ግራፊክስ ዲዛይን ዮናስ ኃ/ማርቆስ 09 70 51 46 16
01 18 21 23 25 05 09 ላልደረሱት ትንፋሾች ... ከላኮመንዛ ሰማይ ስር ህልም ከምን ከምን ነው የተሰራው? አለመወደድ አልቻልሁም አግዙኝ! እንዲህም እንዲያም ነን አገባባዊ ድጋም (Syntactical Repetition of Poetry) ከ”ውስጠት” የግጥም መድብል አንጻር! በሩት ሃብተማርያም አይተነው ንጉሴ ቤዛዊት ዘርይሁን አድኀኖም ምትኩ ሳምራዊት ንጉሤ ወንድማገኝ ሶሪ ውብአረገ አድምጥ ኑኒ ባይራክ!
ላልደረሱት ትንፋሾች ... ሩት ሃብተማርያም ከመኝታዋ ስትነሳ አታረፍድም። ሳታዘው ትነቃለች። ትታጠባለች። ትለብሳለች። ጸጉሯን በወጉ ታበጥራለች። እጇ ላይ ያለ ሰዓቷን አይታ ፈገግ ብላ ትወጣለች። ታውቃለች። አያረፍድም። እንዳታረፍድ ትጣደፋለች። መንገድ ላይ ከሚተመው ህዝብ ላይ ዓይኖቿ መነፅር ያደረጉ አይኖች ይፈልጋሉ። እሱ ህልም ውስጥ ነው። ሲያቅፋት ፤ ሲስማት ፤ የሚያምር ሀብሏን ሲነካ ምናምን ምናምን ... ይነቃል። ይደነግጣል።የወንደላጤ ቤቱ ሲያስጠላው። ከሚያምር ህልሙ የትናየት ሩቅ አይነት የሚያስጠላ። ጠዋት ሲነቃ የሚፈልገው ሰዓቱን ነው። ያያል። ያውቃል አታረፍድም። ላለማርፈድ ይጣደፋል። እንደነገሩ ይለብስና ይወጣል። ከሚርመሰመሰው ህዝብ መሃል የሚያምር ሀብል ይፈልጋል። የሁለቱም ትልቅ ህልም ጎዳናውን መሻገር ነው። የኔ ህልም ጉዳዩን ለእናንተ መተረክ ነው። የነገር አጀማመር መጨረሻውን ወስኖ አያውቅምና እኔም የትረካዬን መጨረሻ አላውቅም።ጎዳና ነኝ እኔ። አልፈውብኛል። ሲዋደዱ ነክተውኛል። ሲደሰቱ ረምርመውኛል። ሲነፋፈቁ ታዛቢ ነኝ። የመዋደዳቸውን ቄጤማ ሲነቅሉ እንግጫው ነበርኩ። ሲበርድ ፣ የመውደዳቸው ትኩስነት በስልባቦት ሲተካ ሁሉን ታዝቤያለሁ። ዛሬ ያልደረሱ ትንፋሾቻቸውን በእኔ በኩል ትሰማላችሁ። እሷ ... ትናንትና ዛሬ በሚሉ የጊዜ መለኪያዎች መካከል ስንት ልዩነቶች አሉ መሰለህ ? እንኳን ትናንትና ዛሬ አሁን እና ቅድም በሚሉት ውስጥ እንኳ ሽራፊ ልዩነት አይጠፋም። እውነት ! በሽርፍራፊ ስከንዶች ውስጥ ስንት እንቅፋቶች በእግር ላይ ሰልጥነዋል? ስንት አውሎ ንፋስ ተነስቶ በርዶ ይሆን ? ፀሐይ በልጅነት ተወልዳ፥ ለስላሳነቷን ሰጥታ ማቃጠሏን አስከትላለች? በአሁንና በቅድም ልዩነት ውስጥ ስንት ዳኛ ፈርዶ ይሆን ? ስንት ትዳር ፈርሶ፥ አንድ መሆን ሁለት ሆኖ ይሆን? ስንት ትንታ በአንድ ጉንጭ ውኃ በርዷል ? ስንት ሰው ከመኖር ወደ አለመኖር ነፍሱ ሮጣበታለች ? ትናንትና ዛሬ አንድ አይደለም! አሁንና ቅድምም! 1 ያያታል። ታየዋለች። የመንገዱን ግራ ይዞ ይሄዳል። ቀኟን ይዛ ታዘግማለች። አዘውትሮ ሸሚዝ ይለብሳል። ሁሌም ቀሚስ ትለብሳለች። መነፅር ያደርጋል። የሚያምር ሀብል አላት። ረጅም ነው። አጭር ናት። ጠዋት ድልድይ ስር ላሉት ሽማግሌ ብር ይሰጣል። ማታ ሳንቲም ትሰጣለች። እሷ © Pinterest
... ክረምት አለፈ፥ አደይ ጎመራ ከልብ ሳንጫወት፥ ፍቅርን ሳናወራ አብረን እንዋል፥ እንጫወት ፍቅሬ የፍቅርህ ገዳፊ፥ የጾምኩትን ሽሬ። “ጊዜ የሁሉም አለቃ ነው። የጥንካሬና የኃያልነት ብቸኛ ገዢ ጊዜ ነው። ጠንካራ የነበረ ሰው ለእርጅና እጁን ይሰጣል። ኃያልነትም ባለበት አይቀጥልም። ጊዜ የራሱ አዲስ ኃያል ይሰራል። በጊዜ ያልተሸነፈ ፍቅር ብቻ ነው።” ትለኛለች አያቴ። በነገሮች ተፈትኖ ቢወይብም ፍቅር ሁሌም የዘገየ አሸናፊ ነው። ለዛ ነው አሁን ረስቼሃለሁ፥ ዘንግቼዋለሁ ካልሁበት ሳብ አድርጌ፣ በትናንት እና በመቀየም አቧራ የተሸፈነ ፍቅራችንን ‘እፍፍፍ’ ስለው እንደ ተዳፈነ እሳት፥ እንደቆሰቆሱት ልቤ ላይ የሚነደው። ... አሁን የትናንትናዋ ባለአበባ ቀሚሷ ወጣት አይደለሁም። ጸጉሬ መሃል ያ የምትወደው ጠረን የለም። እየበታተነ የሚጫወትበት የለም። ትናንት ከሰዓት አንተ ስትገፋኝ ምሽቱን ሌላ የትዳር እቅፍፍ ውስጥ ወደቅሁ። አሁን የምትወዳቸው ጡቶቼን ልጅ እያሳደግሁበት ነው። አንተን የሚስሙ ከንፈሮቼ ትዳሬን አሰማምርበታለሁ። ቤተሰቤን እስምበታለሁ። ልዩነቱ እንዳንተ ዓይኔን ከድኜ ቦታ ሳ’ለይ አልስመውም። እዚህ በቀመር ነው ሁሉም ነገር። ከመስመር አያልፍም። አልሳሳትም። ዓይኔን ከፍቼ መስመሬን አስምሬ እስመዋለሁ። ታዲያ አንዳንዴ በፍቅር ጨዋታ መሃል ትዝ ትለኛለህ። ልሰጠው የጀመርኩት ሙቀቴ ተሰብስቦ የሄደበት ይጠፋኛል። እንደዚህ ሲሆን ገላዬን ከገላህ በአካል ባላዋህድም ታማኝነቴን ያፈረስኩ እየመሰለኝ እሸማቀቃለሁ። እባክህ ይሄኛው ህመሙ ኃያል ነውና እንደዚህ አታድርግ እሺ! ... እና ግን ደህና ነህ? አገባህ? ወለድህ? ሚስትህን እንደ እኔ ጸጉሯን እየበታተንክ ትጫወታለህ? መንገድ መሃል ትዘፍንላታለህ? የሸሚዝህን ቁልፍ አሁንም ታዛንፋለህ? መነፅርህን አውልቀህ ዓይንህን ከድነህ በጥልቅ ትስማታለህ? ድንገት ስራ መሃል ደውለህ ግጥም ታነብላታለህ? ደስ የሚል እብደትህን ስርአት እና ማደግ የሚሉት ነገር ሸረሸረብህ? አሁንም ጆሮዋ ላይ ፅጌሬዳ ያደረገች ሴት ትወዳለህ? የሰው አጥር ላይ አበባ ለመቅጠፍ ብለህ ውሻ ያሳደደህ ትዝ ይልሃል? ሃሃሃ ... አሁን ድረስ ግርማ በየነን እኮ አልሰማውም። ከሰማሁት ለሳምንት እደነዝዛለሁ። ‘ፅጌሬዳ’ን እንዴት ልርሳው? እና ይሄ ሁሉ ማያያዣ እያለን ግን ተለያይተናል? ረስተኸኛል? ረስቼሃለሁ? ጸደይ መሃል ፈክተን ጸደይ መሃል ጠወለግን። እኛ ተለያየን እንጂ ሁሉም ከመስመሩ አልተዛነፈም። እና እጆችህ ከእጆቼ መላቀቃቸው አይቆጭም? ፍቅር ማለት እንደ እነሱ ነው እንዳልተባልን ስስታችንን ምን ወስዶት፣ የፍቅራችን ክረምት ደረሰ? እና ትናንት እንደ ዛሬ አይደለም። ዛሬም ትናንትን አያክልም። ከጊዜ ትበልጣለህ። አላይህም ፣ አታየኝም ግን አብረኸኝ አለህ። ይሄ ልክ ነው ልክ አይደለም? ከትዳር ፆሜ መሃል የምታስፈስከኝ ሀጢያቴ ነህ!! 2 1 ፍሬሕይወት ለማ “አብረን እንዋል”። 1 © Pinterest
3 እሱ ... “ነገሮችን አልፌ ሳያቸው የምቆጭ አይነት ሰው አይደለሁም። ታውቂ የለ? ትናንት ያደረግሁት ነገር በጊዜው ልክ ነበር ከሚሉት መሃል ነኝ። ይሄ አቋሜን ልክነት የነሳሽው አንቺ ነሽ። ከትናንት የሚጎድል ወደዛሬ የማይሻገር ነገር ሁሉ በግዴለሽነት የሚታለፍ ነገር እንዳልሆነ ያስተማርሽኝ አንቺ ነሽ። ሃሃ ቢማሩት ምን ይሰራል? ማርፈድ እንደሚያቆስል ከቆሰሉ በኋላ መረዳት ምን ያደርጋል? ... የመጀመሪያ ቀን ሳይሽ አበባ በጆሮ ግንድሽና በለስላሳ ጸጉርሽ መሃል አስቀምጠሽ ነበር። ደስ አልሽኝ። ለአበባ አበባ ምን ይሰራለታል እያልሁ ንብ ሆኜ ልቀስምሽ ተጠጋሁ። ስቀርብሽ ደስ አልሽኝ። ታሳሺ ነበር። ባለቀለም ቀሚስሽን ለብሰሽ እንደ እንቦሳ እየዘለልሽ ስትመጪ ሳይሽ መልአክ ትመስይኝ ነበር። ጸጉርሽ መሃል ያለ ጠረንሽን ዓይኔን ከድኜ ሳጣጥም ሲንደሬላን ያጨሁ ልዑል የሆንሁኝ ይመስለኝ ነበር። የነፍስሽ ንፅህና ከሀጫ በረዶም ያስንቃል። ነገሮቼ ሁሉ በነበር ጫፋቸው ተዘምዝሟል። ልክ ቁጫጭ መሸፈኛ ውስጥ እንዳለ በልቶ እንደጨረሰው ከረሜላ አለሁ እያልሁ ነው የሄድሁብሽ። ... አንድ ቀን የጻፍሽልኝን አስታወስሽ? ወረቀቱ አርጅቶም ኪሴ ውስጥ ተቀምጧል። ላንብብልሽ? እንደ ዱሮው “ጌትዬ አንብብልኝ!” ብለሽ እጅሽን ጉንጮችሽ ላይ አድርገሽ ዓይንሽን ባታንከራትችብኝም ላንብብልሽ። “... እጆቼን አጥብቀህ ያዘኝ። ጣቶችህ ህይወቴን ማስቀጠያ ክሮቼ ናቸው። ከልቤ ኩልል እያለ የሚሰማው የፍቅር ዜማ ለሌላ ሰው ትርጉም አልባ ሹክሹክታ ነው። አንተን ካልሳሙ እንዴት ሊገባቸው ይችላል? ትንፋሽህ በአንገታቸው ዙሪያ ካልዋለ እንዴት ሊሰማቸው ይችላል?? ...ዓይኖችህን ሳይ የሚሰማኝ ምትሃት ልዩ ነው። እ--- አለ አይደል? ፈጣሪ አሰልፎ ዓይን ሲያድል አንተን ሲያይ ቆይ ላንተ ሌላ አለ። ና ተከተለኝ ብሎ ያዳላልህ ይመስለኛል። ሁሌም እደነግጣለሁ። ሃሃ አያስቅም ሀሳቤ? ፈጣሪ ሲያዳላ ሃሃ-- ...በጸጉሬ መሃል እጅህ ሲርመሰመስ የት እንዳለሁ እዘነጋለሁ። ጣቶችህ ነገር ይፈልጉኛል። መንሳፈፍ ስጀምር ትሄዳለህ። ትሸሸኛለህ። ለምን ሩቅ ትሄዳለህ? ለምን ዝም ብለህ አትስመኝም? ... አንተ የተረት ከተማዬ ልዑል ነህ። የተረት ከተማ ነዋሪዎች ደግሞ እ-- ልክ እንደ መልአክ አይታዩም ፤ አይዳሰሱም ፤ ... አይሳሙም። ሁሌም እወድሃለሁ።” እንደዚህ ያልሽን እያነበብኩ ነው የምተነፍሰው።” ፀሐይ ጨረቃም፥ ምንም ናቸው ካንቺ ጋር ቀረ፥ ውበታቸው ባንቺ ያልተገራ፥ ምን ተገኘ ፍቅርሽ ሲነካው፥ ያልተቃኘ። ነገሮች በአሉበት ይቀጥላሉ። ንፅህና ስርዓት በሚሉት ኩል ይኳላል እንጂ ነገር ሁሉ መስመሩን ሳይለቅ ይከናወናል። አገባሁ። ወለድሁ። ልጄን በስምሽ ሰይሜ ዓይኖቿ መሃል ንፅህናሽን የምፈልግ ብኩን ሆኛለሁ እንጂ ደህና ነህ ወይ? ካልሽኝ በሰዎች መለኪያ ደህና ነኝ። ትናፍቂኛለሽ። ጸጉርሽ መሃል ያለው፥ ዓይኔን ከድኜ የማጣጥመው ጠረንሽ ሌላ ቦታ ላገኘው አልቻልሁምና ይናፍቀኛል። አፍ አውጥቼ አልናገር እንጂ የነገሮች ሁሉ ሚዛኔ አንቺ ነሽ። ልክ ነህ እንዲሉኝ የምፈልገው ባንቺ ተመዝኜ ነው። ደህና ነኝ...! ጎሳዬ ተስፋዬ “ይታየኛል” 2 2
4 ፍቅር መልኩ እንዴት ነው ? የሄደው የመጣው መነካቱን የሚለካው በምን ሚዛን ነው ? የፍቅር ልክነት የት ጋ ነው መስቀሉ? የነካን ፣ የወደደን ፣ የተወን ሄዷልን ያልነው ሁሉ የትኛው ሰውነታችን ጋር የሚደበቀው ? አብሮን ለሚነፍሰው ንፋስ አብረነው ብንሮጥም ግን የልባችን እሽክርክሮሽ አብራን የለችምና ለሌሎች የሚታየው መውለብለብ ብቻ ይታያል። እኔ መንገድ ነኝ። እናንተ ደሞ የትንፋሻቸው ፣ የእርምጃቸው ፣ የነበረ መልካቸው መዳረሻዎች ናችሁ። በእኔም አልተጀመረምና በእናንተም አይቆምና ላያችሁት እና ለሰማችሁት እውነታቸው ሁሉ መንገድ ሁኑላቸው። እናም መንገድ ስላጡ ትንፋሾች እንማልዳለን ! ©Etsy Australia (Separation by Edvard Munch Hand-painted Oil Painting blonde)
እንዲህም...እንዲያም ነን ወንድማገኝ ሶሪ “ስሜን ተውት አለ የተቸገረው መላኩ ስሙን ቢፈራው። እኔም እንዲያ ማለት ያሻኛል።መጀርፈፌ፥ መኮርፈፌን ያዩ ሁሉ፣ ” “ ” ደራሲ ወንድማገኝ እያሉ በየ አረቄ ቤቱ ማጣጫ፥ በየ ቡና መጠጫው ሀሣብ መወርወሪያ፥ ቢያደርጉኝ እራሣቸው ሊሉት ያሠቡት ነገር አለ ማለት ነው። ደራሲው ፥ያ ወንድማገኝ፥ ያ ብቻውን ጥግ ላይ ሚቀመጠው፥ የሚሉኝን እውነት ብዬ ተቀብዬው ይሆንን? ደግሞም የቀድምው መምህሬ “ተው አንተ ልጅ ቢያንስ አንድ ሥራ ልትሠራ ግድ ነው “ ቢለኝ የውስጥ መብከንከኔንና ኩርፊያዬን፣ ብዙ እልበታለሁ ያልሁትን የጽሑፍ ሥራዬን ሰጥቼው ነበር። ዛሬ ላገኘውና በጽሑፌ ልንወያይ ነው ወዲህ የመጣሁት። አዎን እንደሁልጊዜው ቀድሞኝ ተከስቷል ። የሠጠሁትን ጽሑፍም እያነበበው ነው። ገረመኝ። ደግሞት ነው አልያም ገና አሁን እያነበበው ነው። “ልቀመጥ ወይስ ሌላ ሚጠብቁት ጥቁር እንግዳ ይኖር ይሆን ?” ፕሮፌሰር ። የእኔው ጥያቄ ነበር። አያይ አንተው ነህ እንግዳዬ ልጅ ወንድምአገኝ። ጥሩ (ተቀመጥሁ) ብዙ አወራን----------- ከማን ጋር? ከስራ ጋር። እናሣ? (ዓይኔን ወደ ወረቀቱ ጣል አደረግሁት ) ከቤት አየወጣሁ ነው ይላል። ትዝ አለኝ። በዓይነ ኅሊናዬ እንደ ገጣሚዎቹ የጻፍሑትን በቃል ተወጣሁት። ተንስኡ ማለት አሻኝ እንደ ካህኑ። ለማንኛውም ተነሳሁ። ተከተሉኝ። ጽሑፌም እንዲህ የሚል ነበር። 5
ከቤት እየወጣሁ ነው --------። (እና ምን አገባን ?) ልትሉ እንዳይሆን? ምን አገባንን ምን አመጣው ? ፍራቻዬ ከዳር የተነሳው እሳት ከዳር አያበቃም።የሚበላውን በልቶ ወደ መሐል ይተማ ል እንጂ። ’ ደግሞ እዚሁ ቅርብ፥ እኛው ከተማ ብዙ ተማሪዎች ከትምህርት ሲመለሱ፣ እናታቸውን ከፍርስራሽ መሐል እንባዋን ጨርሳ፥እ--እታዋን ተኮራምታ ሲታዜም ያገኙበት ጊዜ ብዙም ሩቅ አይደለም። ትናንት እንጂ ! እውነት ይህ የሚረሣ ሆኖ ነው ?ወይስ መርሳቱ ተሽሎን አግኝተነው ? ለማንኛውም ከቤት እየወጣሁ ነው ስል አጃኢብ የሚያሠኝ ፈጠራ ሁኖ ሣይሆን፥ አንድም የጊዜ ሚዛኑ ወዲህ ካጋደለ ይህ ቤቴ አመድ ሁኖ ሊጠብቀኝ ይችላል የሚል ፍራቻ፤ ሲቀጥልም ወጥቶ መቅረት ምንም የሆነበት ሀገር ላይ ከመኖሬ አንጻር ስጋት ቢኮፈኩፈኝ ነው። ዛሬ ላይ የሚደረጉት ነገሮች ያን ያህል ጊዜም፥ ባለሙያም፥ ዕውቀትም አይሹም። (አይሆንንም ትተሽ ይሆናልን ማሠብ ሣይሻል አይቀርም።) የነበረው እንዳልነበር፥ ቁምነገሩ ቅዠት፥ ቅዠቱ ተረት፥ ከአሉ ነበሩ ላለመሆን ነው። ’ እኔ የምለው ሠፈሬ እንዲ የሆነው ከመቼ አንስቶ ነው ? (በሀሣብ ብዙ ተጓዝሁኝ መሠለኝ ከሀገር የመውጣት ያህል ነው የደከመኝ አንተዬ።) ሰው ሀገር ያለሁ ይመስል ‘ባር ባር’ የሚለኝስ ነገር በጤናዬ ነው ? ለቀዬው ባዳ ሆንሁና የማየው የተፈቀደልኝን ነው። ከምን ተነስተን ምን ላይ ደረስን ጃል ? “ወንድም ራበኝ “ ከሀሣብ ከናወዝሁበት የሚያናጥብ ድምፅ። ድምፁን ወደሠማሁበት ፊቴን ቀለስኹ እኔን ከሆነ እንዳልስቅ በሚመስል ምፀት አየሁት። መልከ ጥፉ ነው። ከናፍሩ “ ”በሲጃራ ያረረ፥ የወነቸፈ ወጣት እያጉረጠረጠብኝም መሠለኝ። ቆይ ግን ያ ሠበር የምንለው ነገር፥ ትህትናችን ምን ገባ ?አደራውን የበላሁት እንጂ ምፅዋት ጠያቂ አይመስልምኮ። በእርግጥ አንገቱን ደፍቶም ጠየቀ ተወጣጥሮ ምን አለኝ ‘የተሻለ የምሠጠው? ከሀፍረቴ ውጪ ልስጥስ ብል ምኔን ? ይሄኔ አይደል ከባዶ ላይ መዝገን የሚባለው “ ” ? እሡስ ምን ተዳው ብሎ ? “በዊልቸር የሚለምንን ምስኪን ብር እንድሠጥህ መጀመሪያ አስነዳኝ አይነት ደፋሮች መሀል ”ሁኖ ስለምን ይልመጥመጥ ? አበጀ! ለማንኛውም አራዳ ነው። ዓይኖቼ ስር ኪሴን አወቀው። የሽሙጥ ጥርሱን ፈልቅቆልኝ ሄደ። እእእእእፍ ፎይ … ! ለካ የጠያቂዎችን ያህል ሠጪም ይጨነቃል። አይ ጉዴ! ወገኛ! አሁን እኔ ምኔ ነው ሠጪ ? ዱዲ ኪሴ ሣይኖር ? ማን ይሙት ፈጣሪ ይክፈላት እንጂ እህቴ ያጠበችልኝን ለብሶ ከመውጣት ባሻገር በኔና በየኔ ቢጤው መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው “ ” ? እሱ እውነቱን ተቀብሎ ሲጋፈጥ እኔ ደግሞ በዝምታ ስናውዝ አይደል ጎዳናው ያገናኘን ? “አትሠማም!?” የሆነ ድምፅ ባረቀብኝ። አንደኛውን በመታኝ ሳይሻል ይቀራል ? አልሰማም እንዴ? ጆሮዬ እኮ ለወትሮ ማልፈልገውን ሁሉ እየሠማ የሚያናድደኝ አካሌ ነበር። ዛሬ ምን ነካው የሚያሣ ጣኝ ’ ? “ዎዎዎዎውዎሽሽሽ” ለፉጨት በቀረበ ቃል። ማን ነው ? መቼም እኔን አይሆንም። እንዴታ ?እሠማለሁ እንጂ። ተናደድኩ ቁጣ ቁጣ አለኝ። “ አህያ? ....” እርፍ! ይለይለት። ምን እንዳደረግሁት እንጃ። በያዘው የጎማ ጅራፍ ቂጤን ዣጥ ቢያደርገኝ ደስታውን አይችለውም። “አህያያያያያያ” እሡ ምንም ከኔ ቢርቅም የሚነዳት አህያው ከዓይኔ፥ ቃሉ ከአእምሮዬ ሊወጡ አልቻሉም። (ይህ ንግግር የአህያ ነጂው ብቻ ሀሣብ ነው የሚለውን መቀበል ተሣነኝ። ) ሁላችንስ ከዚህ አዘቅት ያልወጣን አይደለምንን ? የመሪና የተመሪው ሚና ያለ የበት፥ ተመሪው ከመሪው የቀደመበት ጭምር እንጂ። እሠየው ሰደበኝ። አዎ አህያ ነኝ። አህያ ነን። 6
ዝም ብለህ ’የምትሸከም፥ ዝም ብለህ የሠጡህን እንክርዳዱንም ግብስባሱንም የምትግፍ ከሆነ የኋላ ኋላ በቁንጣንህ የሚስቁትእነሡ ናቸው ። እነሱን እንደ ብዙ አንተን እንደ ምንም መቁጠር ያላቆምህ ዕለት አዎን አህያ ነህ ። ነን። እነሱም እንደ ነጂው ስድብ ከምስጋና የተምታታባቸው የቀን ሰካራሞች፥ የተደናበሩ ድንባዣም አይደሉምና ነው ? አሁን ይሄን ሁሉ ስዘበዝብ የሆነ የከፋው መምህር፥ አልያም የተቃዋሚ ፖርቲ አባል መስዬ ይሆናል። እንዳይመስልህ። የወጣልኝ ስራ ፈት ነኝ። መንግስት ኮርቶብኝ እንደ ንብረቱ የቆጠረኝ፡፡ እናታችን ናት እኔና ዘጠኝ እህቶቼን በ NGO ፅዳት ሰርታ የምታስተዳድረን። እውን ማስተዳደርስ የእሱ ፋንታ አልነበር ? የላይኛው ጌታ። እሡን ተወውና እኔስ እህቴ ያጠበችልኝን አይደል ለብሼ የምወጣው፡፡ ምን ይሉት ስንፍና ነው ግን የተጠናወተን ? ቢያንስ ስራ የለኝ፥ ጊዜ አላልቅ ብሎኝ እንደኔም የሚንገላታ የለም፡፡ ታዲያ ምን ነካኝ ቢያንስ ልብሴን ላለማጠብ ለግሜ እሷ ያጠበችልኝን እየለበስሁ የምወጣው? የት ነው ግን የምሄደው ? እንዴት ሰው ቢያንስ ሀገር አይበጠብጥብም ? እኔስ ለመበጥበጥ ምንድን ነው የቀረኝ በደል ? ጎረቤታችን ሱዳን ሁለት ለመሆን አንገሸገሸኝ ስትል እውነት እንደሚሉት ዳቦ ስሙኒ ገባ የሚል ታሪክ ከሆነ እንደሱዳንም ቄንጠኛ የለ። ኧረ ቀበጠች ! እሺ የእሷስ ይሁን የእኛዋስ ምን ነክቷት ነው ? ሆደ ሰፊነቱን ከየት አመጣችው ? አንዳንዴ ምርር የሚያደርጉ ነገሮችን ጠፍተው ነው? ስል እራሴን እጠይቃለሁ። ግና ብዙ ብዙ የእናቴ እኛን አስተኝታ፥ ወደ ፈጣሪዋ አንጋጣ፥ ያለቀሰችው እንባ እውን ለፈጣሪዋ መባ ይሆን ? ወይንስ ብዙ ድንጋይ የሚያስነሱ ብዙ መፈንቅለዎችኝ በየለቱ ሚያስደርጉ ጉዶች ነበሩ ? ግን ካለው ይልቅ የሚመጣውን ፍራቻ፣ የሌሉ ያህል ኦና ውጦን አስፈሪ ዝምታ ውስጥ ገብተናል። በቃ የሙት ልጅ ክብር የለውም ሆነና ነው በሙት አባቴ የማላውቀው ታሪክ እንዲህ አሳሬን የማየው ? የሠፈራችን እድር ግምጃ ቤት ሃላፊ ፊቴ ድቅን ብለው በዓይናቸው በአፍ ጢሜ ከደፉኝ በኋላ፥ እናትህ የእህቷን ሞት ”ተረድታ ኡ ኡ ኡታዋን እያቀለጠች ቁልቁል ዘልቃልሃለች አሉኝ፡፡ “እናትህ ቁልቁል ዘልቃልሃለች፥ የሚሉት ቃላቶች አቃጨሉብኝ። በፊት በፊት እናቴ የሁሉም ነበረች። የመንደር አለቃ፥ለሀዘን ለደስታው ፊት አውራሪ፥ የሁሉንም ሀዘን ሀዘኗ ያደረገች አስተዛዛኝ ዛሬ ላይ ግን በሷ የመጣውን የሚጋራት ጠፋ አ? እናታችን እንዳላሏት እናትነቷን ቀሟት። ያንተ ማለቱ አይደል ዘልቃልሃለች ማለቱ፡፡ ያውም ቁልቁል በመሻል እንጂ በማሽቆልቆል የሚገኝ ጥቅም ያለ ይመስል፡፡ ይህ ስለእናት ብቻ እንዳይመስልህ፤ ስለሀገርም እንጂ። ሀዘኗን የሚያስተዛዝናት አጥታ ቁልቁል እንደ እብድ የሚያስጮኋት ወዳጅ አልባ፥ የሙሽራ ላጤዋ ሀገር ናት። “አለቀ በቃ?” አለ ፕሮፌሰሩ። ቢቀጥልስ ምን ሊጨምር እዚህ ላይ ? ምንስ ጎድሎ? ብዬ መለስሁለት። 7 © Pixels PIXELS (Avoiding Problems - PA Painting by Leonardo Digenio)
68 አንተ ጥሩ ጸሐፊ እንደሆንህ አውቃለሁ። ግን ይሄ ጽሑፍ በደንብ አውጠንጥነህ የሠራኸው አይመስለኝም። እንዴት? ወንዴ ያነሣኸውን ሀሣብ እንደማንኛውም ተርታው ህዝብ ነው ያወጋኸው፤ እንጂ እንደ ደራሲ አይደለም። ደራሲስ የተርታው ህዝብ ወላፈን አይነካውም ? የራሱ አፋፍ ያለው ይመስል ማሽቀንጠሩ ምን ይሉት ነው ? ስትቀነጭርም ስትፋፋም እንደ ህዝቡ ነው። እሱ ልክ ነህ። ግን ሀሣቡ የተረጋጋ አይደለም። እዛም እዚም ይረግጣል። እሠየው! አበጀኋ! እውነታው ከዚህ የዘለለ ነው ? ትናንት ያመሠገንነው አይደል ምን ይሉኝን ሣይፈራ ዞሮ ሲወጋን ሚከርመው? ደራሲ የራሡ ትናንት የራሡ ነገ ይታየዋል የታየውን በጽሑፍ ያሣያል። የት ሁኖ? በአንድ ወቅት ሀያሲ እዝራ አብደላ ከ ዓለማየሁ ገላጋይ ጋ ሲጨዋወቱ እዝራ “ትንሽ ገንዘብ ቢኖረኝ አንድ ቪላ እና የተወሠኑ ሠርቪሶች አድርጌ፥ ደራሢው ለሚበላው ለሚጠጣው ሳይጨነቅ፤ሲቸገርም የኪስ ሣንቲም እያገኘ በነጻነት እንዲያስብና እንዲጽፍ አደርገዋለሁ “ ብሎ ነበር። ሸላይ ሀሣብ ! ህዝብ መሐል ያለን ደራሲ የሚያሽሟጥጥ ማህበረሰብ ጋር ስትኖር ታሽሟጥጣለህ። እኔም የዚያ ወገኔ አጥንት ስንጣሪ ነኝ። ወለም ሲለው ወለም ይለኛል።በዚህ ሁሉ ችግር ውጥንቅጥ ውስጥ ያለች ሀገር ላይ ያለ ጸሐፊ አሽሟጣጭ እንጂ ነብይ ሊሆን ትሻለህ ? ቢሆንም ራስን በዚህ ልክ ማየቱ የለብህም ዘመን ያልፋል። የምንጽፈው ግን ከዘመን ይሻገራል። ይሁና! እውነታው ያ ነው። የኔ ቢጤው፥ ጦርነቱ፥ ስራ አጥነቱ፥ አለመተሣሠቡ፥ አፋፍ ለአፋፍ ተዃኹኖ ግጠመኝ ይዋጣልን ዛቻው፥ የዚህ ዘመን መልካችን ነው።ፓለቲካው እንዳይጠልፍህ እፈራለሁ። አሁን ያለው ጸሐፊ ሁሉ የተጠለፈ ይመስለኛል። ደራሲ የስራው ጌታ ነውና በገፀ ባህሪያቱ መብት እንዳለው ሁሉ፣ በህዝብ ላይ የማኖርም ያለማኖርም መብት አለኝ የሚል ንጉስ ያላት ሀገር ነገዋ አጓጊ አይደለም። ከቦኩ አይቀር ብሽቅጥ ነው።ዘመን መልካምም እኩይም ጎን አለው። ይህ ዘመንም እንደቀድሞዎቹ ሁሉ የሚወደስበትም የሚኮነንበትም ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።ሁሉም እማይባል ሁኖብኝ እንጂ ከሞት ይልቅ ምን ያህል ሚለው ሚያሣስበን፥ የሞት ጅምላና ችርቻሮ የተላመድን፥ከተራበው ህዝብ ይልቅ ብጣሽ የጣለው መንግስት ሚኩራራበት --------ታዲያ እሡ መልካም ስራ አይደል ? ያለፉት መንግስታት ያላደረጉትን ደሃውን ማገዝ ? አንድ እናት ተፍጨርጭራ ልጇን የምታስተምርበትንና የምታሣድግበትን ጉሊቷን ነጥቀህ ስታበቃ፥ ቅስሟን ከሠበርህ በኋላ ልጇን ብታበላ ብታስተምር ምን ሊፈይድ ? ዛሬ አንድ እናት ልጄ ተምሮ ይደርስልኛልን የምታስብ ይመስልሃል ? ልጇ የመንግስት የብድር ኩፖን ከሆነ ቆይቷል። ያደጉት አገራት ስንዴውን እንጂ ማረሻውን አይሰጡንም። ለምን አትለኝም ?ግልፅ ነው። ለማኝነትን ታቆማለህ፤ ትከሻ ከትከሻ ትለካካለህ፤ ይህ ደግሞ እጅ ለመጠምዘዝ አይሆንም። በደካሞች መሐል የበረቱት ያልፋሉ በሚል አመለካከት ደካሞች ብርቱ የሆኑ ለታ አጻፋው ከባድ ነው። የዘመኑ ማንዴላ የማይፈጠርበት፥ ተያይዞ ገደል የሆነ ነገ ይመጣል። ስጋትህ ይገባኛል። ይሄን ጽሑፍ ግን በስነ -ጽሑፍ ዓይን ለማየት ነው የሞከርሁት። አምናለሁ በደንብ ታስተካክለዋለህ። ያ ራስን ማታለል ነው። ቢሆንም እሞክራለሁ።ድንገት ከተቀመጥሁበት ብድግ ብዬ ፕሮፌሰሩን ተሰናብቼ ጉዞዬን ቀጠልሁ። በመጣሁበት መንገድ ማዝገሙን ተያያዝሁት። ሌላ መንገድ --- ሌላ ሃሳብ። ይቀጥላል ...
አገባባዊ ድጋም ውብአረገ አድምጥ ከ “ውስጠት” የግጥም መድብል አንጻር! (Syntactical Repetition of Poetry) በቃል ድጋም ሲጀመር ... ዓለም የቆመችው በቃላት ኃይል ነው ይባላል። መጀመሪያ ቃል ነበር እንዲል ታላቁ መጽሐፍም። ቃላት ኃይል አላቸው።ቃላት ሲደጋገሙ አንዳች ጉልበታም መንፈስን ያሰርጻሉ። ለዚህም ነው ሁሉም ነገር በቃል የሚሰራው። በተለይ በቤተ እምነቶች ዘንድ የቃላት ኃይል በደንብ አጽንኦት ይሰጥበታል። ከጸሎት ይጀምራል። ብዙ ጸሎቶች በቃል ይደረሳሉ። በቃል ከመደረስ ባሻገርም እንዲደጋገሙ ህጋቸው ያዝዛል። ጸሎትስ ተደገመ አይደል የሚባለው። በኦርቶዶክስ ክርስትና አስተምህሮ በቀን ሰባት ጊዜ ጸሎት ይደገም ዘንድ ይደነግጋል። እያንዳንዱ ሰዓታት የየራሳቸው ትርጉም ቢኖራቸውም ጉዳያችን እሱ ስላልሆነ ከድጋም (Repetition) ጋር የሚያያዘውን እንመልከት። በቀን ሰባት ጊዜ መጸለዩ በራሱ ድግግሞሽ ነው። በእነዚህ የተወሰኑ ሰዓታት ላይ ደግሞ እንደ መዝሙረ ዳዊት፥ የዘወትር ጸሎት፥ ውዳሴ ማርያም፥ አርጋኖን የመሳሰሉት ጸሎቶች ይደገማሉ። በዚህ መደጋገም ውስጥ ከመለኮት እንደርሳለን፥ ልመናችም ይሰማል ተብሎ ይታመናል። ምዕመናን አስራ ሁለት ጊዜ እግዚኦ መኃረነ ክርስቶስ ይላሉ። በእንተ እግዝእትነ ማርያም መኃረነ ክርስቶስ ተብሎም ይደገማል። ኪርያላይሶን እየተባለም ድግግሞሹ ይቀጥላል። መነኮሳት በመቁጠሪያቸው ዙር እየተሽከረከሩ ኤሎሄ እያሉ ቃላትንና ስሞችን በመደጋገም ጸሎታቸውን ያደርሳሉ። ቅዳሴው፣ ማኅሌቱ፣ ኪዳኑ ሁሉ የቃላት መደጋገምን ይፈቅዳል። በእስልምና ሃይማኖት ዘንድም ይሄ መደጋገም አለ። ቢስሚላሂ አል አረህማን አል ረሂም አልሀምዱ ሊላሂ ረቢል አለሚን አል ረህማን አል ረሂም ማሊክ የውሚዲን ኢያከ ናእቡዱ ወኢያ ከነስተኢን ኢህዲነ አል ሲራጠል ሙስተቂም ሲራጠ አል ለዚነ አንአምተ አለይሂም ገይሪል መግዱቢ አለይሂም ወለ ዳሊን አሚን 3 4 አገባብ- የቅኔ፥ የሰዋስው፥ አገባብ፤ በስም ላይ በነባር አንቀጽ፤በዘማች አንቀጽ ላይ እየገባ ማሰሪያነት የሚያስለቅቅ አገባብ (መስተዋድድ) ይባላል። (ከሣቴ-ብርሃን ተሰማ፤ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ከተሰማ ሀብተሚካኤል ግጽው ተደርሶ የተጻፈ 2011ዓ/ም፥ ገጽ 811) ድጋም - በቁሙ መድገም፥ መደጋገም፥ድገማ፥ ድግሚት ፥ ጸሎት። ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወ ግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ 2ኛ እትም 2013 ዓ/ም፣ ገጽ 339) 3 4 69
10 እያሉ በቀን አስራ ሰባት ጊዜ ወደ አላህ ጸሎታቸውን ያቀርባሉ። ያውም በዜማ። ደስ በሚል ጥዑም ዜማ! ከሃይማኖቶች ተሻግረን ወደ አስማትና ድግምት ከሚሰሩት መናፍስት ጠሪዎች ዘንድም ብንሄድ ተመሳሳይ ነገር እናገኛለን። ቃላት በመደጋገም ሃረጋትን ደጋግሞ በማነብነብ አንዳች መንፈሳዊ ኃይልን ይቀዳጃሉ። እርኩስም ይሁን ቅዱስ ድርጊቶችንም ሲፈጽሙ ይታያል። ለዚህ ነው K. Chandrasekhara Rao እንዲህ የሚለው። Learning anything by heart through repetition gives a sort of command over it. People often repeat phrases that they think important in their conversations or public speeches. Poetry is more akin to magic, prayer, prophecy and myth than a skill to perform mechanical task. ለዚህ ሁሉ መሰረቶቹ ቃላት ሲሆኑ ድርጊቱ ደግሞ የተመረጡትን መደጋገም ነው። በመደጋገም ውስጥ ውበትን፣ ስሜትን፣ እውነትን ማስረጽ ይቻላል ተብሎ ይታመናል። ራመድ ወደ ግጥም----- በግጥም ዘንድም ይሄ ድግግሞሽ አለ። በእንግሊዝኛው Syntactical Repetition ይባላል። እኔም መዝገበ ቃላቶችን አጋለብጬ ስሜቱን ይገልጥልኛል ባልሁት መሰረት አገባባዊ ድጋም ስል ሰይሜዋለሁ። አገባባዊ ድጋም ማለት በግጥም ውስጥ ድምጸትን፣ ፊደላትን፣ ቃላትን፣ሀረጋትን፥ ስንኞችን ወይም አርኬዎችን በመደጋገም አንድን እውነት ወይም ስሜት የማስረገጥ ሂደት ነው። በእንግሊዝኛ ግጥም ውስጥ ይሄንን ድግግም በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ይከፍሉታል። እነሱም Repetitions of sounds (የድምጸት ድግግሞሽ) እና Repetition of words, or phrases, lines and stanzas [ The Significance of Repetition in Poetry by K. Chandrasekhara Rao Seminar Paper] (የቃላት፥ የሃረጋት፥ የስንኞች እንዲሁም የአርኬ ድግግሞሽ) ብለው ይከፍሏቸዋል። በውስጣቸውም ብዙ ክፍፍሎችን እየሰጡ ግጥማቸውን ይተነትናሉ። ለዚህ ጽሑፋችን መንደርደሪያ ይሆን ዘንድ ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ ጠቀስ አድርገን እንለፍ። በድምጸታቸው ወይም በምታቸው (Rhyme) ድግግሞሽን ከሚያሳዩ ግጥሞች ውስጥ እንደ ምሳሌ ከኢድጋር አለን ፖ (EDGAR ALLAN POE) The Raven ግጥም ውስጥ የመጀመሪያውን ስንኝ ማየት እንችላለን። Once upon a midnight dreary, while I pondered, weak and weary ከኮለሪጅ ረጅም ግጥም ውስጥም አንድ ምሳሌ ብንደግምስ። In mist or cloud or mast or shroud የቃላት ድግግሞሽ ከሚታይባቸው ግጥሞች ውስጥ ከጆን ሚልተን ግጥም ውስጥ ለቅምሻ እንመልከት። “For Lycidas is dead, dead ere his prime, Young Lycidas and hath not left his peer. እንዲሁም The years to come seemed waste of breath, / A waste of breath the years behind” የሐረግ ድግግሞሽን በምሳሌ ለማየት ያህል ከዊሊያም ሸክስፒር ኦቴሎ ላይ እንምዘዝ። 5 6 7 8 The Significance of Repetition in Poetry by K. Chandrasekhara Rao Seminar Paper Public domain. First published by Wiley and Putnam, 1845, in The Raven and Other Poems by Edgar Allan Poe. The Ancient Mariner, by S.T Coleridge Lycidas, John Milton William Butler Yeats “An Irish Airman Foresees His Death 5 6 7 8 9 9
“Put money in thy purse; follow thou the wars; defeat thy favor with an usurped beard; I say, put money in thy purse. It cannot be that Desdemona should long continue her love to the Moor--put money in thy purse--nor he his to her: ለምሳሌ ያህል ከላይ ያሉትን ግጥሞች አየን እንጂ እጅግ ብዙ ገጣሚዎች ይሄን አገባባዊ ድጋም በግጥማቸው ውስጥ ይጠቀሙታል። በዚህም የግጥም ቴክኒክ ማድረስ የሚፈልጉትን ስሜት ማጋባት ይችላሉ። አገባባዊ ድጋም (Syntactical Repetition) ለመሆኑ ይሄ አገባባዊ ድጋም (Syntactical Repetition) ምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ የተለያዩ የስነ ጽሑፍ ሰዎች በተረዱት ልክ ትርጓሜ ሰጥተውታል። መምህርና ገጣሚ ቴዎዶር ሮትኪ (Theodore Roethke) “Some Remarks on Rhythm” (1960), በሚለው መጣጥፉ ስለ ድጋም እንዲህ ይላል። “Repetition is in fact “the very essence of poetry.” Arguably, you can write a poem without repeating a single word or rhyme scheme or phrase, and call it a poem, but in that instance, you may find people in fact mistake your poetry for prose”. ግጥምን ያለምንም ድጋም መጻፍ እንደማንችል አስረግጦ ያስገነዝበናል። ቢያንስ ቢያንስ ከግጥም ባህርያት ውስጥ አንደኛው የሆነውን ሙዚቃዊነትን ወይም ዜማዊነትን መልቀቅ እንደማንችል ሲነግረን ነው። በየትኛውም ግጥም ውስጥ የቤት መምታትና ቤት መድፋት እስካለ ድረስ የድምጽ መደጋገም የማይቀር ነው። በእኛ የአማርኛ ግጥም ውስጥም ያለ ምት ወይም ያለ ቤት መምቻና ቤት መድፊያ የተጻፈ ግጥም ግጥም ተብሎ ለመጠራት ይቸግራል። አያ ሙሌ እኔን ካበቀለ አፈርና ውሃ እንዴት ቀለብ ነፍጎ ያደርገናል ድሃ? ብሎ ሲቀኝ በስንኙ መጨረሻ ላይ ባሉ ተመሳሳይ ሃ ፊደላት ውስጥ አ የሚል ሙዚቃዊ ድምጸት አለ።እነዚህ ሁለት ስንኞች አንዳች ውበትን ለመጎናጸፍና ግጥም ለመሰኘት የቃል ወይም የድምጸት ወይም ደግሞ የፊደላት ተመሳስሎት በቤት መድፊያውና በቤት መምቻው ላይ መኖር አለበት። ለዚህ ነው ከላይ ድግግሞሽ የግድ ነው ማለቱ። ከላይ የጠቀስነው ቻንድራስካራም Repetition is a rhetorical device. But it should not be studied as only a technique. It has psychological implications ማለቱ። ምክንያቱን ግጥማዊ ድግግሞሽን እንደ አንድ ቴክኒክ ብቻ የምንማረው ሳይሆን ስነልቦናዊ ተጽእኖም ለማሳደር ሲባል ተግባራዊ የሚደረግ በመሆኑ ነው። በስነጽሑፍ ላይም ተግባራዊ ለማድረግ ከፍ ያለ ምክንያትና ችሎታ የሚጠይቀው ይሄ ጠጣርነቱ ግድ ስለሚለው ነው። ቻንድራስካራ “Repetition of all kinds necessitates the arrangement of words and lines in a pattern that creates a structure. This structure in turn makes the poem an object of aesthetic appreciation. Repetition draws the attention of the reader to the language itself. It provides ‘literariness’ to the text there by making it different from ordinary speech ሲልም ያክላል። 116 10 12 11 13 Iago in William Shakespeare’s Othello, Act 1, scene 3 እኔ መዩ ወርቅ እዮቤልዩ ሙሉጌታ ተስፋዬ - የነቢያት ጉባኤ። The Significance of Repetition in Poetry by K. Chandrasekhara Rao Seminar Paper ibid 10 11 12 13
126 ውስጠት ከገጣሚና መምህር እንዲሁም ፎክሎርስት ሠይፉ መታፈሪያ ፍሬው ግጥሞች ውስጥ አንዷ ናት።በሃገራችን ከታተሙ ምርጥ የግጥም መድብሎች ውስጥ አንደኛዋ ናት ቢሉ ማጋነን አይሆንም። በአጻጻፍ ይትባህሏም ይሁን በግጥማዊ ቅርጽ የራሷ የሆኑ ቀለሞች አሏት ። አገባባዊ ድጋምን ከውስጠት የግጥም መድብል አንጻር በሶስት ዋና ዋና ዘርፎች ከፋፍለን ለማየት እንሞክራለን። ይሄም ማለት ገጣሚው አገባባዊ ድጋምን ለምን ዓላማ ተጠቀመው ? ምንን አጽንኦት ለመስጠት መሳሪያ አደረገው የሚለውን ለመፈከር እንሞክራለን። ከላይ የተጠቀሱት በውስጠት ላይ ተግባራዊ የተደረጉት ሶስቱ የአገባባዊ ድጋም ተልዕኮዎች አንክሮ፤ ውስጠት እና ሂደት ናቸው። አንድ በአንድ እንዴት ከግጥሙ አንጻር እንደተጠቀሟቸው እንይ። ሀ / አንክሮ አንክሮ ማለት አንድን ጉዳይ ከፍ ያለ ትኩረት የመስጠት ተልዕኮ ነው። አጽንኦት የሚሰጠውን ጉዳይም በኪናዊ ድግግሞሽ ከሰዎች ልቦና ውስጥ ለማድረስ የሚደረግ የቃላት መዋደቅ ነው። ገጣሚው ስል መንፈሳቸውን፣ የቃላት ህያው ሃብታቸውን ተጠቅመው፤ የቃላትን የሃረጋትንና የአገባብን ጉልበት ተመርኩዘው ሊያሰርጹት የሚሹትን የሃሳብ ነጥብ በኃይለ ቃል ተረማምደው ከግብ ያደርሳሉ። “ ሰባ ሰማኒያ” በሚሰኝ ግጥማቸው የእድሜን መገስገስና የትናንትናን የውበት ከፍታ ለመግለጽ በመጀመሪያው አርኬ ላይ እንዲህ ሲሉ ይጀምራሉ። እንዴት---እንዴት--እንዴት --ሙዋሸሸ፥ አበባ የሁዋሊት ሁዋሊቱን ሸሸ፥ ውስጠትሽ ሽብሽብ ብሎ ቀረ፥ ቆዳሽ የፊትሽ እንዲያ ሙሉ የነበር እንዲያ ሙሉ፥ የልጅነትሽ ጸዳልሽ፤ በቀድሞ ተማሪዎቻቸው ዘንድ አብዬ ሰይፉ እየተባሉ ይጠራሉ። ወደ ስድስት የግጥም መድብሎችን ያሳተሙና ወደ ሶስት የሚጠጉ ያልታተሙ የግጥም መድብሎችን አዘጋጅተዋል፣ የቋንቋ ሊቅ፣ ገጣሚ፣ ሃያሲ፣ የፎክሎር ተመራማሪና ለረጅም ዓመታት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በቋንቋ መምህርነት ያገለገሉ ረዳት ፕሮፌሰር ነበሩ። በካርቱም ዩኒቨርሲቲ የእስያና አፍሪካ ጥናት ተቋም ውስጥ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የፎክሎር ተመራቂ ናቸው፣ የማስተርስ ዲግሪያቸው የሰሩት እዚያው ነው። በኋላም በ 1984 ከተባረሩ 42 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ውስጥ አንዱ ናቸው። በስደት በሚኖሩበት አሜሪካ ህይወታቸው ካለፈ ጥቅምት ሁለት ዓመት አለፈው። (ምንጭ- ታናሽ ወንድማቸው ብርጋዴር ጄኔራል መስፍን ኃይሌ፥ የቀድሞ ተማሪያቸውና በጀርመን የሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና ኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል የፎክሎር መምህር ዶ /ር ጌቴ ገላዬ እንዲሁም የቀድሞ ተማሪያቸው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ህዳር 2014 ከዶቼ ቬለ እና ከ VOA ጋር ካደረጉት ቃለ መጠይቅ ተቀንጭቦ የተወሰድ ) (ገጽ 17-18) አጽንኦት የእኔ 14 15 16 ውስጠት 14 15 16
136 እያለ ቁልቁል በሚወርደው ግጥም ውስጥ እንዴት፥ ሁዋሊት፥ እንዲያ ሙሉ የሚሉ ቃላትንና ሃረጋትን እየደጋገሙ የትናንትንና የዛሬን ንጽረት በአንክሮ ልዩነቱን ቁልጭ አድርገው ለማሳየት ይሞክራሉ። የሴትነት ውበት ለልጅ በሚከፈል ህያው ወሮታ ውስጥ ሙሽሽ ብሎ እንደሚቀር አጉልቶ ለማሳየት አገባባዊ ድጋምን ከአንክሮ አንጻር ተጠቅመውታል። ብዙ አገባባዊ ድጋም በሚታይበትና “የህይወት ፍጥርቅታ”17 የሚል ርዕስ ባለው ግጥማቸው ውስጥ በአምስተኛው አርኬ እንዲህ ይላሉ። እና የኔውም ይሄ ነው ይሄው ነው ዶሴዬ ይሄ ነው ገላጭ ዳኛ እማይገኝለት ይሄ ነው ክሴ ይሄ ነው፥ የሚሊዮና ሚሊየን ዓመታት ቅርሴ ሰብአዊ አባዜ በባዶ ሜዳ ባዶ ሜዳ ትካዜ። - - - የህይወትን በተቃራኒ ኃይሎች ውስጥ ገብቶ መላተምና መፈጥረቅ ይሄ ነው እያሉ በተደጋጋሚ አስረግጠው ያሳያሉ። ተደራሲም በቃላት ጉልበት ተመክቶ ሊያሳዩት ወደሚሹት የህይወት እውነታ እንዲንጠራራና እንዲደርስላቸው ውብ ቃላትን እየደጋገሙ ይዋደቃሉ። “ከስፍር ባሻገር”18 በሚለው ሌላው ግጥማቸውም የውበትን አይሰፈሬነት አደግድገው ያመሰጥራሉ። ያበቦች ቀለማምነት ያበቦች፥ ችቦ ድምቀት ውበት እሱ ውበት ነው እሱ ውበት በእፍኝ የማይሰፈር፥ እማይመተር በስንዝር እማይለካ እማይነካ፤ - - - እያለ በሚወርደው ግጥማቸው የአበቦችን ውበት ከምንም ስፍር ወጥተን እንድናይላቸው ይማጸናሉ።እሱ ውበት ነው እንጂ ሌላ አይደለም እያለ የሚጠቁምን ታላቅ የቅኔ መምህር ይመስላሉ። አፉን እንዳልፈታ ልጅና፥ ልጁን ደግሞ ንግግር እንደሚያስተምር አባት እየደጋገሙ እሱ ውበት ነው ማለታቸው አንድም ከስሜታቸው እንደርስ ዘንድ፤ አንድም ደግሞ ኪኑ በፈጠረላቸው የድግግሞሽ ህግ አስረግጠው እውነቱን እንካችሁ ማለታቸው ነው።የዚህንም ገፊ ምክንያታቸውን ዝቅ ብለው አይሰፈሬነቱን፥ አይመተሬነቱን አጉልተው አሳይተውናል። *** 17(ገጽ 21-23) 18(ገጽ 51)
146 ለ / ውስጠት ውስጠት የግጥም መድብሉ መጠሪያ ስም ነው። ለዚህም መግቢያቸው ላይ “ርዕሱን አስመልክቶ” በሚል ቀዳሚ ቃላቸው ላይ አንዳንድ ነገሮች አንስተዋል። ከዚህም ውስጥ ለዚህ ጽሑፍ የሚያስፈልገንን ጠቅሰን ወደ ዋና ጉዳያችን እንለፍ። ውስጠት ማለት “ወሰጠ” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ነው። ትርጉሙም በውስጥ መሆን፥ ወደ ውስጥ መግባት፥ መክበብ፥መካከል ማለት እንደሆነ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ይነግረናል። ውስጠትም የአንድ ነገር በአንዱ ውስጥ መሆንን ይወክላል ይላሉ። ለምሳሌ ጠላና አንኮላን ብንወስድ የጠላው በአንኮላው ውስጥ መሆንና፥ አንኮላው ደግሞ ጠላውን በውስጡ መያዝ ውስጠት ይባላል ይላሉ። ከዚህም በመነሳት የአንዱን በአንዱ ውስጥ ተወሳስጦ መኖርን በግጥማቸው ውስጥ በአገባባዊ ድጋም መልክ እንዴት እንደተጠቀሙበት መፈተሽ እንችላለን። “ተፈጥሮ ብልጠቱዋ”19 በሚለው ግጥማቸው የመጀመሪያው አርኬ እንዲህ ይላሉ። አንዱም፥ አንዱም፥ አንዱም፥ አንዱም የነጠላዎች ድግምግም ተዳምሮ ከምርምር ቃላት አካል ቀምሮ የተፈጥሮ፥ ተፈጥሮ፥ ተፈጥሮ - - - እያለ ይወድርዳል። በዚህ ግጥማቸው ውስጥ “የውስጠትን” ጽንሰ ሃሳብ በተፈጥሮ መካከል እንዴት እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል። አንዱ ነጠላ ዘአካል በራሱ የቆመ ሆኖ ከሌሎች ጋር ያለውን መዛመድና መጋመድ ያመላክታሉ። ከፍ ሲልም የተፈጥሮን ትስስሮሽ ከምላተ አካል ቁመና ጋር እያሰናሰሉ ይቀኛሉ። በዚሁ ግጥም ዝቅ ብለው በሁለተኛው አርኬ እንዲህ ያክላሉ። ተዳምሮዎቹዋ እና ተካቶዎቹዋ የጽንስ፥ ጽንስ፥ ጽንሶችዋ20 ይላል። ታላቁን ተፈጥሮ እንደ አክንባሎ ከላይ ደፍተው የፍጥረታትን ተደማሪነትና ተፈጥሮ ለሚባለው ግዙፍ ሰውነት የእኛን ጽንስነት በውስጥ ለውስጥ እንደ ድር ዘሃ ያያይዙታል። ለዚህም እንደ ዋና መሳሪያ የሚተቀሙት ቃላትንና ሃረጋትን ደጋግሞ መጠቀምን ነው። ተሳክቶላቸዋልም። *** ሐ / ሂደት ሌላው በውስጠት የግጥም መድብል ውስጥ አገባባዊ ድጋምን ገጣሚው አጥብቀው የተጠቀሙት ሂደትን ለማመከት ነው። የነገሮችን በጊዜ ሃዲድ ላይ ያለ መትመም ለመግለጽ፤ የተፈጥሮን በሰዓት ሰረገላ ’መነፍላሰስን ለማንጸር፥ የገጠመኞችን ወይም የሁነትን ሂያጅነትና ተራማጅነት ለማንጸር በቃላት ሲጠበቡ ይታያል። እንዲሁም የነገሮችን የቅጥልጥሎሽ አንድምታ ለማጉላት በእጅጉ ተክነውበታል። እንዲያውም አገባባዊ ድጋምን ያዘወተሩት የክዋኔዎችን ሂደት ለመግለጽ ነው ማለት እንችላለን። በብዛትም ይሁን በተደጋጋሚነት ከሌሎች በበለጠ ሂደትን ወካይ ሆኖ ቀርቧል። 19(ገጽ 18-25) 20 ዝኒ ከማሁ
156 “ ልጃገረድ”21 በሚለው ግጥማቸው የልጃገረዷን የእርምጃ ስልት በሙዚቃ ቅኝት መስለው እንዲህ ተቀኝተዋል። በንጃልሽ እንጃልሽ ጠባቸው፥ ስትሄደው ድምጻቸው አለንም---የለንም! አለንም---የለንም! አለንም---የለንም! አለንም---የለንም! -------- ምስኪን ልጃገረድ ሴት ልጅ ሆኖ መወለድ - - - ይላሉ። እዚህ ግጥም ላይ የሰራ አካላቷ እንጃልሽ እንጃልሽ እየተባባሉ የእርምጃዋን ስልተ ምት ተከትለው ሲያረግዱ በዓይነ ህሊናችን መሣሉ አይቀርም። አለንም የለንም እያሉ የሚወርዱ ስንኞች የልጃገረዷን ቁመናና ተውረግራጊ አረማመድ ቁልጭ አድርገው ያስቀምጣሉ። ይሄ መውረግረግ ደግሞ ሂደትን የተከተለ መሆኑን ለማሳየት አገባባዊ ድጋምን ዋና መሳሪያቸው አድርገው መጠቀማቸው ውስጠ ሃሳባቸውን ግዘፍ ነስቶ ለአንባቢ እንዲደርስ አድርጎላቸዋል። “ የፒያኖ ላይ ምጥ ”22 በሚል ርዕስ በከተቡት ሌላ ግጥማቸው ላይ የፒያኖውን ቁልፎች እየተከተለ የሚነጉደውን ተስረቅራቂ የድምጽ ፍሰት እንዲህ ያመሰጥሩታል። “ድን” እየመለሰ፣ እየመለሰ “ድን” “ድን-ድን”፥ ድን እና ድን አንዲቱዋን ኖታ ብቻ መባቻ መጣሁ--መጣሁ ለሚለው ዜማ መክፈቻ ” - - - እያለ ይወርዳል። ይሄ የድንድንታ ቅጥልጥሎሽ ከከያኒው ምናብ ተተርትሮ ለሚወጣው ዜማ በር መክፈቻ ነው። ሂደቱ እስከ ተቀመረ ዜማ ድረስ -ዜማው እስከ ዘለዓለማዊ የፍጡራን ነፍስ ድረስ መሻገር ነው። በዚህ ድን ድን ውስጥ ዘለዓለምን የሚያህል የድምጸት መንገድ አለ። በእሱ መንገድ ተራምዶ ነው ከተሸመነ የዜማ ልባስ መድረስ የሚቻለው። ድን ድንታውን በድጋም ቀምሮ ሊል የሚሻውን የመንፈስ ፍልቅቅታ ማድረሱ እሙን ነውና አጃይብ ብለን እንሻገር። 21(ገጽ 32-34) 22(ገጽ-36)
166 “የፍጻሜው ባላደራ”23 በሚለው የሟችንና የቀባሪን ጉዞ በተቀኑበት ተጓዥ ግጥማቸው የግጥምን አገባባዊ ድጋም እንዲህ ተጠቅመውታል። ጌታ ሞት እፊት--እፊት--እፊት--እፊት ሁዋላ ሁዋላው የቀባሪው ትመት ረመድመድ---ረመድመድ ረመድመድ---ረመድመድ እያለ ይወርዳል። በዚህ ግጥም ላይ አንዳች እንደ ገብረ ጉንዳን ተያይዞ የሚጥመለመልን የሰዎች ጉዞ በምናባችን ቁልጭ አድርጎ እንዲቀረጽ ያደርገዋል። ከዚህ የቀባሪ ረገዳ ሂደትን በድግግሞሽ መግለጽ የሚችል ኪናዊ ውበት መፍጠር መቻል የግጥም መሰጠትን ይጠይቃል። በተመሳሳይ “ያንድ አቅጣጫ ጩኸት”24 በሚለው ግጥም ላይም መሰል የሂደት አገባባዊ ድግግሞሽ ይገኛል። ዝቅ ወደ ታች--ታች--እታች--ዝቅ ዝቅዝቅ እኩል ለኩሉን ታጥፎ እና ካፈር አላክፎ - እያለ ይቀጥላል። ሌላም “እርካታ”25 በሚሰኝ ግጥም ላይ መሰል ሂደት በግልጽ ይታያል። እየቀጠነ ሄደ እየቀጠነ ጭብጥ እየመጠነ ውፍረቱ እየተወረደደ ቅርፊቱ እየሰለለ ክርክራቱ ግንድ ንጣቱ ቀቅ--ቀቅ--ቀቅ እና ው--ድ--ቅ ዘፍ ግርስስ--ተገረሰሰ ይቀጥላል ይሄ የአንድ እድሜያማ የዛፍ መቆረጥን ሂደት የሚያሳይ የሚመስል ግጥም፤ የዛፉ ግንድ በመጥረቢያ እየተቦደሰ፤ ግንዱም እየቀጠነ መሄዱን ግሩም በሆነ አገባባዊ ድጋም ያሳያል። ይሄ አይዛፍ መቁረጥና የግንድ እየተቀረደደ መሄድ ከተራ ግድን ቆረጣ ባሻገር የቆራጭንና የተቆራጭን እጣ ፋንታ የሚፈክር መሆኑ እሙን ነው። እሱንም ተምሳሌታዊ በሆነ መልኩ እንዲህ ሲገለጽ ደስ ያሰኛል።እንዲሁም “ምርጫ ያለው ይመስል”26 በሚለው ግጥም ውስጥ እንዲህ የሚሉ ስንኞች አሉ። እራሱ --ከራሱ ጋራ-ራሱ ጋራ የያዘ መስሎ ሙግት ግራ ቀኝ አያይ ግራ ቀኝ አይገላመጥ ውደ ሁዋላው አይመለከት ወደ ፊት--ፊቱ ብቻ ወደ ፊት ፊቱ ሁዋላ ሁዋላው ፍየል፤ ፍየል ሁዋላ ሁዋላው ታብቶበት በሆነ ስበት ገመድ ታች እየነዳለት ዘመድ በንዲያ-ንዲያ ሄዱ፤ ሄዱ በንዲያ ንዲያ ተያይዘው 23(ገጽ 42-45) 24(ገጽ-58) 25(ገጽ 60) 26(ገጽ 64)
176 እያለ ይወርዳል። ይሄ ግጥም የአንድን ፍየልና የአራጅን ጉዞ ምስል ከሳች በሆነ መልኩ የሚያሳይ ግጥም ነው። ታራጅ መታረዱን ሳያውቅ በገመድ ተይዞ የሚያደርገውን ወደ ሞት ግስጋሴና መፋጠን፣ የአራጅንም የሆዱን በሆዱ ይዞ ፍየሉን በገምድ አስሮ መብከንከን ያስቃኘናል። የግጥሙ ሃሳብ ከፍየልና አራጅ ግንኙነት ባሻገር የሚንጠራራ የፍጥረዓለማትን የህይወት መልክ የሚፈክር አንዳች የሂደት ትዕይንት ነው። ሲጠቀለል ከላይ በዘረዘርናቸው ግጥሞች ለማየት እንደሞከርነው ገጣሚ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬ የግጥም አገባባዊ ድጋም በመባል የሚታወቀውን አንድ የአገጣጠም ዘዴ ተጠቅመው ሃሳባቸውን ከዳር አድርሰዋል። ቃላት እየደረቱ አንዳች ድምጸትን ከመፍጠር ባለፈ ታላቅ ሰዋዊ ብሎም ባለቅኔያዊ ተልዕኮን እንደተሸከመ ባለሟል ጉዟቸውን ከዳር አድርሰዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። እንደ ምሳሌ ውስጠት የግጥም መድብላቸውን ተመለከትን እንጂ በሌሎች የእሳቸው የግጥም መድብሎችም ይሁን በሌሎች የሃገራችን ገጣሚዎች የግጥም ስራዎች ውስጥ መሰል ቴክኒኮችና ተልዕኮዎች እንዳሉ እሙን ነው። እኛም ይሄንን እንደ መንደርደሪያ ተመልክተን ቀሪዎቹን የግጥም ስራዎች በተለያየ አረዳድ እያየን ህያው ስራቸውን እንድንመሰክር እያሳሰብሁ በቻንድራስካራ መደምደሚያ ልሰናበት። The aura that is created by the usage of repetition cannot be achieved through any other device. It has the ability of making a simple sentence sound like a dramatic one. It enhances the beauty of a sentence and stresses on the point of main significance. Repetition often uses word associations to express the ideas and emotions in an indirect manner. 27The Significance of Repetition in Poetry by K. Chandrasekhara Rao Seminar Paper
ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ እና ከዚያም በላይ ዘመናት ታሪክ ባለቤት ናት ቢባልም፥ በጣት ከሚቆጠሩ ታሪካዊ ከተሞቿ ውስጥ አብዛኞቹ የተመሰረቱት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ነው። ከተሞች የተመሰረቱት ለገዢዎች የግዛት ማስፋፋትና ማስገበር የሚስማሙ ምቹ ቦታዎችን በመምረጥ ነው። የግዛቶቹ አስተዳዳሪዎች ለሚቆረቁሯቸው ከተሞች ወይም ለሚቀመጡባቸው ነባር ከተሞች ድምቀት የሚሆኑት የሚያሳንጿቸው ቤተመንግስቶች ውበትና የሚመርጧቸው ቦታዎች ናቸው ። ከእነዚህ ከተሞች መካከል ራስ ሚካኤል (የኋላው ንጉስ) በ1875 የቀድሞ ዋና መቀመጫቸውን ተንታን ትተው ወደ ቆረቆሯት ከተማ፥ የዛሬዋ የወሎ መዲና ወደ ሆነችው ደሴ አምርቻለሁ። እነሆ የግል ምልከታዬን ላካፍላችሁ። ደሴ በንግድ የተጨናነቀች ሁለተኛዋ መርካቶ ነች። የሰሜን መተላለፊያ፥ የኡለማዎች መፍለቂያ፥ ለዝየራ የአረብ ገንዳ ማዝገሚያ፥ መርሳ አባ ጌትየን መማፀኛ፥ የግሸን ማዝገሚያ፥ ወደ ፅዮን መቃኛ ልዩ ድባብ ፈጣሪ ናት። የኪነት እምብርት፥ ወደ መቅደላ ማዘቅዘቂያ፥ ወሎ ደሴ የቆንጆ መፍለቂያ፥ የሙሀባዎች መዲና፥ የፍልቅልቅ እናቶች መንደር፥ የልበ ቡቡ አባቶች መስክ ነች። ደሴ ቀዝቃዛ ነች። ዙሪያዋን የከበቧት ተራሮች በክንፎቻቸው ሸፋፍነው እንደ ሙሽራ አጅበዋታል። ጀንበር ዘቅዘቅ ስትል ወደ ጄሜ ኮረብታ አቀናሁ። ጄሜ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ በእይታ ቁጥጥር (አልፎ በቅርብ እርቀት ያሉ አካባቢዎችን በግልፅ ለማየት) ስር ለማዋል ሁነኛ ቦታ ነው። የንጉሥ ሚካኤል ቤተመንግሥት “አይጠየፍ አዳራሽ” መገኛም ነው። ጉልበት ያዝ የምታደርገውን አቀበት መውጣት ስጀምር የከተማዋን ጓዳ ጎርጓዳዋ ቁልቁል እያየሁ አቀበቷን ጨርሸ ከቤተመንግሥቱ በር አረፍ አልሁ። አካባቢው አመሻሽ ላይ ልዩ መስህብ አለው። ከታች ከወደ ባቲ አቅጣጫ በቀስታ ሽው እያለ በስሱ የሚነፍሰው ዳሳሽ ነፍስ ውስጥን ያሞቃል። በከተማዋ ላይ ደልገመን ጥሎ ለእጅ ሰላምታ የቀረበውን የጦሳ ተራራን እስከ አዝዋ ገደል በእልፍ ሸንተረራማ ተፈጥሮ የታጀቡ ሁነቶችን እያስተዋሉ ከራስ ጋር የሚያወጉበት ነው። ዝቅተኛ ቦታዎች ከታች የአፋር በረሃ፥ የበረሃ ገነት ገመገሞች፤ ከባቲ እስከ ገራዶ መውጫ በጀምበር ግባት ፀአዳ ውብ መስክ የነፍስን ትህፍስት መቃመስን የሚሰጥ ልዩ ቦታ ነው። አባ ሻንቆን28 አሰብሁት (በጉዞና ስራ የዛለ ሰውነቱ) እዚህ ቦታ ሲቆም ምን ያህል ውስጣዊ ድባብ እንደሚፈጥርለት ያውም በዛ ጀግንነት ንጉሥነትን ደርቦበት ስለ እሱ እኔ ፈገግሁ። ከላኮመንዛ ሰማይ ስር አይተነው ንጉሤ ከላኮመንዛ ሰማይ ስር 28የንጉስ ሚካኤል የፈረስ ስም 186
ዙሪያ ገባውን በመስገብገብ እየቃኘሁ ወደ በሩ አመራሁ። ቤተመንግሥቱ ዙሪያውን በነጭ ግንብ ታጥሮ ነጭ ሽቦ ተጨምሮ ቢያዝም ያ በኖራ እና በእንቁላል የተለሰነ (ልስን) ግንብ መደረማመስ ጀምሯል። ከጥበቃ ነፃ ነው። ግርማው ግን አሁንም አልሸሸውም። በሩን ላልፍ ስል ቆምሁ። ሰውነቴን የሚነዝር ስሜት ተሰማኝ... በሀሳቤ ሸማ ጣል ያደረጉና ጦር ከጋሻ ያነገቱ ግራ ቀኝ ቀጥ ብለው የቆሙ ዘቦችን እያሰብሁ ሰፊውን ጉበን ተራምጀ ወደ ውስጥ ገባሁ። ቤተመንግሥቱ ከተገነባ 140 ዓመታትን ደፍኗል። እድሜ ጠገብነቱና ወናነቱ ወደ እርጅና ቢወስዱትም ግርማ ሞገሱ ግን አልተገፈፈም። የተሰራበት ውብ የስነ-ህንፃ ጥበብ በግርምት እጅን አፍ ላይ ያስጭናል። ከሌሎች በተለየ ሁኔታ የተንጣለለው አይጠየፍ አዳራሽ የግብር ማብያ ሲሆን ከ3000 ሰው በላይ የመያዝ አቅም አለው። በጊዜው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለምርጫ ያስተናግድ ነበር። የአይጠየፍ አዳራሽን ጣራ ጠፈጠፍ መውረጃ ስንመለከት፥ በአንድ ጎኑ ያለው ጠፈጠፍ(ጣራ) ያጠራቀመውን የዝናብ ውሃ ለአዋሽ ገባሪ ወንዞች ሲያዋጣ በሌላኛው ያለው ደግሞ ለአባይ ገባሪዎች ጀባ ይላል። ቤተመንግስቱን ናፍቀውት እንደሰነበቱ ህፃን ልጅ ሁሉ አይቸም ዳስሸም አልጠግበው አልሁ። የሆነ ጊዜ አብረን የቦረቅን(የቦረቅንበት) ከዚያም ለብዙ ዘመን ተነፋፍቀን እንደቆየን ባልንጀራ ያለ ስሜት .... ። አሳዘነኝ! ብቻውን እንደቀረ ብቸኛ ሰው፥ ወይም በሰው መንጋ መካከል ሁኖ ሰው እንደመራብ (መናፈቅ).... መሸሸጊያ ጥግ ያጣ መሰለኝ። “እሸሸግበት ጥግ አጣሁ”29 እንዳለው ሎሬቱ አፍ አውጥቶ ባይናገርም መሸሸጊያ ጥግ ማጣቱን መራቆቱ ይናገራል። አዳራሹ አንድ ፕሮግራም ቀርቦበት ሳይጠረግ የቀረው ጉዝጓዝ አርቲ፣ጠጀ ሳርና ቄጤማ ተዝረክርኮ ወለሉን ሞልቶታል። አባ ሻንቆ ያንን ዠርጋዳ ሽንጡን ያዝ አድርጎ የተንጎማለለበትን ግቢ ያለ ከልካይ ከታች እስከ ላይ ዋኘሁበት። ከውብ መታጠቢያ ገንዳዎች እስከ ልጅ እያሱ እልፍኝ፥ ከችሎት መሰየሚያ እስከ ጸሎት ቤት፥ ከማድ ቤት(ከምግብ ማብሰያ) እስከ መኝታ ቤቶች፥ከእንግዳ መቀበያ የምድር ቤት እስር ቤት ድረስ....። በየ ጥጋጥጉ ያሉ ቄንጠኛ የዚያ ዘመን ብቻ ሳይሆን አሁንም ታይተው የማይጠገቡ ቤቶች መሰረቶቻቸው እየከዳቸው መደረማመስ ጀምረዋል። ባለ ጥዑም መአዛ ምግቦች እየተሰሩ የሚወጡበት የምግብ ማዘጋጃው አፈር ከድሜ በልቶ ወደ አመድነት ለመቀየር ከአንድ እንቁጣጣሽ የበለጠ እድሜ አያሻውም። ያኔ ለመንካት የሚያሳሱት የመታጠቢያ ገንዳዎች ንጣታቸው አሁንም ለእያሱ እንደተዘጋጁበት ዘመን ቢሆንም፥ ከቦታቸው ተነቃቅለው የውሃ መተላለፊያቸውና መመጠኛቸው ወላልቆ ሸረሪት አድርቶባቸዋል። ታስሮ ውሎ የተራበ በሬ ተፈቶ ወደ ብዙ ሳር እንደተለቀቀ ዓይን አዋጅ ሁኖብኝ ከላይ ታች እየሮጥሁ የራሴን ዘመን ትውልድ ናቅሁኝ። አቧራቸውን አራግፎና ለቱሪስት ምቹ አድርጎ አገርን ከማስተዋወቅ ባሻገር ገቢ ማስገባት ሲቻል................። ግን ለዚያ የሚያበቃ ለስራ የታጠቀ ወኔ አይሸመት ነገር። በእንደዚህ አይነት ውብ የተፈጥሮ ገጸ-በረከት የታደለ ቦታ ላይ ሰርተው ያወረሱንን ቅርስ ማደስ ባንችል ማፅዳት እንደት ተሳነን? ቢሮ ወንበር ሲያሞቅ የሚውለውን የቱሪዝም ዘርፉን ትተነው፥ እዛው ኮረብታ ስር ከቧንቧ ውሃ እስከ አረብ ገንዳ ድረስ ተደርድሮ የሚውለው ወጣት ባለ ትኩስ ጉልበቱ “ጦሳ ተራራ” ላይ ውብ ቤተመንግሥት መገንባት ቢሳነው እንዴት አይጠየፍን መጥረጊያ ሞራል አጣ? 196 29ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን (ሰቆቃዎ ጴጥሮስ)
ከቤተመንግስቱ ጋር ተያይዛ የተሰራችውን ቤተክርስቲያን ለመሳለም ወደ ቦታው የሚመጡ ምዕመናን፥ ከጸሎት በኋላ ወደ ቤተመንግሥቱ ውስጥ ጎራ ይላሉ። ከአድማስ አድማስ በሀሳብና በእይታ እየተጓዙ ለማብሰልሰልም ገብተው አረፍ ይላሉ። ከእዚያ ባሻገርነት ያለውን ጥቅም ግን የተረዳ ያለ አይመስልም። በእጅ የያዙት እንዲሉ........። የከተማውን በሰው መከበብ የሸሹ ጥንዶች ወደ ኮረብታው ጎራ ይላሉ። ከታች ከበረሃው ከአፍደራ እየተነሳ በስሱ ሽው እያለ የሚነፍሰውን ውብ ነፍሻ አየር እየማጉ ውብ ውብ የፍቅር ቃላትን ተወራውረው ቁልቁለቷን ያዘግማሉ። አይጠየፍ ቤተመንግሥት ግን ከቀን ወደ ቀን እንደ አዛውንት ጉልበቱ እየደከመ ወደ ነበር ማዝገሙን ከጀመረ ቆይቷል። * * * እየተስለመለመች በመጥፋት ላይ ያለችውን የሚያዝያ ጀንበር ከምህዋሯ ጀምራ እስከ አይጠየፍ ስር የለቀቀችውን ክበቧን እያየሁ፥ ልብን የሚያጠግብ የምህዋሯን ውበት ሳትሰበስብ፥ እንባ እየተናነቀኝ ጉልበቴ ስብር ስብር እያለ ጀሜን ወደ ኋላ ትቼ ቁልቁለቱን መውረድ ጀመርሁ። አይጠየፍን አይቼ የእኔን ትውልድ በመጠየፍ በቀረችኝ ምሽት የተዘጋ በሩንም ቢሆን ለማየት ወደ ወይዘሮ ስሂን አመራሁ ። 206
ይመስለኛል..... ሶስት አዲስአበባ ሙሉ ብልጭልጭ፥ ሁለት ወሎን ያህል ቁሌት፥ ትግራይን ያህል ውበት፥ ናዝሬትን ያህል ለብ ያለ ስካር የሰሩት የሰመመን ሀሴት ይመስለኛል:: እንደ ፀሐይ ያልበራ፥ እንደጨረቃ ያልደበዘዘ፥ ስስ ብርሃን የተሣለበት ሰፊ ባር፥ የህልም ውስጥ ህልም፥ ቅዠት እና ዱካክ በየአይነት የሚቀርብበት፤ ሁልጊዜም የህልም ውስጥን ህልም አንስቼ በአንድ ትንፋሽ ላጥ አደርጋለሁ። የህልም ቪአይፒ ውስጥ የተመረጠ ህልም አያለሁ። ከሜኑው ላይ እየጨለፍሁ በትንሽ ትንሹ እቀምሳለሁ። ከእናቶቻችን ጥጥ በላይ በነጣ እና በሳሳ ዳመና እየቀዘፍሁ፥ ሩቅ የነበረውን ቅርብ አደርጋለሁ። ያጣሁትን አገኛለሁ። የወደድሁት አጠገብ እሆናለሁ። በሞት የተለየኋቸው እቅፍ መሐል እድር’ እላለሁ:: ደሞ ህልም ምን ምን ይላል? ያልጨረስነውን እንደመቀጠል፥ ሀዘንን እና ልብ ስብራትን እንደ መሻር፥ ልብ መሀል ሙሉ መሆንን፥ ምላስ ላይ መጣፈጥን፥ በደስታ መናወዝን ሁሉ ይላል። ~~ አንድን ነገር ስፈልግ የፍላጎቴ መጠን ልገድበው የማልችለው ኃይለኛ ጉልበት አለው:: የልቤ በርና መስኮቶች አፍነው ለማስቀረት አይችሉትም። ከውስጤ የሚወጣው ኃይል ከፊቴ ያለውን ምንም አይነት ነገር ጥሶ መገኘት ያለበት ቦታ ይገኛል። የፈለግሁትን ብርጭቆም ይሁን ሰው ፊቴ አገኘዋለሁ:: ከዚህ በፊት ይሄ ሁሉ ሆኖ ያውቃል። አያያዙን እና አጨራረሱን ባላውቅበትም የማላሰነብተው ብዙ ከልብ የወጣ ስሜት ያመጣቸው ነገሮች መጥተው ሄደዋል:: ብርጭቆውም ተሰብሯል፤ ሰውም ሄዷል:: እናም በህልሜ ህልም አየሁ። ስቤው የማላውቀው ሰው፥ በቀን ተቀን ውሎዬ የማላገኘው፥ በአካል የማላውቀው ሰው አጠገቤ ነበር:: እንደፍቅረኛ እጄን ሲይዘኝ፤ ዓይን ዓይኔን እያየ ሲያወራኝ፤ ከንፈሬን ሲስመኝ፤ እጁ ተንሸራቶ ከወገቤ ወደዳሌዬ ሲወርድ፤ በደስታ ስሜት የተወጠረች ነፍሴ ከከንፈሩ መሀል በትንሹ እህህ ብላ ራሷን ስታስተነፍስ፤ የከንፈሩ ሜንት ሜንት የሚል ጣዕም ምላሴ ላይ አየር እየሳበ፥ ኮሌታው ላይ በነሰነሳት ሽቶው ከወንድነቱ ጠረን ጋር ተደባልቆ አውዶኝ ገነት እንዲህ እንዲህ ካላለች እልፀድቅም፥ እስክል ቀይ ፊቱ ላይ በተነሰነሰው ፂሙ አንገቴ ዙሪያ ጉንጮቼ ድረስ በደስታ ሲኮልኩለኝ፤ ትልቅ ሰውነቱ ገና ሳያርፍብኝ ግርማው ከብዶኝ፥ በህልሜ ህልም ውስጥ ሆኜ መንቃትን አልፈልግም ብዬ፥ ፊቴ ላይ መልኩ እንደ ሚጨስ ነገር ሲበታተን እንዳልነቃ ዓይኔን ጭምቅ አድርጌ ጨፍኛለሁ:: አያያዙ ከቃል በላይ ነበር ። ማጥበቅ አለበት። መያዝ ነበረበት። እንክብካቤ እና አለሁ ባይነት አለበት:: እንደሌሎች ህልም እልነበረም። ምናልባት ያን ዕለት ስተኛ የህልምን ኤክስትራ ስፔሻል ህልም አዝዤ ነበር የተኛሁት። ህልም ከምን ከምን ነው የተሰራው? ቤዛዊት ዘርይሁን © Antex Sisay 216
206 ይሄ ሲሆን አየሁ። ስነቃ ሰውነቴ ተቃጥሏል። ከረሜላው ካፉ ወድቆ አፈር እንደተለወሰበት ህፃን ክፍት ብሎኛል።የእውነት ይመስል ነበር። መነካካታችን እና ስሜታችን ነፍሴ ድረስ ተሰምቶኛል። ስነቃ የእጁ ዳና ከወገቤ እና ዳሌዬ ላይ አልጠፋም። ሽቶው አፍንጫዬ ላይ ነበር። ጉንጮቼ ላይ ፂሙ የፈጠረብኝ መኮስክክስ በስሱ ያሳክከኛል። ተመልሼ ልተኛ ብሞክርም ማስመሰሌ አልሰራ አለ:: እንዲህ አይነት ነገሮች ግራ ያጋቡኛል። አንዳንዴ ህይወት እኛ ባልገባን መንገድ በሚስጥር የምትሰራ ይመስለኛል:: አንዳንዴ ሳይሆን ብዙ ጊዜ:: የቀን ተቀን ድግግሞሻችንን እንደቅዠት በህልም ከማየት ያለፈ እንዲህ አስቤው የማላውቀውን ሰው ከርቀት ጎትቶ በህልም ማስተዋወቅ ምን ሊባል ይችላል? ሁሉንም በዚች ነፍሴ አሳበብሁት። ነፍሴ ቀልቃላ ናት። እንደማንኛውም አይነት ሰው ኑሮ ለመኖር ስልቹ ነች:: በ”ነው” ወይ “አይሆንም” ለመታጠር አትፈልግም። መሞከር ትወዳለች። መውደቅ ብርቋ አይደለም:: ወይንም ሰውነቴ በድግግሞሽ ዝሎ አእምሮዬ ሲያንቀላፋ ወንደረር ነፍሴ እሺ ብላ አትተኛም። ይመስለኛል........... ይመስለኛል ያለእውቀቴ ብዙ መንገዶች ሄዳለች። በሌለሁበት ወደኋላ ተመልሳ፥ ሳትጠግብ አደግሽ ተብላ የተከለከለችውን የካሬ ድንጋይ ከጣለችበት ሀሙስ ቤት ላይ አንስታ፥ እስከ ቅዳሜ ተጫውታ አርብን ቤት ገዝታለች:: ማርያምን አታረገውም አይባልም። ወይንም እናቷ ጋር ተቀምጣ በ”ሳብ በለው ሳብ በለው የሀሙሱን ፈረስ”30 የወሎ እስክስታዋን አስነክታዋለች። ወይንም ወደፊት ሄዳ ወደፊት የአሁን ምኞቶቿን በድብቅ እየኖረቻቸውና እየተመለሰች ይሆናል። ምናልባት ይሄን ልጅ ቀድማኝ ተዋውቃዋለች። ምናልባት ምንም ባላሰበበት በሌላ ፍቅር መንገድ ላይ ሆኖ ያለፍቃዱ ዓይኑን ስማዋለች:: እጁን ይዛዋለች። ፈገግ ብላ አይታዋለች... ምናለበት .... ይሄኛውን ልታልፈው ብላ መወጠሪያ ገመዷን አላልታዋለች። ምንም ቀልቃላ ብትሆን ራስወዳድነት የለባትምና የሷን ልብ ልትሞላ የሌላውን አትሰብርም... ለዛ ይሆናል ቶሎ የቀሰቀሰችኝ። እንኳን ነቃሁ። 226 30ፍቅራዲስ ነቃጥበብ (ሳብ በለው)
2036 አለመወደድ አድኀኖም ምትኩ Pinterest: -Sad Children Crying Canvas Art ጸጉሯን ጭብርር አድርጋ በቱታና በክፍት ጫማ ትመጣለች፣ ያሻትን ታወራኛለች። በምታወራው የምይዘው አቋም አያስጨንቃትም። ስታወራኝ ፊቴን አታነብም ፣ ነገሬን በቁም ነገረ አትይዘውም። የድሮ ፍቅረኛዋን ኳሊቲ ስትናገር ስለወንድሟ የምታወራ ነው የምትመስለው ። የሰጣትን ስጦታ አይነት ልትነግረኝ ሁላ ትችላለች። እማላቀውን ሰው በቅናቴ ምክንያት እጠላዋለሁ ። ፍሬህይወት ነገሬ ሁሉ ግድ አይሰጣትም። እኔ ... የአለመወደድን ጠረን አውቀዋለሁ። ያለመጥቀምን ስሜት ከየትኛውም መጥፎ ሁኔታ በላይ አልወደውም። የአልወድህም ምልክት ስታሳየኝ ልቤ ላይ የማልወደው ስሜት ተንከላወሰ። ጠፋሁባት። በሌላ ምክንያት ከሆነ ብዬ፣ እለታዊ ሙድ ከሆነ ብዬ፣ ተናዳብኝ ይሆናል ብዬ፣ እጅግ ብዙ ቆይቼ ከሁለት ቀን በኋላ አግኝቻት ስሜቷን ሰለልሁት። ከአስር ደቂቃ በኃላ እንደተገናኘን ነበር ሁኔታዋ፣ ዓይኗ ላይ ያለው መሰልቸት በጉልህ የተነበበኝ። ሁኔታዋ ገፈተረኝ። አገፈታተሯ እና አወዳደቄ ሳያዘጋጁ ከድንገተኛ መንጋለል ስሜቱ ይበልጣል። ህመሜ በማዘን አይነት እፊቴ ላይ የሚነበብ ይመስለኛል። ጠፋሁ!! ታግሼ ለመወደድ ብጥር፣ እኔነቴን ባሳያት፣ ፍቅሬ የእውነት እንደሆነ፣ በምንም ሁኔታዋ አብሬአት ሆኜ ባሳያት ጥሩ ነበር። አለመወደድን መጋፈጥ አልችልም። አለመወደድን ከምጋፈጠው የምወደውን ነገር ሳጣ የሚሰማኝን ደባሪ ስሜት መቋቋምን እመርጣለሁ። ጉልምስናችን የልጅነታችን ባርያም አይደል?! አለመወደድን እንድታገስ ልጅነቴ አይፈቅድልኝም። --- አስራ አንድ ዓመት እንደሞላኝ እናቴን መኪና ገጭቶ ገደለብኝ። ጋሽ አበራ የሚባል ዘመዳችን እሳድግሃለሁ ብሎ ወሰደኝ። የእናቴ የነበረው የቀበሌ ቤት በሰባ ብር ተከራየ። እሱ እና ዘመዶቹ ለሁለት ሳምንት ከንፈራቸውን እየመጠጡ እኔን ለመንከባከብ ሞከሩ። ምግብ ብላ፤ እናትህ ኖራ ቢሆን፣ እያሉ በተቻላቸው መጠን አቀማጠሉኝ፤ ተቀማጠልኹ። ጋሽ አበራ የኔ እኩያ ልጆች አሉት። ከእነሱ አንፃር በብስለት እኔ ትልቅዬ ሰውዬ ነበርሁ። እናቴ የቆጥ የባጡን ታወራኝ ስለነበር የማይገባኝ ነገር ያለ አይመስለኝም።
2046 የዘመዴ ቤት ሁለት ዓመት ከሁለት ወር አካባቢ ተቀመጥሁ ። ሁለት ዓመት ተሰቃየሁ። ልጅ ስለምመስላቸው ብልግናቸውን ጥበብ አያለብሱትም ነበር። የሚያደርጉት ነገር ሁሉም ይገባኝ ነበር። አድራጎቱም፣ የድርጊቱ ምክንያትም፣ ስለሚገባኝ እታመማለሁ። ጥጋበኛ ነው፣ የልጅ መርዝ፣ ውለታ ቢስ ይሉኛል። አሁን የአስራ ሶስት የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ እንዲህ ይባላል?! በእርግጥ የሃያ ሶስት ዓመት ልጅ አክል ነበር። በደላቸው አጥንቴ ውስጥ ተቸነከረ። ስንት የማይገባኝ የሚመስላቸው አድሎ ደምስሬ ውስጥ ተተበተበ። እናቴ ናፈቀቺኝ ...ድሃዋ እናቴ፣ ጓደኛዬ፣ ናፈቀቺኝ። ምግብ እንጂ ፍቅር አጉላብኝ የማታቀው እናቴ ናፈቀቺኝ። የዓለም ትልቁ መከራ አለመወደድ ነው! ኖ አይደለም። ነገሬ የሚል ሰው ማጣት ነው። አይደለም። የማትረባ እንደሆንህ ሁሉም ሲስማማብህ ያለው ስሜት ነው። ይሄ ሁሉ አንድ ላይ ሲመጣ ሌላ ሲዖ እንደሌለ ይገለፅልሃል! በመገፋት ብዛት እግዛቤርን አዋርቼው አውቃለሁ .... እሱ ያኔ መልስ አይመለሰልኝም ነበር። እኩያዬን ቱቦ ውስጥ የወደቀበትን ኳስ ለምን አወጣህ ብለው ይገርፉታል። እኔን ቱቦውን አፅዳ ይሉኛል። በደንብ አላፀዳኸውም ብለውም ይከሱኛል። በመጨረሻ ወደ ቤቴ ቀጥ ብዬ ሔድሁ። በሰባ ብር የተከራየውን ሰውዬ ውጣልኝ ብዬ ለመንሁት። ከአምስት ቀን በኋላ እወጣለሁ አለኝ። አምስት ቀን በረንዳ አደርሁ። ከአምስት ቀን በኃላ ውጣልኝ ስለው እወጣለሁ እንዳለም እረስቶት ነበር። እኔ አምስት ቀናት እንዲሞላልኝ ሰዓት ስቆጥር እንደከረምሁ አላወቀም። የአንዳንድ ቀጠሮ ግዝፈት ሁኔታችን ላይ የተንጠለጠለ ነው!! ሁኔታዬን ሲያይ አብረን እንኑር አለኝ። እምቢ አልሁት። ጎረቤቶቼን ሰብስቤ አስለመንሁት። በስንት አማላጅ ወጣልኝ። ብቻዬን መኖር ጀመርሁ። ተሸከምሁ ፣ተላክሁ ……. ሊስትሮ ጠረግሁ። መከራ በላሁ። የማይወግንልኝ ሳይኖር ብቻዬን የማልችለውን እየተሸከምሁ፤ ሸክሜ ሲወድቅብኝ አሸካሚዬ ሲሰድበኝ፤ ጫማ ስጠርግ የጫማውን ቀለም ካልሲ አስነክቼ ሲመቱኝ፤ ልጅነቴ አሳዝኖቸው እሰጥሃለሁ ካሉኝ በላይ እየሰጡኝ፤ ቀን ቀን አስፋልት ላይ ማታማታ የእናቴ ፍርስርስ ያለች ጓጆ ውስጥ እያደርሁ፤ ሲከፋኝ እያለቀስሁ፥ እግዛቤርን እያናገርሁት አደግሁኝ። አምላኬ ሁሉን እያየ ነበር ። ለሁሉም ወሮበላ ሱሰኛ ሌባ ነበርሁ ። ክፉ ነገር ሲከሰት እኔ የመጀመርያ ተጠርጣሪ ነኝ ። መጀመርያ ሰሞን ስጠረጠር ደምስሬ ተገታርትሮ እያለቀስሁ አስረዳ ነበር። እናቴ ስለእውነት እና ስለ እምነት ያሳየችኝን እነሱ የት ያውቃሉ? በቆይታ ብዛት አለመታመን የሚያናድደኝ አልሆን አለ። በጥርጣሬያቸው አለመናደዴ ለሌብነቴ እንደማስረጃ ያጣቅሱታል። የልቤን ጌታ ያውቃል እል ነበር። ክፉ ቀኔን በጌታዬ ድጋፍ ተሻገርሁ ። ዛሬ በቂ አለመወደድ እና አለመ’ፈለግ ስላስተናገድሁ አለመወደድን ፊት ለፊት መጋፈጥ አይሆንልኝም ።
አባት ልጁን ይዞ እየሄደ እያለ፥ በመንገዳቸው ዛፎችን ያያሉ። ከዚያም ልጁ አባቱን “አባቴ ይሄንን ዛፍ አነቃንቄ ቅጠሎቹን ማንቀሳቀስ እችላለሁ?”ብሎ ጠየቀው። አባቱም “አዎ! ሙሉ አቅምህን ከተጠቀምህ በደንብ ትችላለህ” አለው። ልጁ አባቱ እንዳለው ወደ ዛፉ ይሄድና ዛፉን መነቅነቅ ይጀምራል። ቆይቶ ወደ አባቱ እያየ “አባቴ አልቻልሁም” አለው። አሁንም አባቱ “ሙሉ አቅምህን ተጠቀም ትችላለህ” አለው። ልጁም እንደገና ሞከረ አልቻለም። አባቱንም “አባቴ ሙሉ አቅሜን ተጠቀምሁ ግን አልቻልሁም” አለው እያዘነ። “ሙሉ አቅምህን አልተጠቀምህም”። እኔ አብሬህ አለሁ። እንዳግዝህ ግን አልጠየቅኸኝም!”አለው አባትየው። እርዳታ መጠየቅ ክብራችንን የሚቀንስብን የሚመስለን ስንቶቻችን ነን? “አግዘኝ” ማለት ሞት የሆነብን። “እሱን እርዳኝ ከምል ብሞት ይሻለኛል” ብለን እናውቃለን እኮ። አቅም እናድርጋቸው። አንዳንዶች “በእኔ ነው እኮ እዚህ የደረሰው እንጂ እሱ ምኑን ችሎት”ይላሉ። ይበሉ! ለእኛ መወጣጫ አድርጎ ካዘጋጃቸውስ? እሱን ፈርተን አይደል “እርዱኝ”፥ “አግዙኝ” የማንለው። “ኧረ በኋላ ጉራውንም አልችለው”እያልን ስንቱ አመለጠን? አንዳንዶቻችን ለመርዳት፤አንዳንዶቻችን ለመረዳት የተፈጠርን ቢሆንስ? ግን ደግሞ “ይሄ አለኝ ይሄን ጨምርልኝ፤እስከእዚህ መጣሁ የቀረውን አግዘኝ”፥ ለማለትም ትንሽም ይኑረን። ሰዎች ጥረታችንን ሲያዩ ደስ እያላቸው ይረዱናልና። የወር ሰው ይበለን። አልቻልሁም አግዙኝ! ሳምራዊት ንጉሤ 2056