየሁ ቆምኩ።” *** አንድ ቦታ ላይ ገፀ ባህሪው እንደዚህ ይላል:- 9
ባይራ ፈጠረ ይለናል። ደራሲው ራሱ ድርሰቱ ውስጥ አለ። በስም ሳይገለፅ። በድርሰት ውስጥ ሌላ ድርሰት ማለት ነው። በስተመጨረሻም ጋሽ አሌክስ የፈጣሪን መንበር በምናብ ተረክቤያለሁ ብሏል። “ፈጣሪ ራሱ በዳግም ፈጣሪዎች ተፈጣሪ ሆኗል” ይለናል። ጉድ በል ! ይሄኔ ነው እንግዲህ አስታርቂኝ ማለት ። *** ለአንዳንድ ገፀ ባህሪያቱ የሰጣቸው ስሞች ዘና የሚያደርጉ ናቸው *ሌባው ሰረቀ(ሠረቀ ብዬ ነው ያነበብኩት ሃሃሃ) *ጉንፋናሙ አባይነህ *የንጉሱ አጎብዳጅ ጀነራል ይገዙ *ሰጠኝ በግዱ ስሞቹ በምክንያት ከወጡ ዘንዳ መፍትሔም ስሙን ይመስል ይሆናል ብዬ ብጠብቅም... እንዳንጠይቀው ደግሞ በሆሴዕ በኩል ታላላቅ ደራሲዎችን ጠቅሶ “ህዝባቸውን ከመሳደብ ባለፈ መፍትሔ ማምጣት ያልቻሉ የቃላት እማሪዎች ናቸው” ብሎናል። “ብትፈልጉ ከእነዚህ ውስጥ መድቡኝ” እያለን ይሆን??? *** ደራሲው በዋና ገፀ ባህሪው በኩል የክህደት ውጤት የሆነው የወረቀትና የዲጅታል ገንዘብ ጉዳይ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳለ ለማሳየት ይሞክራል ።(“ክህደት???”ብላችሁ ከጠየቃችሁ “Nickson shock”ብላችሁ ጉግል ታደርጉ ዘንድ እጠቁማለሁ።) ደራሲው እንደዚህኛው መጽሐፉ በእምነት ነክ ሀሳብ በኩል ሚዛናዊ ለመሆን ሲሞክር ያየሁበት የለም ። እንደውም የኛ አማኝ ነን የምንል ሰዎችን በእምነት እና በክህደት ወይም በእምነት እና በጥያቄ ውስጥ የመዋለልን ኑሮ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል። “ዘሀቲ ጥበብ ፈጠረተና”(አንዲት ጥበብ ፈጠረችን) ሲል ይቆይና መልሶ ደግሞ አንዲት ተንኮል በሚል ይቀይራታል። (በዚህ በድህረ ዘመናዊነት ጊዜ የአብዛኛው “አማኝ” መንገድ ይህንን ይመስላል። ዋሸሁ???) ዋናው ገፀ ባህሪው መፍትሔ ፍጥረት ዓለሙን በአንክሮ ሲያስተውልና በእጅጉ ሲገረም “ዘሀቲ ጥበብ” ይላል። ህይወት የማይለቅ አዙሪት ውስጥ ስትከተው ደግሞ “እውነት አንድ ጥበብ ናት የፈጠረችን? እንዲህ ያለ ተንኮለኛ ማድፈጥ ያለበት ግጥምጥሞሽ የጥበብ ውጤት ነው? አንዲት ተንኮል ማለት አይሻልም?” ይላል። ከቤተክርስቲያን አፀድ ተቀምጦ ጥያቄው ሁሉ ድራሹ ሲጠፋ “ዘሀቲ ጥበብ” ይላል። ከዚያ ደግሞ ህይወት ዱላዋን ስታሳርፍበት “ ተንኮለኛ ደራሲ እጅ የገባን ይመስለኛል፤ እግዚአብሔርማ ይህን አያደርግም “ ይልና ይሸሻል፤ ማን? ራሱ ደራሲው ዓለማየሁ ። “ከዚያስ?” አትሉም ? ዓለማየሁ ገላጋይ ደራሲውን ፈጠረ ። ስም ያልተሰጠው ደራሲ ደግሞ ቤባንያን 10
ባይራ እንደ ሀገር ጊዜውን ያልጠበቀ መንጠራራት ላይ እንዳለን ለማሳየት ሲፈልግ እንዲህ ይላል።”ሸኖ እቃ በእቃ መለዋወጥ መች አንሷት? ቤታችን የተትረፈረፈውን ይዘን አንዲት መገናኛ ቦታ ላይ መቆም፤ሌላው ቤቱ የተትረፈረፈ ግን እኛ ዘንድ የሌለ ይዞ ሲመጣ መለዋወጥ፤ገንዘብ ባንክ ለሸኖ ምን ያደርግላታል!?” የገንዘብ ጉዳይ ከኢኮኖሚ አሰተሳሰብም በላይ እንደተሻገረ ሲገልፅ “የደም ዝውውር ማዕከል”፣ “የትንፋሽ መለኪያ” ሆኗል ይለናል። እንዲሁም የዘዋሪዎቹ ዋነኛ እኛን መቆጣጠሪያ መሳሪያ ሆኗል:: ምናልባትም ወደ እቃን በእቃ ልውውጥ ብንመለስ “ከመንግስትና ከጀሌዎቹ ፍፁማዊ ተፅእኖ ነፃ እንሆናለን። “ ይለናል። ወንድሜ “ቴሌ ብር”፣”እንቶኔ ብር” እየተባለ ጨርሶ ወረቀቱን ገንዘብ ለማስቀረት የሚደረገው ሩጫ ተራ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሀሳብ ከመሰለህ አልተገናኘንም። (ገብቶሀል አላብራራም) በአንዱ ገፀ -ባህርይ አማካኝነትም ባንክን “የገንዘብ ሱቅ” ወይንም “የአራጣ ሱቅ” ይለዋል። በመጽሐፉ የአራጣ አበዳሪ የሆኑትን አባ ድሪባን አንስቶ “ባንክ ማለት ዘመናዊ አባ ድሪባ ማለት ነው ። ወይም ደግሞ አባ ድሪባን በሺህ አባዝቶ መልቀቅ ማለት ነው”ይለናል። የገንዘቧን ጉዳይ በዚህች የአንድ ገፀ ባህሪ ንግግር ልጨርስ። በምልልስ መሀል እንደዚህ ይላል:- “አንድ ቀን ከረባት ባሰረ ጅብ ታስበሉናላችሁ።” እናስ ከረባት ባሰረ ጅብ ከመበላት የምንድንበት መንገድ ያለ ይመስላችኋል? አላውቅም! 11
ባይራ መጠነኛ ቅሬታዎቼ *የመጽሐፉ ቅርፅ አልባ መሆን! ቁርጥርጥ ያሉ ብዙ ሀሳቦች የታጨቁበት ሆኖ ታይቶኛል። በእርግጥ ሀሳብ ሀሳቡን ብቻ ለሚፈልግ እንደ እኔ አይነት አንባቢ ተስማሚ ነው:: አብዛኛው አንባቢ ግን የሚይዘው ታሪክ ይፈልጋል፤ ያስፈልገዋልም:: ምሳሌ ፍቅር እስከ መቃብር፤ትኩረትን በሚስብ፣ልከኛ ፍሰት ባለው የፍቅር እና የቤተሰብ ታሪክ ባይታሽ ምን ያህሉ ሰው ያነበው ነበር? በውስጡ የያዘውን ትልቅ ሀሳብ ሳያስተላልፍ መቅረቱም አልነበር? አንባቢ ሰብለ ወንጌልን ፍለጋ ሲመጣ አያይዘህ ሀሳቡን ትግተዋለህ... እያነበብኩ በእርግጥም ጋሽ አሌክስ ሸኖ ለመጀመርያ ጊዜ ከአዲስ አበባ መውጣቱ አስታወቀበት እያልኩ ነበር:: እንግዳ ሆኗል :: ሸኖን ከመረጠ አይቀር ከሸኖ ጋር በስሜት ልንቆራኝ በሚያስችለን መልኩ ቢስልልን መልካም ነበር እላለሁ:: ሆሴዕ ጋሽ አሌክስ ራሱን የቻለ ገፀ ባህሪ መፍጠር አቅቶት ነው ዲዮጋን ላይ ያስደገፈው? ወይንስ እግረ መንገድ ዲዮጋንን ለማስተዋወቅ ሲል ያደረገው ነው? የሚለው ጥያቄዬ ነው። 12
ባይራ ይሄ“የሰማዩ ጥልቀት”፣ “ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል” አይነት ገለፃዎች ብዙ ገጽ ይዘዋል:: እንደውም መጀመርያው አካባቢ “ጋሽ አሌክስ ምን ነካው? ጀማሪ ደራሲ ይመስል አበባው፣ አየሩ፣ ሽታው የሚለን” እያልኩ ሳስብ ነበር:: *** አጠቃላይ የመጽሐፉ ሂደት ለእጣ ፋንታ እጅ በመስጠትና ነፃ ፍቃድን በመጠራጠር ላይ የሚሽከረከር ነው:: ከዘፍጥረትም አይደል የጀመርነው ዞረን ዞረን በበርካታ ነገሮች ውስጥ አልፈን ስናበቃ በዚህች የመጽሐፉ መደምደሚያ በሆነች ሀሳብ ነው:: “አንዲት ጥበብ ሰው ያስመሰለችን ምንም ነን።” ከዘፍጥረት ወደ ምንምነት! ይህ ነው የሰው ልጅ ጉዞ፤ የሰው ልጅ ብቻ አይደለም የዓለምም ጉዞ ጭምር:: አላስፈላጊ ገለፃዎች ሀንቲ ጥበብ ፈጠረትኒ! ዋሪ ነጋ! ራራ ነጋ! 13
ባይራ ቁራኛዬ ቁራኛዬ በሲነርጂ አበሻ ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ የቀረበ የደራሲና አዘጋጅ ሞገስ ታፈሰ ፊልም ነው። የፊልሙ መቼት ፲፱፻፲፮ ዓ.ም በንግሥተ ነገስታት ዘውዲቱ ዘመን እንዲሆን ታስቦ የተሰራ ነው፡፡ የፊልሙ ታሪክም ጎበዜ ደርሶ/ጋሻዬ/ የሚባል አንድ የቆሎ ተማሪ በማህጸን ሳለ በልጅህን ለልጄ ወግ ለትዳር ቃል የተገባችለት አብሮ አደግ ፍቅሩ “ጎንጥ ጥጋቡ” በሚባል የጭቃ ሹም ተጠልፋ ጠፍታበት፤ ከብዙ ዓመታት ፍለጋ በኋላ አግኝቷት እሷን ለማስመለስ የሚሄደውን ርቀት የሚያሳይ ነው። በፊልሙ ንጉሣውያኑን ይጠቀሙበት የነበረውን “በላ ልበልሃ” በመባል የሚታወቀውን የፍርድ ስርዓት ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ በበላ ልበልሃ የፍርድ ስርዓት መሰረት በዳይና ተበዳይ ኩታቸውን ወይ ከላይ የደረቡትን ማንኛውም ቡሉኮ በአንድ እዚያው ባለ ሹም ወይም ባላባት እርስ በእርስ ይታሰራሉ። እስሩ ሳይፈታ እንዲዳኛቸው ከሚፈልጉት ሸንጎ እንዲደርሱ መሃላ ያደርጋሉ፡፡በዚህ መልኩ ሳይካካዱ ለፍርድ ከሸንጎው የሚደርሱበት መንገድ ሲሆን ይህም ባህል “መቆራኘት” በመባል ይታወቃል፡፡ መቆራኘት ማለት መታሰር ወይም መተሳሰር ማለት ነው፡፡ በአስቼ 1
ባይራ ፊልሙበምስል ጥራት ደረጃ በ፲፻፹/HD/ የተቀረፀ ነው፡፡ የካሜራ እንቅስቃሴው በጠቅላላው ማለት በሚቻል መልኩ ካሜራው ሳይንቀሳቀስ/simple shot/ የተወሰደ ሲሆን ተንቀሳቀሰ ከተባለም ለመግቢያ፣ ገጸ ባህሪያትን ለማስተዋወቅ፣ እና ለመውጫ በብዛት የጎንዮሽ እሽክርክሪት/pan/ ለማሳየት ነው። ይህም በማድረጋቸው ለማቀናበር/edit/ ከመመቸቱም በተጨማሪ ተመልካች በአላስፈላጊ የካሜራ እንቅስቃሴ/shake/ እንዳይረበሽ ያደርጋል። ብሎም የትረካ ስሜትን ስለሚፈጥር ይበልጥ በስሜት ተመልካች የመያዝ አቅምን ይጨምርለታል። በብርሃን/light/ ረገድ ስናየው የውጪ/outdoor/ ቀረጻ ላይ የተፈጥሮ ብርሃንን ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ያም በመሆኑ ከተለመደው የፊልም መልክ/cinematic look/ ጠቆር ያለ አድርጎታል። ይህ ደግሞ ደብዘዝ/fade/ ካለው የቀለም ድመቀት/ color temperature/ ምርጫቸው ጋር ተዳምሮ ምስሉ ላይ የድሮ ፊልም መልክ አይነት ስሜት ሊያመጣላቸው ችሏል። ይህን በማድረጋቸውም በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ የተለመደው የድሮ ጊዜን ለማመልከት በጥቁርና ነጭ እያረጉ የመስራት ልምድን በመቀየር ከነ”የነገን አልወልድም” ፊልም ተርታ ፈር ቀዳጅ የሆነ ፊልም ነው ለማለት ያስደፍራል። የቀለም ድምቀት ምርጫው እራሱ ለተፈጥሯዊው ቀለም የቀረበ በመሆኑ የሚታየው ምስል ለዓይን የማይረብሽ እንዲሆን አድርጎታል። ለቤት ውስጥ/indoor/ ቀረጻው ደግሞ ሰው ሰራሽ ብርሀን/artificial light/ ተጠቅመዋል። የጀርባ መብራቱ/backlight/ “spot light” የምንለውን የመብራት አይነት በመጠቀምና አልፎ አልፎም ከላይ እና ወደ አንድ ጎን በመድረግ ሾልኮ የገባ ብርሃን በማስመሰላቸው የተፈጠረው ምስል የራሱን ውበት ሊፈጥር ችሏል። 2
ባይራ በ ገጽ ቅብ/costume and props/ ደረጃ ስናየው የምስሉ ዋና መሠረት ነውና ከእግርና እጅ ጌጥ ጀምሮ እስከ መናንያን ቆብ ድረስ ጠልቀው በመጨነቃቸው የታሪኩን አንኳር ታሪኮችን በትእይንት ላይ በቀላሉ ለመናገር አስችሏቸዋል። ከ፻ ዓመታት በፊት ይለብሱትም ሆነ ይጠቀሙት ከነበረው ከቆሎ ተማሪ ቁርበትና እራፊ ጨርቅ እስከ ነገስታትና ሹማምንት ብሎም ካህናት አለባበስና የሚጠቀሟቸውን ቁሳቁስ ሳይቀር ምን ይመስል እንደነበር ሊሳዩን ሞክረዋል፡፡ በዘመኑ ምን ሲጠቀሙና እንዴት ሲኖሩ እንደነበር በዚህ ዘመን በቀላሉ ለማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ምን ያህል ጥልቅ ምርምር እንዳረጉ ምስክር ይሆናል፡፡ በተለይ በግሌ መናኒዋን ንግሥታችንን የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱን የመመነን ውሳኔ ከመናንያን ቆብ በላይ ዘውድ ስትደፋ በማሳየት ብቻ ንግሥና ከሃይማኖት ጋር ያለውን ትስስር አያሌ ሃሳቦችን ያዘለና ልዩ ስሜት ያለው አይረሴ ትዕይንት ሳላደንቅ ማለፍ አልፈልግም፡፡ 3
ባይራ በ ታሪክ አንጻር ስንቃኘው የፍቅር ፊልም ዘውግ ሲሆን የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ወደ ፊልሙ መጨረሻው ክፍል በመውሰዳቸው የጡዘቱ/ Climax/ መንስዔ ሆኖ ታሪኩ ሰቅዞ የመያዙ/suspense/ አንዱ ምክንያት ሆኗል ብዬ አስባለሁ። በቋንቋ ረገድ ባህላዊ ጨዋታችንንና እጣነ ሞገርን ጨምሮ ብዙ ቅኔያዊና ግጥማዊ ዘዬ የታጨቀ ነውና ማራኪነቱ ‹ወይ ግሩም› ያሰኛል፡፡ በተጨማሪ ያንዳንዶቹ ንግግሮች/dialogue/ በዛ ዘመን ለችሎት ክርክር ይጠቀሙባቸው በነበሩ ቃላት በጥንቃቄ የተቀነበበ በመሆኑ በጊዜው የነበረውን የአነጋገር ዘይቤ ቀለሙን ሊያገኝ ችሏል። ይህም በመሆኑ ምን ያህል እንደተለፋበትና ምን ያህል የአበው ልሂቃን አሻራ እንዳረፈበት አይቻለሁ። እውነት ለመናገር አፍ የህሊና ማስተንፈሻ ነው እንደሚባለው ይሔን በሚያህል ቅኔያዊና ግጥማዊ ስነቃል በወጥነት ያለመኮለታተፍ ከመናገር አልፎ መከራከር መቻላቸው፣ በእውነት በዘመኑ የሚኖሩ ሰዎች በነገሮች ላይ የነበራቸው የማስተዋል ልህቀትና ስብዕና ብሎም እንደሰው የመብሰል ደረጃ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል እላለሁ። በዛ ላይ በዳይና ተበዳይን የሚያክሉ ሁለት ተቃራኒ ዋልታዎች በአንዲት “መቆራኘት” በምትባል የኩታ መተሳሰር ሃሳብ ብቻ ተዳድረው ሳይጎዳዱ ቀርቶ ጭራሽ እየተደጋገፋና እርስ በእርስ እንክብካቤ እየተሰጣጡ፣ ከፊታቸው የሚያጋጥማቸውን መከራ በጋራ እየተከላከሉ ባስ ሲልም እርስ በእርስ እየተፃለዩ ለቀናት ብሎም ለወራት በጋራ ፍትህ ለማግኘት መጓዛቸው የልብ ገርነታቸውንና የስብዕናቸውን ግዝፈት በጉልህ ያሳያል፡፡ ከፍ ሲልም ፍትህ ለማግኘት የሚሄዱበት እርቀት ምን ያህል እንደሆነና ለፍትሕ ያላቸውን በቃላት የማይገለጽ ክብርና ቀናኢነት ይመሰክራል፡፡ በፍትሕ በኩል ስናየውም በጊዜው ዓለምን ያስደነቀ እና ከተጻፈ ሕግ በተሻለ ለስብእናና ለስሜት በቀረበ የፍትሕ ስርዓት ስንተዳደር እንደነበር ታሪክ በደንብ ይመሰክራል፡፡ እንደው እንደምሳሌ እንውሰድ እንኳን ብንል ታላቁ ንጉስ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በፍርድ ችሎታቸው ምክንያት የፈረስ ስማቸው “አባ ዳኘው” መባሉን አንስተን መጨዋወት እንችላለን፡፡ ካሰኘንም የነገር ብልት ያውቃሉ ተብለው በእንግሊዞችም ሆነ በጣሊያኖች ብሎም በቀናኢ ፈራጂነታቸው በዓለም ትልቅ ዝና ያላቸውን የጦር ሚኒስትሩን ፊትአውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን (አባ መላ) ጠቅሰን፤ ካስፈለገም ሌሎች እማኝ አድርገን ማውራት እንችላለን፡፡ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል እንዲሉ ፊልሙን ስመለከት ካስታወስኳቸው ብዙ ከሚደንቁ የአባ መላ ፍርዶች አንዷን አስደናቂ ፍርድ ብቻ መዝዤ ተርኬ ላብቃ፡፡ 4
ባይራ እንደሚታወሰው እንግሊዞች ኬንያ በእጃቸው ነበረችና በዛ በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ገፍተው መሬት መያዝ ስለሚፈልጉ በግጭት ምክንያት መሬት ለመውረር ምክንያት እየፈጥገሩ ይተነኩሱን ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ሁለት ያልታጠቁ የእንግሊዝ ወታደሮች ያለፈቃድ ገብተው ኖሮ በስህተት በድንበር ጠባቂዎች ይገደላሉ፡፡ የእንግሊዝም ሃገር በቆንጽላው በኩል ከእምዬ ምኒሊክ እልፍኝ አቤቱታውን ያቀርባል፡፡ ጥያቄውም “በሃገራችን ህግ መሰረት ወታደራችን የሞተበት መሬት የእንግሊዝ ይሆናልና የተገደሉበት መሬት ይሰጠን!” ነው፡፡ አፄ ምኒልክም ወይ ወታደሮቹ ይቀጡም ቢሉ አሻፈረኝ ብለው በጥያቄአቸው ይፀናሉ፡፡ ነገሩ የመሬት መቁረስ ጥያቄ እንደሆነ የተረዱት ንጉሱ ትንሽ ካሰቡ በኋላ “ሃብቴ አንተ እየው እስቲ ይህንን ጉዳይ?” ብለው ወደ አባመላ ይመሩታል፡፡ ፊታውራሪም “በእውን በሃገራችሁ ያለው ደንብ እንደሱ ነው?” ሲሏቸው “አዎ” ይላሉ ቆንጽላዎቹ፡፡ ይሄኔ አባ መላ አሰብ ያደርጉና “እንግዲያውስ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዕእለማየሁ እናንተ ሃገር ሄዶ ነው ያረፈውና እናንተም ሎንዶንን ስጡን እና እኛም ይህንን እንሰጣችኋለን፡፡” ብለው ውል አርቅቀው “በሉ ፈርሙ!” ይሏቸዋል፡፡ ይሄኔ እንግሊዞቹ “ልዑል ዓለማየሁ እኮ ታሞ ነው የሞተው፡፡” ብለው ቢመልሱላቸው “እሱን እናንተ አላችሁን እንጂ እኛ ከዚህ በምርኮ ተወስዶ እዛ እንደሞተ ነው ምናውቀው፡፡” ብለው ይመልሱላቸዋል፡፡ ነገሩ ያላማራቸው እንግሊዞችም ታዲያ ውሉን አንፈርምም ብለውና አቤቱታውን አንስተው ይመለሳሉ፡፡ በዚህ ፍርዳቸውም ንግስቲቱና ንጉሱ እጅግ ተደስተው ተነስተው እንደሳሟቸው በታሪክ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በመጨረሻም እንደ መጠቅለያ እኛ ሁላችን የዚህ ዘመን ትውልዶች ብሎም በፍትህ ሙያ ውስጥ ያሉ ወገኖች ከበላ ልበልሃም ሆነ ከኦሮሚያው አባገዳ ስርዓት፣ ከደቡቡም ዱቡሻ፣ ከሃመሩ ዶንዛ ሆነ ከጉራጌውም፣ ከአፋሩም የፍትህ ስርዓትም ሆነ ከሽምግልና ስርዓት እጅግ እጅግ ብዙ እምንማረው ይኖረናል። እናም እንደ “የሚመለከተው አካል” እና “መንግስት” አይነት የአፍ ሸጋታ ቃላት ወጥተንና ታሪክን በበዳይና ተበዳይ መነፅር ከማጥናት አልፈን ታሪካችን ውስጥ በምናገኘው ጥበብ ልክ ብንቃኝ እያልሁ፤ ፊልሙ እጅግ መታየት የሚገባው ነውና ፊልሙንም ማንነታችንንም ብናይ እላለሁ አመሠግናለሁ! (ማስታወሻ:- በዚህ ጽሑፍ ላይ አንዳንድ ሙያዊ ቃላትን ለመተርጎም ተሞክሯል፡፡ ምናልባት የትርጓሜ ግድፈት ካለም ታላቅ ይቅርታ እየጠየኩ ከጎኑ በቅንፍ ዋናው ቃሉ ይገኛል፡፡) ኢትዮጵያዊነት ልባምነት! 5
ባይራ በቃላት መማለል የአፍታ ዳሰሳ ከሃገራችንገጣሚዎች ውስጥ መንፈሱን በአንዳች መቃተት ውስጥ ያሳለፈ የምድርን ጣዕመ ህይወትም እንደ ኢምንት ቆጥሮ እንዳለፈ የሚነገርለት ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ ነው። በእኔ ትንሽ መረዳት የህንዱ ባለቅኔ ራቢንድራናት ታጉር ( Ravindranath Tagore) ተመሳሳይ መማለሎች እንዳሉት ለማየት እንሞክር እስኪ። ከሁሉ አስቀድሞ ግን ስለሁለቱ ባለቅኔዎች ትንሽ ብለን እንጀምረው እንጂ። በውብ አረገ ተማልሎዓዊነት (Mysticism) አንዳች መለኮታዊ ሃይልን ወይም ታላቁን ፈጣሪ በአርምሞና የስጋ ፍላጎቶችን ችላ በማለት ፈጣሪ ዓለማቱን፣መጋቢ ፍጥረታቱን የማሰስ የነፍስ ህቅታ ነው። 1
ባይራ ትውቂያ ባ ለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ ሚያዝያ 1946 ዓ፡ም ተወልዶ ሃምሳ ዓመታትን ከተንከራተተ ብሎም ከተመሰጠ በኋላ በነሐሴ 1996 ዓ፡ም ይህቺን ስጋዊ ዓለም ተሰናበተ። እስካሁን ድረስ የታተሙ “የባለቅኔ ምህላ” እና “የነቢያት ጉባኤ” የተሰኙ የግጥም መድብሎች አሉት። በተለያዩ ግለሰብ እጆች ውስጥ የተጠራቀሙና በግምት ከ1000 በላይ ግጥሞች እንዳሉት ጭምጭምታ ይሰማል።የመጀመሪያ ልጁ የሆነው ሼህ አብዱ ሙሉጌታ (ዳንኤል ሙሉጌታ) እና ስንዱ አበበ የባለቅኔው ብዙ ግጥሞች የትም ተበታትነው እንደቀሩና በአንዳንድ ግለሰቦችም እንደተሰረቁ አልደበቁም። በህይወቱ ላይም የተጻፉ “የባለቅኔው ኑዛዜ” እና “ኢትዮጵያዊነት እምነት” የተሰኙ መጻሕፍት አሉ። በ1991 ዓ፡ም ከፈርጥ መጽሔት ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ደራሲ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ “ፍልስምና ዓራት” በሚሰኝ ቅጹ ውስጥ አጠቃሎታል። ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ) 2
ባይራ ባለቅኔው እጅግ በጣም ብዙ የዘፈን ግጥሞችን ለታዋቂ እና ጀማሪ ድምጻውያን ማበርከቱም አይካድም። ለእነ ጸደንያ ገብረማርቆስ፣ ሃና ሸንቁጤ፣ አበበ ተካ፣ አበበ ብርሃኔ፣ ብጽዓት ስዩም፣ፍቅራዲስ ነቃጥበብ፣ ይሁኔ በላይ፣ ጃን ስዩ ሄኖክና ለሌሎችም ድምጻውያን ያበረከታቸው እልፍ ግጥሞች ዛሬ ድረስ የአድማጭን ስሜት እንደኮረኮሩ ናቸው። ባለቅኔው በዘመኑ ባለው የህይወት አረዳድ እንደ ኢምንት ተቆጥሮ ያለፈ ነበር። ብዙዎቹ እንደሚንቁት፣ ብዕሩን ሊሸቅሉበት እንደሚፈልጉም በህይወት በነበረበት ወቅት ተናግሯል። የሰው ልጅ ቅዱስም ንጉስም ሊሆን ነውና የተፈጠረው እኔም እንዲያ ነኝ ይል ነበር። አዎ ቃሉ እውነት ነው፣ ቅዱስ ነበር! በሰዎች ህያው ልብም ውስጥ ንጉስ ነው የሚሉ ቋሚ ምስክሮች አሁን ድረስ አሉ። በልብ ላይ የሚነግስ ደግሞ መለኮት ነው። ታዲያ የባለቅኔ መስተካከሉ ከመለኮት ሃገር አይደለምን? 3
ባይራ ራቢንድራናት ታጉር ( Ravindranath Tagore) ታላቅ የህንድ ገጣሚ ነው። በተወለደባት ቤንጋል ስሙ ህያው ነው። ከ 1861-1941 እ.አ.አ ለ80 ዓመታት በህይወት ኖሯል። ለመጀመሪያ ጊዜ Gitanjali ተብሎ በተጻፈውና በራሱ በገጣሚው Song of Offerings በሚለው ወደ 106 ግጥሞች በተካተቱበት የግጥም መድብሉ የ 1913 እ.አ.አ የስነ ጽሑፍ ኖብል ሽልማትን (Noble prize in Literature) ወስዷል። በዚህም ግጥም የታላላቅ ገጣሚያንን ቀልብ መሳብ ችሏል። በህይወቱ ከእነ Albert Einstein, Robert frost, Thomas Mann, George Bernard Shaw, H.G Wells ጋር ለመገናኘት ችሏል። በተለይ ከታላቁ የፊዚክስ ሊቅ Albert Einstein ጋር በዘመኑ በነበረው Quantum mechanics ጉዳይ ያደረገው ክርክር አይዘነጋም። ራቢንድራናት ታጉር (Ravindranath Tagore) ታጉር ከ1000 በላይ ግጥሞችን በትውልድ ሃገሩ የአፍ መፍቻ ቋንቋው በ ቤንጋሊ ቋንቋ (Bengali Language) ጽፏል። ወደ 2230 የሙዚቃ ግጥሞችን ደርሷል። ዜማዎችንም አቀናብሯል። ስምንት ታላላቅ ልብ ወለዶችን፣ ስምንት የአጭጭር ልብ ወለድ ስብስቦችን፣ ስድስት ኖቬላዎችን(ቤሳ ልብወለዶችን)፣ ከሁለት ደርዘን በላይ ቴአትሮችን ጽፏል። ሙዚቃዎችን በራሱ ተጫውቷል። በተውኔቶች ላይ አብሮ ተውኗል። ብዙ የፍልስፍና ጽሑፎችን እንዲሁም ዲስኩሮችን አዘጋጅቷል። በአምስቱም አህጉራት ከ30 በላይ ሃገራትን በመዞር ትምህርቶችን ሰጥቷል። ታጉር የባንግላዲሽንና የህንድን ብሔራዊ መዝሙር በማዘጋጀት በአንድ ጊዜ ለሁለት ሃገራት ብሔራዊ መዝሙሮችን ማዘጋጀት የቻለ ብቸኛው ሰው ነው።ላበረከተው የስነጽሑፍ አስተዋጽኦ በ1915 እ.አ.አ ከእንግሊዙ ንጉስ ጆርጅ አራተኛ (King George V) ታላቁን የክብር ሽልማት (Knight ship) ተቀብሏል። ነገር ግን የእንግሊዝ ወታደሮች በህንድ ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊ ግለሰቦች ላይ በፈጸሙት ግድያ ታጉር የተቀበለውን ማዕረግ በ1919 አውርዷል። በወታደሮች ጥቃት ወደ 400 ንጹህ የህንድ ዜጎች ሲገደሉ ከ400 በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለው ነበር ነው። 4
ባይራ የአያ ሙሌናየታጉር ህይወተ ጥበብ ጥቂት የማይባል ተመሳስሎት አለው። የመጀመሪያው ሁለቱም በህይወት የሌሉ ገጣሚዎች መሆናቸው ነው።ሁለተኛው ሁለቱም በዘመናቸው በፖለቲካ ውስጥ የተሳተፉና ከታላላቅ የሃገራቸው ፖለቲከኞች ጋር ግንኑነት ያበጁ መሆናቸው ነው። ታጉር እና ማህተመጋንዲ የቅርብ ጓደኖች ነበሩ። በአንዳንድ ሃገራዊ አረዳዶች ላይ ተቃርኖ ቢኖራቸውም በህንድ ነጻነትና የሰው ልጅ እኩልነት ግን አይደራደሩም ነበር። በህንድ የተደረገውን ጭፍጨፋም አብረው ነበር ያወገዙት። ታጉር ለህንድ ነጻነት የታገለ፣ ከማህተመ ጋንዲ ጋር እኩል ለሃገሩ የተዋደቀ ባለቅኔ ነበር። ሃገሩም ለዚህ ህያው አስተዋጽኦው ክብሯን ከመቸር አልተቆጠበችም። የሃገራችን ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬም ከኢህአዴግ ጋር ግንኙነት ነበረው። ።”የምደግፈውም የምቃወመውም ኢህአዴግን ነው” ይል ነበር። “ሲያጠፉም አልለቃቸውም!” ማለቱን በአካል የሚያውቁት አጫውተውናል። በተለይ ከበረከት ስምኦን ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበራቸው። እንዲያውም ከበረከት ስምኦን ጋር የሚገርም ገጠመኝ አላቸው። አያ ሙሌ እንደ የኔ ቢጤ ወደ ጎዳና ሲወጣ ሴት ልጁ 10 ዓመቷ ነበር አሉ። በረከትም የእውቀት አድናቂ ነው ይላሉ። ታዲያ የአያ ሙሌን ወደ ጎዳና እየወጡ ሲንከራተቱ መዋል አልፈለገውም። ሁሌ ወደ ጎዳና እየሄደ ተመለስ ወደ ስራህ ይለው ነበር። ታዲያ አንድ ቀን በረከት አያ ሙሌን ለማሳመን እንዲህ ይለዋል። “ህጻን ልጅህ እንኳን አታሳዝንህም? ትንሽ ልጅ ያለ አሳዳጊ ትተህ መውጣትህ ደግም አይደል” ይለዋል። “ትንሽ ልጅ እኮ አይደለችም። አንተን አንድ ዓመት ትበልጥሃለች።”ብሎ መለሰለት አሉ። ለምን እንዲህ እንዳለው እስካሁን ግልጽ ባይሆንም ቅሉ። ሁለቱም መንፈሳዊያን ናቸው። አያ ሙሌ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ነበር። ብዙ ግጥሞች ላይ የዚህ ጫና ይታይበታል። ሁሉንም ሃይማኖቶች ለማወቅ እንደሞከረ ራሱም አልካደም። በሚስጥረ ስጋዌ፣ በሚስጥረ ድኅነት እንዲሁም በነገረ መስቀሉ ላይ ትልቅ ተማልሎ ነበረው። ለዚህም እንዲህ ሲል ነገረ ክርስቶስን ይቀኝበታል። ተማልሎ ወ ተመሳስሎ 5
ባይራ “ቃል” ካስራ ሁለት ዓመት በላይ ያለን ነገር ፍቅርና ወሲብ የራሱን ይናገር ሌላው ሳይጋገር ውበት ሻተኝና ጦም ጀመርሁ እንደ ቀልድ ጉልበት እንዳያንሰኝ ሰገድሁ እኔን ልወልድ ለካስ በጸሎት ውስጥ ቃል ኖሯል አበ ወልድ። በሌላ ቦታ ላይም “ቃል ሆኖ ተፈጥሮ ቃል ሆኖ ሞት ሽሮ የዘላለም ንጉስ በቃል ተሞሽሮ ቃልማ ፊርማ ነው የሰለሞን ማህተም እንደጉም ደመና እንዳሻው የሚተም”………………. እያለ የቃልን ነገር፣ የአምላክን ሰው መሆን፣ የክርስቶስን ህይወት ሰጪነትና ሚስጥር በተመስጦ ይፈክራል። 6
ባይራ በ ዚያ በኩል ታጉር ደግሞ በባክህቲ (Bhakti) እምነት ወይም ባህል ላይ ተመስርቶ ፈጣሪ ዓለማት ብሎ የሚያምነውን ይለማመናል። Misha Kandhari እንዲህ ትላለች ስለ ጊታንጃሊ የግጥም መድብሉ። “Gitanjali are the reminiscent of a great Indian tradition called the Bhakti tradition.” በሰባተኛው ክፍለዘመን እንደተስፋፋ ይነገራል ይህ የባክህቲ እምነት። በውስጡም ሁለት ዘርፎች አሉት። አንደኛው Nirguna bhakti ሲባል ሌላኛው ደግሞ Saguna Bhakti። ታጉር ይከተለዋል ተብሎ የሚታሰበው Nirguna bhakti አምላክ “ቅርጽ የለሽና” በውስጣችን ያለ አንዳች ሃይል ነው ብለው ያምናሉ። በፍቅርና ራስን አሳልፎ በመስጠት ውስጥ ይሄን ህያውና በጽንፈዓለሙ የሞላውን አምላክ ማገልገል እንደሚቻልም አምነው ይተገብሩታል። የገጣሚያንና የሙዚቃ ተልዕኮም ይሄን ሃይል ማገልገል ነው ትላለች ሚሻ። (Nirguna bhakti, God or the supreme power was a formless energy or force that had to be deeply felt and realized. These poets spoke of everyday activities as a service to God. They believed in love and surrender and in universal religion. 7
ባይራ አንተ ብቻ “Only you“የሚል ርዕስ ባለው ቅኔው ታጉር አንተ ብቻ ነህ ሁሉ ነገሬ ይለዋል። ምን አይነት መሰጠት ነው? ምን አይነት ራስን አሳልፎ እንደ አምሃ ማቅረብ ነው? ምን አይነት የጽንፈዓለሙን ቡጥ መሻት ነው? T hat I want thee, only thee—- let my heart repeat without end. All desires that distract me, day and night, are false and empty to the core. As the night keeps hidden in its gloom the petition for light, even thus in the depth of my unconsciousness rings the cry —-`I want thee, only thee’. ሌላው የዚህ የተማልሎአቸው መገለጫ ደግሞ አምላካቸውን ለመንካት የሚያደርጉት መንጠራራት ነው። የባለቅኔ ከፍታው ከመለኮት መተካከል ነው ቢሉ ማጋነን አይሆንም። ሰብአዓለሙንና ፍጥረታቱን በሙሉ የሚያንቀሳቅሰውን ሃይል ለመጎናጸፍ ስጋን ማጎስቆል የሁለቱም ባለቅኔዎች መንገድ ይመስላል። ለዚህም ነው አያ ሙሌ ነገር ዓለሙን ሁሉ ትቶ እንደማንም በመንከራተት ያሳለፈው። ከአለቤ ሾው ቀርቦም ሳይበላ፣ ሳይጠጣ፣ ወሲብ ሳያደርግ መኖር እንደሚመኝ በአንደበቱ መስክሯል። ግጥሞቹም ያንን ያሳያሉ። ስጋውን ክዶ በመንፈሱ ከመለኮት ለመደራረስ በሚያደርገው ህቅታ ውስጥ የሚከተሉትን የጭንቅ ቃላት አውርዷል። የባለቅኔው ምህላ በሚል የራሱን ህይወት አዙሮ በፈከረበት ግጥሙ ያሉትን ስንኞች ለአፍታ መመልከት እንችላለን። 8
ባይራ “የማይሰፈር ስለካ፣ ከማይቀመስ ስፎካከር እሰጥ አገባ ስጎሰጥ፣ ጉንጭ አልፋ ስከራከር እየመሸ እየነጋብኝ፣ ዓይኔ እያየ ዘጋብኝ። ችዬ አልችልም ብቻዬን፣ አልጸናም ባንድራሴ ድሃ አደግ ምን ቢተባ ፣ አይደምቅም እንደ እንደራሴ በእምርታህ በይቅርታህ ማርከኝ፣ እንደ እዝነትህ እንደ ቸርነትህ ባርከኝ ኤሎሄ ኢላሄ፣ ምሉዕ በኩለሄ ዕለተ ሞቴን አታስረሳኝ፣ ወንፊት እንጂ እንባ አትንሳኝ’።……………………. እያሉ የሚዘንቡት የቃላት ቆሎዎች የከያኒውን መንፈስ ፍትጊያ የሚያሳዩ መማለሎች ናቸው። ከህይወቱ ባሻገር ሞቱን እንዳያስረሳው ይለማመናል። እንደ ደቹ impressionist ሰዓሊ ቪንሰንት ቫን ጎህ (Vincent van Gogh) What is certainly true in this reasoning is that while we are alive we cannot go to a star, any more than, once dead, we could catch a train እያለ ሞትን የሚለማመን ይመስላል። ሌላው የመንፈስ ተንከራታችና ባለቅኔ ታጉርም “Give Me Strength” በሚለው ግጥሙ እንዲህ ይቃትታል። ብርታቱን፣ ጉልበቱን አምጣ ይለዋል። አንተን የምወድበት፣ ከልቤ ሰሌዳ ላይ አይጨበጤ ማንነትህን አውለው ዘንድ ጥንካሬውን ስጠኝ ይለዋል። ከዕለታት መነከላዎስ ባሻገር እመለከት ዘንድ ና ወደ እኔና ጉልበትህን አስርጽብኝ ይለዋል። Give me the strength to make my love fruitful in service. Give me the strength never to disown the poor or bend my knees before insolent might. Give me the strength to raise my mind high above daily trifles. And give me the strength to surrender my strength to thy will with love. በምድር ላይ የሚያደርገውን አሰልቺ ህይወት ይታዘበዋል። አያ ሙሌ የስጋን ጉልበት ሊሽር፣ የኑሮን ቀዳዳ ሊሸነቁር ከመለኮት ቤት እንግዳ ሆኖ ሊታደም አንድ በለኝ እያለ ይጎተጉተዋል። በእውነት መንገድ ምራኝ፣ የብርሃናትን መስኮት አመላክተኝ ይለዋል። ብርሃን አይጨበጥም። ብርሃን አይመረመርም። ታዲያ ታላቁን ብርሃናማ መንገድ መሻት የባለቅኔ እጣ ፋንታ አይደለምን? አንድዬ! 9
ባይራ ቤት ለእንግዳ በለኝ፣ በእመ አምላክ ቤት ለእምቦሳ እንድል፣ በምስራቅ በር ከጥሬ ዱለት አላለፈም የእኔ ያልሁት ምላስ ሰንበር………………… ታጉር Strong Mercy በሚል ልመናው ይቅርታውን፣ እምርታውን ያላብሰው ዘንድ ያን የፍቅር አምላክ በፍርሃት ይለማመነዋል። ወሰራ ዶሮ ሳያርድ፣ ከዛፍ ስር ወድቆ እየተነሳ ሳያለቅስ እንዲሁ በቃላትና በዜማ የምህረትን ዣት ይጠብቃል። My desires are many and my cry is pitiful, but ever didst thou save me by hard refusals; and this strong mercy has been wrought into my life through and through. ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ አስምአኒ በሚለው የጸሎትና የምህላ ግጥሙ እንዲህ እያለ ይቃትታል። አስምአኒ! ከጌታ ሰማኒ፣ ህያዊት--ለባዊት ነባቢት፣ ነፍሴ ጋር አስታርቀኝ እኔም ጠፍቼ እንዳልባክን፣ አንተም እንዳትርቀኝ አንተ ብቻ በውስጤ ከብረህ፣ ስላንተ ብቻ እንድመሰክር ላክልኝ ጰራቅሊጦስን፣ በመንፈስ ቅዱስ እንድሰክር…………. እንዲህ እያሉ የሚወርዱ የሁለቱ ባለቅኔዎች መማለል በአንክሮ ለተመለከተ አንዳች መመሳሰልና መሳሳብ እንዳለባቸው ያመላክታሉ። እንደ መሰብሰቢያ ሃ ሳባችንን ስንሰበስበው አያ ሙሌና ታጉር አምላካችን ከሚሉት አካል ላይ ሆነው ጽንፈዓለሙን የሚጋተሩ ባለቅኔዎች ነበሩ። ከዚህ ውጪ ሌላ ሃሳብ አልነበራቸውም ማለት አይደለም። ግን ነፍሳቸውን ለአንዳች ሃይል ለማድረስ የሚሳቡ የጥበብ ፈርጦች እንጂ። በእርግጥ ለታጉር ይሄ መንፈሳዊነቱ የተጫናቸው ግጥሞች የኋላ ኋላ ትችትን አምጥተውበታል። ታላቁ አየርላንዳዊው ገጣሚ፣ ጸሐፊ ተውኔትና ፖለቲከኛ ዊሊያም በትለር የትስ (William Butler Yeats 1865–1939) የቀድሞ ውዳሴውንና አድናቆቱን ረስቶ ብዕሩን ሲያስነሳበት ጥቂት ዓመታት ነው የፈጁበት። እንደሚታወቀው የጊታንጃሊ የግጥም ስብስቦችን መግቢያ የጻፈለት ይሄው የትስ ነበርና ነው። ለዚህ ወቀሳው ደግሞ መነሻው “ብዙ ግጥሞች ህግጋተ ግጥምን ያልተከተሉ ዝርው ስንኞች ሆነው ሳለ ሃሳቡ ከአንድ ሃይማኖታዊ ጉዳይ አልወጣም” የሚል ነበር። 10
ባይራ እነዚህን መንፈሳዊ መመሰጥ ወይም ተማልሎ የተጫናቸውን ግጥሞች ለመረዳት አንድም መንፈሳዊነትን ልምምድ ማድረግ ይጠይቃል። የአንድ ቤተ እምነት ምሰሶዎችና ዲበ አካላዊ (metaphysics) የህይወት፣ ሞትና ዘለዓለማዊነት ትርጓሜዎች ማዎቅ ግድ ይላል። ከእነዚህ መሰረቶች ውጭ ሆነን ስናያቸው ግጥማቸው ከአንዳች ልመናና የሃሳብ ድረታ የተሻገረ እውነት እንደያዙ ለመረዳት እንቸገራለን። የአያ ሙሌ ግጥሞችም ሆኑ የታጉር ቅኔዎች መዳረሻቸው የሰውን ህይወትና አኗኗር ማሰስ ነው። በዚህ ማሰስ ላይ አንዳች ልዕለ ፍጡር ይመራናል ብለው ያስባሉ። እናም ስጋዊ ፍላጎታቸውን ወደ መሸሽ ያዘግማሉ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም አያ ሙሌ ልጅና ትዳሩን በትኖ ወደ ጎዳና የዘመተው። በአንድ ወቅት ግጥም ለመጻፍ ምን ያስፈልጋል? ተብሎ አልቤ ሾው ላይ ሲጠየቅ የመለሰው መልስ አንድና አንድ ነው። እንባ!የሚል ነበር። “ካለቀሰው ጋር ስታለቅስ፣ እርቦ ነጠላ ለብሶ፣ ንጣይ እንጀራ ቀምሶ ከሚውለው ጋር አብረህ ሆነህ ህመሙን ስትረዳው ገጣሚ መሆን አይከብድህም” ይላል። በሌላ ቦታም “ግጥም ለመጻፍ ስትሞክር ብዕርና ወረቀትህን ይዘህ ወደ ቀራንዮ ተመልከት። ወልድ ራሱ ይጽፈዋል “ብሎ እንደነገረው እንዳለጌታ ከበደ (Ph.D) ሲናገር መስማቱን የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ምስክር ነው። ከዚህ የምንረዳው ህይወት በአንዳች ህመም የምታልፍ ከንቱ መብሰክሰክ ናትና በዚህ መቃተት ውስጥ የሰውን ህመም መፈከር የከያኒ አይነተኛ መሳሪያ ነው ማለት ነው። በዚያው በሃምሌ 1992 ከፈርጥ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ እንዲህ የሚል ሃሳብ አክሏል። “ገጣሚ የሚለውን የሚሰማ መንግስት ብቻ ነዉ በትክክል ማስተዳደር የሚችለዉ። ሰው የሆነ ገጣሚ ካገኜ ነው ታዲያ። መጀመሪያ ገጣሚው ሰው መሆን አለበት። Because the poet is the people ግን he is the people. Because he is the language. Has the best access to many members of the society better than anybody else. አሪፍ አሪፍ wayዎች ካሉ ልናመላክታቸው እንችላለን።” ይላል ቃል በቃል። ይሄ ነው ባለቅኔ ማለት። በመቃተትና በአንዳች መማለል ውስጥ ሆኖ ሰው የሚባለውን ግዙፍ ፍጡር እንደ አርማ የሚያውለበልብ። በእነዚህ በሁለቱ ገጣሚዎች ውስጥ ያለው መማለል መጨረሻው የሰው ልጅና መለኮት ነው። ነገር ግን እንዲህ አይነት ገጣሚዎችን ሳንረዳቸው ያልፋሉ። ትክክለኛ ገጣሚዎች መለኮት የሚልካቸው ሃዋርያቶቹ ናቸው። እነሱን የሚሰማ ህዝብና ዓለም ይድናል። በብላሽ የሚያያቸውን ግን ታዝበውት ያልፋሉ። በተለይ በዚህ ሸቀጤ ማህበረሰብ (consumer society) ከስጋ እየሸሹ ወደ ሰው ልጅ ልብ እየጠለቁ የሚማልሉ ገጣሚዎች ተደማጭነታቸው ምንም ነው። ለዚህ አይደል አያ ሙሌ እኒያን ሁሉ ቅኔዎች አንዝቦልን ከአንዳች ብናኝ ካፊያ እኩል የምናየው። በመጨረሻም በ Misha Kandhari አባባል ሃሳባችንን እንዝጋ። “When material interests dominate the life of the people the poet is generally undervalued. He is apt or be regard as an unpractical, or even an eccentric and valueless member of the society” ባለቅኔን የሚያዳምጥ እዝነ ልብ ያድለን እያልን የተማልሎ ዳሰሳችንን አበቃን። 11
ባይራ ዶርዜ --- ሳሮ ሁላችንም በየራሳችን ቀለም ስንሰባሰብ ሀገር ትደምቃለች! “ሳሮ” ይላል ዶርዜ“..ሰላም ፣እንዴት ናችሁ ፣ጤናችሁ እንዴት ነው “እነዚህን ሁሉ ትርጓሜ የያዘ ቀለል ያለ ግን ብዙ መልዕክት ያለው ቃል ነው። እኔም “ሳሮ” ብዬ ጽሑፌን እጀምራለሁ። እንደ ሀገር ብዙ ያልተነኩ ፣ያልታወቁ ፣ያልተዳሰሱ ባህሎች ፣ወጎች ፣እሴቶች ባለቤት ነን :: እሰይ!ተመስገን ነው።ማወቅ ግዴታችንም ነው ።ሌላ ምን እንላለን ማለት የፈለግነውን እያየን እንጨምራለን ። እንግዲህ “ሳሮ” ወደሚላችሁ፣በደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ሚገኘው፣የሽመና ጥበብ ባለሟል ወደሆነው የዶርዜ ማህበረሰብ ዘንድ በሥነ-ጹሑፍ ሀዲድ አብረን እንጓዝ ዘንድ ወደድሁ ። አማልክቱ ከኛ ጋር ይሁኑ። በወልደሐዋርያት ዘነበ 1
ባይራ ዶርዜ !! የ ስሙ ትርጓሜ ‘’የተመረጠ’’’ እንደማለት ነው። ሐይማኖት ላይ ያለው ቀናኢነት ከእስራኤላዊያን ጋር ያመሳስለዋል። በመላው ኢትዮጵያ የሚገኘው የዶርዜ ህዝብ ብዛት ከ150,000 በላይ እንደሚሆን ይገመታል። በአፄ ምኒልክ ዘመን ንጉሡ የዕደ ጥበብ ስራ የሚሰሩ ሸማኔ ዶርዜዎች እንዳሉ ሲነገራቸው መጥተው አዲስ አበባ ላይ (ሽሮ-ሜዳ) ይከትሙ ዘንድ እንዲሁም ወደ ሰሜኑ ክፍል ሔደው ሽመና ያስተምሩ ዘንድ አዘው እንደነበረ ይነገራል። በዶርዜ ከ13 በላይ ቀበሌያት እንደሚገኙ ይነገራል ። አከባቢው በሽመና ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሙያ ዘርፎችም የምሁራን መፍለቂያ ፣የጠቢባን መገኛ ነው ። “ሽመናን ያለ ዶርዜ ማሰብ፣ ንጉስን ያለ መንበር እንደማሰብ ነው” እላለሁ። ሽመና ለመጀመሪያ ጊዜ መሸመን የተጀመረው ከዛሬ “500”ዓመታት በፊት በ1590ዎቹ በዶርዜ “ሂርጶ” ቀበሌ ላይ እንደ ሆነ ይነገራል ። በጊዜው የዶርዜ ማህበረሰብ በሽመና ጥበብ የላቀ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።በዚህም የተነሳ የደቡብ ህዝቦች ለንጉሡ የሚያስገቡት ግብር “’ቡሉኮ”’ ነበር። ቡሉኮ ማለት የሽመና አንዱ ምርት ነው !!!... 2
ባይራ ስለ ዶርዜ ማህበረሰብ ጥቂት እውነታዎች በኢትዮጵያ ብቸኛው ዕለተ ሰኞ ስራ የማይሰራ ህዝብ ዶርዜ ነው። ለምን ቢሉ ቅዳሜ ና እሁድ ላይ በጨዋታም ይሁን በስህተት የተጣላ ቢኖር ሰኞ ነው የሚታረቀው። በዚህም የተነሳ ዕለተ ሰኞን ‘የማርያም ቀን’ ይሏታል።(እዛ ጥቁር ሰኞ የሚባል የለም ሃሃሃ) አዲስ አበባን ‘ቱንጋ’ ብለው ይጠራሉ።(ደማቅ ከሚለው ቃል ጋር ይቀራረባል) ከ800 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የዶርዜ ኤሊ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መገኛ ናት። ከአክሱም ማርያም ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ተመስርቷል ተብሎ የሚነገርለት ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መገኛም ጭምር ናት። የዶርዜ ማህበረሰብ አዘውትሮ የሚለብሰው የሽመና ውጤት የሆነውን ድንጉዛ ነው።በደስታውም በሀዘኑም ቀን ይህን ልብስ ይለብሰዋል።አብዝቶ ይወደዋል ከሌሎች አልባሳት ለየት ባለ መልኩ።ድንጉዛን በፎጣ ፣በቀሚስ ፣በሱሪ ፣በሽርጥ መልክ እያደረገ ይለብሳል። ”ድንጉዛ ምንድነው ? የትስ ተጀመረ ? ማንስ ጀመረው ?” ለሚሉ ጥያቄዎች ይሄው መልሱ:- 3
ባይራ “ድንጉዛ” ታሪካዊ አመጣጥ ድንጉዛ ለመጀመሪያ ግዜ የተፈጠረበት ቦታ “ምንድቄ “ይባላል። የድንጉዛ መገኛ ሚንድቄ! በሀገራችን ኢትዮጵያ ለብሔር ብሔረሰቦች መለያ የሆነው የባህል ልብስ የ“ድንጉዛ” ስራ በዶርዜ ሂርጶ ተወላጆች አማካኝነት ከ 300 ዓመታት በፊት መሸመን መጀመሩን አባቶቻችን በአፈ ታሪክ ይናገራሉ ። ታሪክ ሲቆይ አፈታሪክ ይሆናል እያለ እያለ ተረት ይሆናል ! ድንጉዛ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዶርዜ ታላላቆች ማለትም “ለአለቃ ፣ለካዎ፣ዳና ፣ቄስ ፣ደሙሳ መለያ እንዲሆን በሚል የሂርጶ ፓንጎ ተወላጅ አባቶቻችን ከአዕምሯቸው አመንጭተው ፈጥረዋል ።እነኚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ስሞች የማዕረግ ስሞች ናቸው። “ፊትአውራሪ ፣ቀኝአዝማች” ወዘተ እንደማለት ! በጦር ሜዳ ስራ ብቻ አይደለም እነኚህ ማዕረጎች የሚሰጡት ለየት የሚያደርገው እርሱ ነው ! የጥለት አጣጣሉም የራሱ የሆነ ታሪካዊ አመጣጥና ትርጉም አለው። የድንጉዛ ባህላዊ ልብስ ዋነኛ ቀለሞች ሶስት አይነት ሲሆኑ 4
ባይራ እነርሱም:- ቢጫ ፣ቀይ እና ጥቁር ናቸው። ቢጫው ፦ የዶርዜ ሚንደቄ የተባለው የዱቡሻው አጥር ምሳሌ ነው ቀዩ ፦በሚንድቄ “ለፍርድ ፣እርቅ ፣ለስብሰባ ፣ለምክክር ፣ለውይይት እና ለንግሥና የሚቀመጡ የዶርዜ ታላላቆች ማለትም የአለቃ ፣የካኦ የደሙሳ ፣የዳና እና እድሜ ጠገብ አዛውንት አባቶቻችን ምሳሌ ነው ። ጥቁር ፦”ሂርጶ ማጫራ ማጎ”ህዝቡ ለደስታ እና ለሀዘን በጋራ የሚጠቀምበት አደባባይ ትልቅ ሜዳ ምሳሌ ነው ። 5
ባይራ አባቶቻችን እንደሚሉት ቀለማቱ በዘመናዊ መልክ ከመዘጋታቸው በፊት:- 1.ቢጫውን ፦ከተለያዩ ተክሎች በመጭመቅ (በተለይ ጋላሎ ከሚባል ተክል እንጨት ) 2.ጥቁሩን ፦ከሰል ፈጭቶ በመበጥበጥ 3.ቀዩን ፦ ከእንስሳት ደም ያዘጋጁት እንደነበር ይገለፃል። ቢጫው- አጥር ቀዩ- ታላላቆች ጥቁሩ- ሃዘንና ደስታ አሰራሩ ደግሞ ከመሃል ጥቁሩ አለ። ከጥቁሩ አንዳንድ ቦታ ትርፍ ትርፍ እየሆኑ የወጡ አሉ። ያንን ክፍተት ደግሞ በቢጫው ይሞሉታል። ቢጫው የሚጎድለውንም ቀዩ ይሞላዋል። ቀዩ ግን በአንድ ጎኑ ቀጥ ያለ መስመር ይሰራል። ይተርጎም ቢባል እንዲህ ሊሆን ይችላል:- ጥቁሩ መደብ ሰፊው የዶርዜን ማህበረሰብ ይወክላል።ሃዘኑም ደስታውም በዚያ አለ። እንደ ጸብ አልያም አለመግባባት ያሉ ነገሮች ሲፈጠሩ ወደ ሚንደቄ ማቅናት ግድ እንደሚል ያሳያል። እንደዚያም ሆኖ ስምምነቱ ላይመጣ ይችላል አንዳንዴ። ይሄ ክፍተት ታድያ በሃገሪቱ ባለ አዋቂ፣ መምህር፣ ሽማግሌ ይሞ’ላል። የቀዩ መደብ በአንድ በኩል ወጣ ገባ የለውም። የዙሩም መደምደሚያ ነው። ከሽማግሌዎችና ከሃገር አዋቂዎች የሚሻገር ጸብም ሆነ ደስታ እንደሌለ ያመለክታል። 6
ባይራ ለቅሶ በሀገራችን በሁሉም አካበቢዎች ዘንድ ራሱን የቻለ የለቅሶ አካሄድ ስርአት አለ ። በዶርዜ ማህበረሰብ ዘንድ ‘ለየት ካሉ ቋሚ ስርዓቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የለቅሶ ስርዓት ነው ።ይህ የለቅሶ ስርዓት ከሌሎች የሀገራችን አከባቢዎች ምን ለየት ያደርገዋል ? የዶርዜ የለቅሶ ስርዓት “ባሌ“ተብሎ ይጠራል ።ባሌ ሁሉንም ጠቅልሎ የያዘ ቃል ነው። በባሌ ስርዓት ብዙ የሚካሄዱ ሁነቶች አሉ ። ዳንስ ፣የህብረት ዜማ ፣ሙዚቃ ፣የመጠጥ አይነት ፣የምግብ አይነት ፣የትርኢቱ ስፍራ ፣አለባበስ ፣አለቃቀስ ፣ እነዚህን እና መሰል ትርኢቶችን አጠቃሎ የያዘ ነው ።” ባሌ “ቃሉ ዶርዚኛ ሲሆን ማልቀስ ወይም የአልቃሽ ስብስብ እንደ ማለት ነው። ይህ ስርዓት ለሁሉም የዶርዜ ማህበረሰብ ክፍል ያለ መድሎ እኩል ይደረጋል ። የባሌ ስነ-ስርዓት የማይካሄደው ሟች በገበያ ቀን ና ሰኞ ዕለት ሲሞት ብቻ ነው ።ዕለተ ሰኞ እንደነገርኳችሁ የማርያም ቀን ተብሎ የተሰየመ ዕለት ነው።በዚያን ቀን የሚካሄደው የዕርቅ ስርዓት ብቻ ስለሆነ ወደ አመሻሽ አከባቢ የባሌ ስርዓት እንዲካሄድ ይደረጋል። 7
ባይራ ሌላኛው የገበያ ቀን ነው ። በዶርዜ ህዘብ ዘንድ በገበያ ቀን የትኛውም አይነት የለቅሶ ስርዓት እንዲካሄድ አይፈቀድም። ይህም የሆነው ህዝቡ በገበያ ቀን ያለ የሌለውን አቅም አሟጦ ስለሚነግድ የህዝቡ ኢኮኖሚ እንዳይዋዥቅ ፣እንዳይቀዘቅዝ ፣ታስቦ ነው ።ለቅሶ ስርዓት ከተጀመረ በለቅሶ ላይ ከመታደም ውጭ ሌላ ነገር ማድረግ ስለማይፈቀድ ንብረታቸው ለአደጋ ተጋላጭ ስለሚሆንም ጭምር ነው። ቅድሚያ ሟችን እንቅበር የሚል አይነት አመለካከት በማህበረሰቡ ዘንድ አለ። ባሌን የሟች ዘመዶች ሜዳማ በሆነ ስፍራ ላይ በሩጫ ያስጀምሩታል።የሟችን ቤተሰብ ተከትለው የቅርብ ጓደኛ የሆኑ ሰዎች እየሮጡ በመያዝ ያስተዛዝናሉ። ሩጫው የሚሮ’ጠው ሟች እኛን ጥሎ ሄደ ፣አመለጠን የሚል መንፈስ ለመፍጠር ነው ።የቅርብ ጓደኛ ሮጦ ካልያዘ ሩጫው ይቀጥላል። ለቅሶ ከሶስተኛ ቀን በኋላ ካልሆነ ቤት ውስጥ ተካሂዶ አያውቅም። የሚካሄደው ሜዳ ፣ገበያ ላይ ነው።የባሌ መርሀ-ግብሩን በነፃነት ለማካሄድ ቤት ውስጥ አመቺ ስላልሆነ ብሎም በዶርዜ አከባቢ ለቅሶ መኖሩ ከታወቀ ሁሉም ነዋሪ ይደርሳል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። በዚህም ምክንያት ስርአቱ ሰፊ ቦታን ስለሚፈልግ ሜዳ ላይ መደረጉ የግድ ነው። ለቅሶው ያማረ እንዲሆን የሟች ቤተሰብ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።አንድ የዶርዜ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ “የለቅሶ ስርዓቴ ያማረ ይሆን ዘንድ...” ብሎ በማሰብ የቅርብ ዘመዶቹ ጋር ሳንቲም ይቆጥባል ።ሁሉም እርስ በእርሳቸው ተቀማጭ ገንዘብ ይይዛሉ።ያ የሚቀመጠው ገንዘብ ለቀስተኛው የሚጋበዝበት ነው :: በዕለቱ የሚደረጉ የሚወጡ ወጪዎችን በጠቅላላ የሟች ቤተሰብ ይሸፍናል። ምግብ ፣መጠጥ ፣ ሌላው በእድሜ ጠና ያሉ ወይንም ሊሞቱ ጣር ላይ ያሉ ግለሰቦች የተወሰኑ ሰዎችን በቤተሰቡ አማካኝነት ወደ ቤታቸው በመጥራት የተለያዩ የእንስሳት አይነት በማረድ ሰዎችን ያበላሉ ያጠጣሉ ። ቀብድ መሆኑ ነው። የኔ ለቅሶ ቀን በደምብ አድርገህ አልቅስ !! ከቀብር በፊት የሟች ቤተሰብበች የሟች የቅርብ ጓደኛ በሆኑ ሰዎች አንድ በአንድ እየተጠሩ ምግብ ፣መጠጥ ይጋበዛሉ። ሟች ወጣት ላጤ ከሆነ እንዲህ ብሎ ህዝቡ እየዘፈነ ፣እየጨፈረ ወደ ቀብር ስፍራ ይጓዛል:- አቤባ ፣ናይቼክ አቤባ (አበባ ነው ልጁ፤በቅርቡ ያብባል ተብሎ ደረቀ ) ናይቼክ ሜቂሬስ ፣ናይቼ ሜቂሬስ (ልጁ ተሰበረ፤ ከሚሄድበት መንገድ ተሰበረ ፤ተቋረጠ ) ጱጱሌክ ናይቼ ፣ናይቼ ጱጱሌክ (ልጁ እንቁላል ነው በቅርቡ ተሰበረ፤ ተቀጨ ) ሟቿ ሴት ልጅ ስትሆን ደግሞ:- ናያ ሚችዙ ፣ናያ ሚችዙ (ሟች ታሳዝነናለች ፣ሟች አሳዛኝ ነች ) ሎሊዙ ናያ ሎሊዙ ፣(ታምራለች፤ ሟች ቆንጆ ነች ) ባለትዳር የልጆች እናት ፣አባት ሲሞቱ:- ሀዲርሳ ኦጌ ፣ሀሆ የሊሪ ዬጎ ፣ሜቶ (የግራ መንገድ ረዥም ነው፤ ወልዶ ጥሎ መሄድ ችግር ነው ፤ማንስ ሊያሳደግ እንዴትስ ሊያድጉ ነው?) እየተባለ ሴቶቹ አንሶላ በመልበስ ጭናቸው ስር ልብስ ወትፈው እንደ ከበሮ እየተጠቀሙበት፣ እየዘለሉ ፣እየጨፈሩ ወደ ቀብር ስፍራ ይጓዛሉ ። ወንዶች ቡሉኮ ለብሰው ፣ጦር በመያዝ እየጨፈሩ ፣እየዘለሉ ሽለላ እና ቀረርቶ እያሰሙ ይጓዛሉ ። ከቀብር በኋላ ማልቀስ አይፈቀድም።ወደ ሟች ቤተሰብ ቤት ተሂዶ አይዞን ፣በርታ ከማለት ውጪ ማልቀስ አይቻልም ። 8
ባይራ መስቀል (ዮዮ ማስቀላ) ዮዮዮ ዶርዜ ማስቃላ!! አከባበር .. ዮ ማስቃላ ዮ ኡፋይሳ (ደስታ) 9
ባይራ በዶርዜባህል የመስቀል በዓል ዝግጅት የሚጀምረው ከ ነሐሴ 16 ጀምሮ ነው።እስከ ጥቅምት አምስትም ይቆያል ። በእነዚህ ቀናቶች ማህበረሰቡ ልዩ በሆነ መንገድ ሰላምታ ይሰጣጣል ።ከጓደኞቻቸው ጋር ሲገናኙ እየዘለሉ ፣እየጨፈሩ “ዮዮዮ” ይባባላሉ ።ሴት ፣ወንድ፣እናት፣አዛውንት ፣ህፃናት ሁሉም እርስ በእርስ ሲገናኙ ዮዮዮ እያሉ ሰላምታ ይሰጣጣሉ።የመስቀል በዓል በዶርዜ ብሄረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓል ነው።በመስቀል በዓል ወቅት ያላገቡ ልጃገረዶች በየምሽቱ ወደ አደባባይ በመውጣት እየዘፈኑ ፣ይጨፍራሉ። ሴት ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ አደባባይ ወጥታ እንድትጨፍር ፣ከቤት ውጭ ከጓደኞቿ ጋር እንድታድር የሚፈቀድላት መስቀል ወቅት ላይ ብቻ ነው።በመስቀል ወቅት አከባቢ ትዳር የመሰረቱ አዲስ ሙሽሮች በተለምዶ አጠራር “ዎዞ” የሚባል የፀጉር አሰራር አይነት ተሰርተው ፀጉራቸው ላይ በትልቁ ለጋ ቂቤ ይቀባሉ። “ጎዝዳ”የሚባል ጨሌ መሳይ ጌጥ አንገታቸው ላይ በማድረግ ከነጭ ነጠላ የተሰራ ቀሚስ መሳይ ልብሳቸውን ለብሰው በዶርዜ ማህበረሰብ ዘንድ ስመ ገናና እና ታዋቂ ወደሆነው “ቦዶ” ገበያ ይወርዳሉ።ገበያው ከተራራው ስር በሚገኝ ወለል ያለ ሜዳ ላይ ይገኛል ።የራስ ቅሏን ቅቤ መቀባቷ የባሏን ጎሳ መቀበሏን በአደባባይ ለህዝቡ ማሳያ መንገድ ነው ።በኋላም በሥነሥርዓቱ ላይ አዛውንት ሴቶች ከልጃገረዶች ጭንቅላት ላይ ያለውን ቅቤ በማንሳት ወደ ሴት ዘመዶቻቸው ያስተላልፋሉ ።ይህም የሚሆነው መንፈሳዊ ቅናትን ለመፍጠር ነው።ላንቺ የሆነው ትዳር ለልጄም ይሁን እንደማለት ነው ።ምኞት ቢጤ... በኋላም ሙሽሮቹ ወደ ገበያ የሚወጡበት እና ከህብረተሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበት ሰዓት አለ። በተዘጋጀላቸው ባህላዊ ስፍራ ተቀምጠው “ማድሀ ዳና “ወይም ቦርዴ የተባለ የዶርዜ ባህላዊ መጠጥ በጋራ እየተጎነጩ፣ ዮዮዮዮ እያሉ እየተቃቀፉ ድንቅ ማህበራዊ ክዋኔና የአብሮነት ጊዜ ያሳልፋሉ ።ይህም ስነስርዓት “ሶፌ” በመባል ይጠራል።ይህም ስርዓት የሚከበረው ከእርድ ስነስርዓቱ 3 ወይም 4 ቀን ቀደም ብሎ ነው ። ለበዓሉ አከባበር በጣም አስፈላጊው ነገር የበሬዎች መታረድ ነው። መስቀል ከመድረሱ ከወራት በፊት በዓሉ ሁሉንም ማህበረሰብ ያማከለ እንዲሆን ሁሉም በየፊናው ይተጋገዛል ።ለምሳሌ ገንዘብ ያለው ሰው የተለያዩ ስራዎችን ራሱ መስራት ቢችል ራሱ ሌሎች ገንዘብ የሌላቸውን ሰዎች ለማገዝ ሲል ገንዘብ ከፍሎ ያሰራል። ገንዘቡን ሲከፍል “ለመስቀል በዓል እንዲሆን ቆጥብ ይለዋል”ከዚህ በተጨማሪ እንደየአቅማቸው የተለያዩ ነገሮችን በዕቁብ መልክ ይጥላሉ።ገንዘብ ፣ጥሬ እህል ፣እንቁላል ፣ቅቤ በዕቁብ መልክ የሆነ ሰው ቤት በታማኝነት ይጣላል። ሲጠራቀም የመስቀል ወቅት ላይ ይከፋፈላሉ። በ15ቱም ቀበሌዎች የበሬ ማደሪያ ስፍራ “ቃታ ካብ “እርከን ዙሪያ ወጣቶች እሳት ለኩሰው እያነደዱ እየዘፈኑ ፣እየጨፈሩ ፣ሌሊቱን ሙሉ ያድሩና በጥዋቱ በሬዎችን ይዘው ብዙውን ጊዜ ገበያ በሚካሄድበት ትልቅ ሜዳ ላይ ይወጣሉ።በመስቀል ቀን 2,000 ሺህ እና ከዚያ በላይ በሬዎች ይታረዳሉ።በዓለማችን በአንድ ቦታ ላይ ከ ሁለት ሺህ በላይ በሬ የሚታረድበት ቦታ ከዶርዜ ውጭ እስካሁን አላየሁም ።በአደባባይ በሬዎችን በማረድ ጥሬ ስጋ እየተበላ ቦርዴ ማድሀ፣ጠጅ ፣አረቄ እየተጠጣ ይውላል ። 10
ባይራ በ ዚህን ቀን ስጋ የማይበላ አንድም ሰው የለም ተብሎ ይገመታል ። በዓሉ በአንድነት ስለሚከበር ስጋ ከጤና ጋር ተያይዞ ካልሆነ የማይበላ ማህበረሰብ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም ። ሌላው የሚገርመው ክረምት እንደ ገባ አንድ ትልቅ ሳር የሚበዛበት ስፍራ ይታጠራል ።ልክ የመስቀል ቀን ያ ሜዳማ ስፍራ ይከፈታል። የተለያዩ የቤት እንስሳት ያለማንም ከልካይ ሳሩን ይመገባሉ ።የዶርዜ መስቀል እንኳን ለሰው ልጅ ለእንስሳትም ጥጋብ ገው ። መስቀል ለዶርዜዎች ሁለመናቸው ነው። ያላቸውን አቅም አሟጠው የሚያከብሩት ትልቅ በዓል ነው ። ሀባ ማስቃላ ዮ ዮ ዮ ሀሹ ጋቲሬስ ። ሁሉም በየራሱ ቀለም ሀገሩን ያድምቅ! 11
ባይራ “የነገ ሰው------” እንዳላብድ ልጅ ሰጠኝ አንድታሪክ ልንገራችሁ እስኪ። እንዳላብድ ልጅ ሰጠኝ ስላለቺኝ ልጅ... አንዲት ሴት ናት እንደዚህ ያለቺኝ። “ታውቂያለሽ?” አለቺኝ “ታውቄለሽ እግዚአብሔርን አስከፍቼዋለሁ--- ብዙ ጊዜ! እርሱ ግን ሁሌ አብሮኝ ነበር። ልክ ያልነበሩ ነገሮች በህይወቴ አልፈዋል። በዛ ብቀጥል ኖሮ አብድ ነበር።” አለቺኝና ወደ ልጅዋ እያየች ፈገግ ብላ “ግን እግዚአብሔር እንዳለብድ ልጅ ሰጠኝ።” አያችሁ ምን አይነት አምላክ ነው እንደሆነ? ሩቅ ሆነን የሰዎችን ህይወት እያየን እንዲ እንላለን ‘ የእጁአን ነው የሰጣት!’ እነሱ ደሞ “እግዚአብሔር እንዳልጠፋ ይሄን ሰጥቶ ሰበሰበኝ” ይላሉ። ሁሌ የስህተት መጨረሻ መውደቅ አይሆንም።አንዳንዴ በስህተቶቻችን ውስጥ በረከቶች ይኖራሉ። አጥፍተን አጥፍተን አናርፍ ስንለው በራሱ መንገድ ያሳርፈናል። ህይወታችሁን ቃኙት። እንዴት ነበር? ከምን መለሳችሁ? ከምኑስ አወጣችሁ? በሳምራዊት ንጉሤ 1